ኢትዮ ቴሌኮም የእቅዱን 81 በመቶ ማሳካት መቻሉ ተገለጸ

ዛሬ ጥር 21 ቀን 2018 የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2018 በጀት ግማሽ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው በእለቱ ለተገኙ በርካታ የሚዲያ ተቋማትሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ኩባንያው ጥራቱን የጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም የገቢ ምንጭን በማስፋት እና የደንበኞችን ቁጥር ማሳደግ እንዲሁም የደንበኞችን እርካታ ከማሳደግ አንጻር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር 87 ነጥብ 1 ሚሊየን መድረሱን ያሳወቁ ሲሆን ከባለፈው ዓመት በ6 ሚሊየን ጭማሪ ማሳየቱንም በመግለጽ በግማሽ ዓመቱ የስራ ሂደት ከ85 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን እንዲሁም የእቅዱን 81 በመቶ ማሳካት መቻሉን በእለቱ በሰጡት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ 133 ከተሞች የ4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ መሆናቸውንና አሁን ላይ 4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ ከተሞች 1 ሺህ 69 መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን በ278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መቋቋማቸው አጠቃላይ ሞባይል ጣቢያዎች ቁጥርም 10 ሺህ 288 ማድረሱ በዋና ስራ አስፈጻሚዋ በኩል ተገልጿል።

በእለቱ ኩባንያው በተለይም በገጠር አካባቢ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኔትወርቅ ተጠቃሚ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን 204 ምርትና አገልግሎቶች ለደንበኞች የቀረቡ ሲሆን÷ ከእነዚህም 81ዱ አዳዲስ፤ 74 የሚሆኑት ደግሞ ማሻሻያ የተደረገባቸው እንደሆኑ ተገልጿል ።

በአሁኑ ወቅት በአለማችን አስጊ የሆነው የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን ኢትዮ ቴሌኮም መተግበር መቻሉን ጨምረው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

በመጨረሻም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በእለቱ የተለያዩ ተቋማት ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት የእለቱ መርሀ ግብር ተጠናቋል።

✍️ ፈለቀ ደምሴ

Leave a Reply

Your email address will not be published.