” ኢትዮጵያ ያለችው እህቴን አይና በጥንካሬዋ እገረማለሁ” – ሲፋን ሀሰን

በነገው እለት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ48ተኛ ጊዜ ለሚከበረው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ተቋም ሲፋንሀ ሀሰንን እንግዳ አቅርቧል። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ለሀገረ ኔዘርላንድ የምትሮጠው አትሌት ሲፋን ሀሰን ባሳለፈነው አመት እጅግ ፉክክር በተሞላበት የሴቶች የፓሪስ ኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበረች ይታወቃል።

ይህች በብርታቷ ብዙዎች ሚጠቅሷት አትሌትም ለዚህኛው የሴቶች ቀን አመታዊ ክብረ-በአል መልእክት እንድታስተላልፍ ተመርጣለች።

አትሌቷ በነበራት አጠር ያለ ቆይታም የሚከተለውን ብላለች:

” ሴት ልጅ የተሻለች ስትሆን፤ ትውልዱም የተሻለ ይሆናል፤ ምክንያቱም እናት ደስተኛ ስትሆን እና በራስ መተማመን ሲኖራት ልጇም እንደዛው ይሆናል። እኔ ከአፍሪካ እንደመምጣቴ በሴቶች በኩል በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ እረዳለሁ፤ ነገር ግን ያንን ፈተና ወደ ጥንካሬ መቀየር ከኛ ይጠበቃል። የዛሬ 10 አመትም ሆነ 100 አመት ሴት ልጅ መፈተኗ አንቀርም እናም አንድን ፈተና ለቀጣዩ ፈተና እንደልምምድ በመውሰድ ብርቱ ተፋላሚ መሆን ያስፈልጋል። አንዳንዴ ሀገር ቤት( ኢትዮጵያ) ስሄድ ልጅ ያላትን እህቴን ሳያት ሁሌ ጠዋት ተነስታ ልጆቿን እና መላው የቤተሰቡን አባል ትመግባለች። እኔም ራሴን እመለከትና ‘ እኔማ ምን ሰራሁ’ እላለሁ በውስጤ፤ እንደዚህ አይነት እናቶች ጠንካራ እና አስገራሚ  ናቸው።ለታዳጊ ሴቶች ማስተላልፈው መልእክት ቢኖር ህይወት በከፍታ እና በዝቅታ የተሞላ ጉዞ ነው እናም ሁሌም ቢሆን በመጥፎ ጎኑ ብቻ ሊያዩት አይገባም። መጥፎውን ነገር ለጥሩ ነገር እንደመነሳሻ መጠቀም ይችላሉ። ‘ ይሄን ፈተና አልፌያለሁ፤ እናም ለቀጣዩ ደግሞ ከዚህ ትምህርት እወስዳለሁ’ የሚል እሳቤ በውስጣቸው ሊይዙ ይገባል።”

ሲፋን የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯን ያደረገችው በ2023 በለንደን ሲሆን በዛ ውድድሯም ሳትጠበቅ 2:18:33 በመግባት ማሸነፏ እና ለራሷ አዲስ ታሪክ መፃፏ ይታወሳል። አሁንም ታዲያ በወርሀ ሚያዚያ በሚደረገው የለንደን ማራቶን ላይ ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል የምትገኝ ሲሆን ልምምዷን በኬንያ እና የተለያዩ አካባቢዎች እየከወነች ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም ለዘንድሮው የአመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ‘ ላውረስ አዋርድ’ እጩ መሆን ችላለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published.