ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በማራቶን ውድድሮች የደመቁበት ሳምንት!

በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያን አትሌቶች ባለድል የሆኑባቸው ሁለት የማራቶን ውድድሮች ተደርገዋል።

ትላንት በተደረገው የዱባይ ማራቶን በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያውያኑ አሸናፊ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተከታታይ በመግባት ውድድሩን ኢትዮጵያውያን የደመቁበት ማድረግ ችለዋል።

በወንዶቹ አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀው ንብረት መላክ ሲሆን 2:04:00 ማራቶኑን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ ነው። ከሱ በመከተል ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ያሲን ሀጂ ሁለተኛ ሲወጣ ሩዋንዳዊው ሯጭ ጆን ሀኪዚማና ደግሞ ውድድሩን ሶስተኛ በመውጣት ጨርሷልተ ከሱ በመከተል ያለውን 7 ደረጃዎች ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ማንንም ሳያስገቡ ተቆጣጥረውት ውድድሩን አጠናቀዋል።በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ2023 የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ንብረት መላክ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየትም ” በመጀመሪያ ውድድሬ  ማሸነፍ ሁሌም ስመኘው የነበረ ነገር ነው። ቀጣይ የአለም ሪኮርድን መስበር እፈልጋለሁ።” ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

በሴቶቹ ደግሞ 2:18:31 በመግባት አሸናፊ የሆነችው አንቺንአሉ ደሴ ስትሆን ሙልዬ ደከቦ እና ፋንቱ ወርቁ ደግሞ እሷን ተከትለው 2ኛ እና 3ኛ ወጥተዋል። በተመሳሳይ እንዲሁ በሴቶቹም እስከ 10ኛ ደረጃ ድረስ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ተቆጣጥረውታል። የግሏን ፈጣን የሮጠችው አንቺንአሉ ደሴ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ” የግል ፈጣን ሰአቴን ማስመዝገቤ ጥሩ ነገር ነው፤ ግን ወደፊት ከዚህ በበለጠ ፈጣን ሰአት  የምሮጥ ይመስለኛል” ብላለች።

በሳውዲ አረቢያ ዋና ከተማ በተካሄደው የሪያድ ፌስቲቫል ማራቶን ደግሞ አበባው ሙኒዬ የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ሯጭ 2:09:31 በመግባት አሸናፊ ሆኗል። በሴቶቹ ዘርፍ ማሪስ ሎሀሚ የተሰኘች ፈረንሳዊ አትሌት 2:25:56 በመግባት ቀዳሚ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች። በዚህ ታላቅ ፌስቲቫል ላይም በተለያዩ ርቀቶች ከ50,000 በላይ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.