ሀገር አቀፍ የስልጠና ሞዴል እውን መፍትሄ ይሆናል? ( በባለሙያ የተሰጠ ትንታኔ)
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪነት ሀገር አቀፍ የስልጠና ሞዴል ለማውጣት ምክክር ተጀምሯል። በዚህ ምክክር ላይም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ‘ A’ ላይሰንስ ያለው ከፈለኝ ደርበው ከስፔን ሀሳቡን አካፍሎናል።
ከፈለኝ የስልጠና ሀሳብን አንድ ወጥ በሆነ መልኩ መገደብ ተገቢ አደለም ብሎ ያምናል። ” የእግር ኳስ ስርአት ልክ እንደፋብሪካ በሆነ ወጥ አሰራር ውስጥ የተቆለፈ አይደለም፤ ተሰጥኦ ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል” ሲልም ሀሳቡን ያስቀምጣል።
” ፒኬ ከወጣበት ላማሲያ ፒዮልም ወቷል፤ በቫልዴቤባስ( የሪያል ማድሪድ አካዳሚ) ከጎለበተ ናቾ እኩል ራውል ወይም አሴንሲዎ በዛው አድገው ወተዋል።” ሲልም እንዴት በተለያየ የአጨዋወት ዘይቤ በአንድ ቦታ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ሊፈሩ እንደሚችሉ ይሄ ማሳያ ነው በማለት ይጠቅሳል።
” በስፔን ማንም ‘አንድ ወጥ የሆነ የአጨዋወት ዘይቤ ይኑር’ ያለ የለም” የሚለው ከፈለኝ ከዴልቦስኬ ዘመን እስካሁኑ የዴላፎንቴ ዘመን ድረስ ብሄራዊ ቡድኑ የተለያዩ የአጨዋወት ዘይቤዎችን መተግበሩንም ይገልፃል። አንዳንዶቹ ሀሰተኛ 9 ቁጥር ተጠቅመዋል፤ አንዳንዶቹ አጫጭር የኳስ ቅብብሎች ላይ ትኩረት አድርገዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ፈጣን እና ቀጥተኛ እግር ኳስን ሲጫወቱ ተስተውሏል በማለትም ሀሳቡን በማስረጃ ደግፎ ያስቀምጣል። በዚህ መሀል ታዲያ ተመሳሳይ ሆኖ የቆየው ነገር ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ ራሳቸውን በሚገባ እንዲገልፁ የተሰጣቸው ነፃነት መሆኑን ይጠቅሳል።
የየዘመኑ የጨዋታ አቀራረብ ልዩነት እያንዳንዱ ትውልድ በራሱ መንገድ እንዲያንፀባርቅ አድርጎታል ሲልም ይናገራል። በአጠቃላይ ታዲያ አሁን የሀገሪቱን ጉምቱ አሰልጣኞች በማሰባሰብ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የስልጠና ሞዴል የማውጣት ሂደት ይሄን የተጫዋቾችን ነፃነት ይገድበዋል ብሎ እንደሚያምን ከሰጠው ሀሳብ መረዳት ይቻላል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ በራሱ ያለውን ብዝሀነት የተወሰኑ ሰዎች ባወጡት ወጥ የአጨዋወት ዘይቤ መገደብ ተገቢ አለመሆኑን ነው ከፈለኝ የገለፀው።
ይህ ሀገር አቀፍ የስልጠና ሞዴል ምክክር በቀጣይ ምን አዳዲስ ነገሮች ይዞ ይመጣል የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል።
✍️ በዮናታን አየለ የተፃፈ
ሰኔ 22,2017 አ.ም