ካፍ የሞሮኮ እና የሴኒጋልን ጨዋታ በተመለከተ ውሳኔዎችን አሳለፈ!

የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል ካፍ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈበትን መግለጫ ንጋቱን አውጥቷል።

በዚህም መሰረት በሴኒጋል በኩል ደጋፊዎች ባሳዩት ያልተገባ ባህርይ፣ ተጫዋቾቹ ከሜዳ በመውጣታቸው እና አምስት የሚደርሱ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከታቸው የሀገሪቱ አግር ኳስ  ፌዴሬሽን በጥቅሉ 615,000 ዶላር ቅጣት ተላልፎበታል። የቡድኑ አሰልጣኝ ፓፓ ቲያው ደግሞ ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርገው ስለነበር በ5 ቀጣይ በካፍ ስር በሚተዳደሩ  ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸውን እንዳይመሩ ታግደዋል። ከዚህ በተጨማሪም የ100,000 ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎባቸዋል። እስማኤላ ሳር እና ንዲዬ የተሰኙት የሀገሪቱ ተጫዋቾችም እያንዳንዳቸው 2 2 የካፍ ጨዋታዎች እግድ ተላልፎባቸዋል።

በሞሮኮ በኩል እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስታድየሙ ኳስ አቀባዮች ፣ ተጫዋቾች እና ቴክኒካል ቡድኑ ባሳዩት ያልተገባ ባህርይ እንዲሁም ደጋፊዎች ጨረሮችን በመልቀቅ ጨዋታ በመረበሻቸው በአጠቃላይ 315,000 ዶላር ተቀጥቷል። አሽራፍ ሀኪሚ ደግሞ በተመሳሳይ ባሳየው ያልተገባ ባህርይ 2 የካፍ ጨዋታዎች ላይ እንዳይሰለፍ ቅጣት ሲተላለፍበት እስማኤል ሳባሪ እንዲሁ የ3 ጨዋታዎች  እና የ100,000 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል።

የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሴኒጋል ጨዋታ በማቋረጥ የአፍሪካ ዋንጫ አንቀፅ 82 እና 84ን የጣሰ ተግባር ፈፅሟል፤ ስለዚህ ዋንጫውን ሊነጠቅ ይገባል ሲል ለካፍ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ካፍም ጉዳዩን በጥልቀት እንደተመለከተው በመግለፅ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.