ሮናልዶ ለአንዲት ሴት ልዩ ስጦታ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ አለ!
ሮናልዶ ከአመታት በፊት በጁቬንቱስ ሳለ ከፒርስ ሞርጋን ጋር ካደረገው ቃለ-ምልልስ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው ንግግሩ 13 አመቱ ሳለ ከጓደኛው ጋር ይርባቸው ስለነበር ከሚኖሩበት ስታድየም አቅራቢያ ወደአንድ የማክዶናልድ በርገር ቤት ምግብ ለመለመን ያቀኑ እንደነበር እና ያኔም ሶስት የበርገር ቤቱ ሰራተኞች ምግብ እንደሚሰጧቸው የገለፀበት እንደሆነ አይዘነጋም።

ከዚህ በተጨማሪም ተጫዋቹ አግኝቶ ሊያመሰግናቸው እንደሚፈልግ በዛኑ ቃለ-ምልልስ ጠቅሶ ነበር። ፒርስም ይህን አስታውሶ ከሰሞኑ ከሮናልዶ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ላይ አንስቶለታል። ፒርስም ሁነቱን ካስታወሰው በኋላ ” ከአንዷ ጋር በቅርቡ በ’ኤርፖርት’ መገናኘትህን ሰማው” ብሎ ስለጉዳዩ በዝርዝር እንዲነግረው ጠየቀው።

ሮናልዶም በምላሹ ” በቅርቡ ከሪያድ ወደ ሊዝበን በሄድኩ ጊዜ በ’ኤርፖርት’ የተከለለ ቦታ ላይ ሳለን አንዱ ጓደኛዬ ‘ ክሪስትያኖ ተመልከት ምን እንዳየው’አለኝና ዞሬ አየሁ። ታውቃለህ ረጅም አመታት ቢቆጠር እንኳን ገና በአንድ እይታ ምታስታውሳቸው ሰዎች አሉ አደል። እንዳገኘኋት ተቃቅፈን ባለቤቴ ጆርጂንያ እና ልጆቼ ምን እየተፈጠረ እንዳለ አልገባቸውም። ኋላ ላይም ነገርኳቸው። ህይወት በትንግርት አጋጣሚዎች የተሞላ ሳጥን ነው። በመቀጠልም ከጓደኞቼ ጋር አወራሁ። አሁን ያን በርገር ይሰጡኝ የነበሩት ሰራተኞችን ለይተናቸዋል። በቅርቡ ለነሱ የተለየ ነገር አደርጋለሁ። ባገኘችኝ ጊዜ በመጠኑ ብትደነገጥም፤ አውርተናል። ለጓደኞቼም ስልኳን ውሰዱ ብያቸው ጊዜ ሲኖረኝ የሆነ ለየት ያለ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቻለሁ። በዛን ጊዜ ለረዱኝ ሰዎች በሙሉ ልዩ ነገርን ማድረግ እፈልጋለሁ” ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

ታሪኩ እዚህ ላይ አያበቃም ያኔ ከሮናልዶ ጋር በማክዶናልድ በርገር ቤት አብሮት ይለምን የነበረው ሆዜ ሴሜዶ በአሁኑ ሰአት የአልናስር እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ( CEO) ነው። የሁለቱ ጓደኝነት እጅግ ጠንካራ ስለነበር አካዳሚው ሆዜን ለቆ ሮናልዶን ለማቆየት ሲወስን ሮናልዶ የአካዳሚው አመራር ጋር በመሄድ ጭምር ጓደኛውን እንዲያቆዩለት ጠይቋቸው ሲፈቀድ በማረፊያ ዶርማቸው ውስጥ 5ኛ አልጋ እስከመጨመር ደርሶም ነበር። ሮናልዶ በስተመጨረሻ ” ህይወት አስደናቂ ነው፤ ፈጣሪ የሚገባህ ቦታ ላይ ያስቀምጠሀል” ሲል ሀሳቡን ያስረዳል።

ሮናልዶ በስተመጨረሻ ” ህይወት አስደናቂ ነው፤ ፈጣሪ የሚገባህ ቦታ ላይ ያስቀምጠሀል” ሲል ሀሳቡን ያስረዳል።

