አለም-አቀፍ የእግር ኳስ ስልጠና ሞዴሎች ምን ይመስላሉ?( በባለሙያ የተሰጠ ትንታኔ)

በትላንትናው እለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሀገር አቀፍ የስልጠና ሞዴል ለማውጣት ምክክር በመጀመሩ ዙሪያ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ‘ A’ ላይሰንስ ያለውን የአሰልጣኝ ከፈለኝ ደርቤን ሀሳብ ከስፔን ይዘንላችሁ ቀርበን ነበር።

ከፈለኝ ከዚህ በተጨማሪ በዘመናዊ እግር ኳስ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያሉ የስልጠና ሞዴሎችን ያካፈለን ሲሆን በሱ ላይ ተመስረተን የሚከተለውን ፅሁፍ አቅረበንላችኋል። እኚህ የስልጠና ሞዴሎች ‘ የሙስካ ሞስቶን የአሰለጣጠን ዘይቤዎች’ ሲሰኙ በስራቸው 7 አይነት ዘዴዎች አሏቸው።

1. ቀጥተኛ ትእዛዝ

በዚህ የስልጠና ሞዴል አሰልጣኙ ለተጫዋቹ ምን ማድረግ እንዳለበት በቀጥታ ይነግረዋል። ተጫዋቾችም የአሰልጣኙን ሀሳብ እንደወረደ ይቀበላሉ። ይህ አይነቱ ዘዴ አዳዲስ ቴክኒኮችይዘን ለመማር እና ‘ታክቲካል ዲሲፕሊንን’ ለመገንባት ሲያግዝ በሌላ መልኩ የተጫዋቾችን የፈጠራ ብቃት እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ሊገድብ ይችላል።

2. የእርስበእርስ መማማሪያ ዘዴ

ተጫዋቾች ጥንድ ሆነው አልያም በቡድን እንዲሰሩ ይደረጋል፤ ተራበተራ እየተፈራረቁም አንዱ ሲሰራ ሌላኛው እየተመለከተ አሰልጣኙ በሚሰጠው መቆጣጠሪያ ቅፅ( Checklist) መሰረት ብቃቱን ይመዝናል። ይህ አይነቱ ዘዴ የቡድን ተግባቦትን የሚጨምር ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾች እንዴት ብቃት መመዘን እንዳለባቸው እንዲማሩ ያግዛል።

3. በጥያቄ ማስተማር

በዚህ ዘዴ አሰልጣኙ የሆነ የጨዋታ ላይ አጋጣሚ መርጦ በዚህ ወቅት ምን አይነት ምላሽ ትሰጣላችሁ ሲል ጥያቄዎችን ይጠይቃል፤ ተጫዋቹም ትክክለኛውን አማራጭ እስኪያገኝ ድረስ በእንቅስቃሴዎች እና በቅብብሎች የተለያዩ ሁነቶችን በመሞከር መልሱን በልምምድ ውስጥ እንዲያገኘው ይደረጋል። ይህ አይነቱ ዘዴ የአእምሮን የማመዛዘን ብቃት እንደሚጨምር ይታመናል።

4. የሜዳ ላይ ‘ ፕሮብሌሞችን'( ሁነቶችን) በመፍጠር ማስተማር

አሰልጣኙ ለተጫዋቾች የሆነ ቻሌንጅ ፈጥሮ ይሰጣቸው እና በዛ መሰረት እንዲጫወቱ ያደርጋል፤ ያ ጨዋታም የራሱ የሆነ አላማ ይኖረዋል። ለምሳሌ አንድ አሰልጣኝ  3 በ 3 ወይም 5 በ 5 የሆነ ግጥሚያ እንዲኖር ያደርግና የዚህ ግጥሚያ ህግም አንድ ተጫዋች ከ2 ንክኪ በላይ ኳስ እግሩ ላይ ሳያቆይ ማቀበል ወይም እንደሁኔታው መምታት ሊሆን ይችላል። የዚህ ስልጠና አላማም ተጫዋቹ ክፍተቶችን በቶሎ አንብቦ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በመግባባት የጨዋታውን ፍጥነት መጨመር ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ እንዲህ እየተባለ በሌሎችም መንገዶች አሰልጣኙ ጨዋታውን ማሳደግ የሚፈልግበትን ቦታዎች ማጎልበት ይችላል።

5. ለታክቲክ ቅድሚያ መስጠት

ይሄኛው ዘዴ ደግሞ ከክህሎት( Skill) በላይ ታእቲካዊ መረዳትን ማጎልበት ላይ ያተኩራል። የታክቲካል አረዳድን ከፍ ለማድረግ፣ ክህሎቶችን መሬት ላይ ለወረዱ መፍትሄዎች ለማገናኘት እና የልምምድ ጨዋታዎችን የበለጠ ጥቅም ያላቸው እንዲሆኑ ያደረጋል።

6. አሰልጣኝ በሚወስነው ከባቢ መጫወት

በዚህኛው የስልጠና ዘዴ አሰልጣኙ የመጫወቻ ከባቢውን በራሱ መንገድ ያበጃጀዋል። ይህ ማለት የጨዋታ ዘዴ፣ የመጫወቻ ቦታ እና ህጎቹ አሰልጣኙ ባወጣው መስፈርት ይሆናሉ። ይህ ዘዴ የትኛውንም የጨዋታ ሁኔታ የሚላመዱ ብልህ ተጫዋቾችን ለመፍጠር ይረዳል።

7. ጨዋታን የመረዳት ዘዴ

ይሄ የ6ተኛው ዘዴ ተመሳሳይ ሲሆን ጨዋታን መረዳት እና በጨዋታ ወቅት ብልሀት የተሞላባቸው ውሳኔዎችን መወሰን ላይ ያተኩራል። እንዲህ አይነቱ የስልጠና ዘይቤ ተጫዋችን ለከፍተኛ ፉክክር ጨዋታዎች የሚያዘጋጅ ሲሆን የታክቲካል አረዳድን ይጨምራል።

በአጠቃላይ ከእነዚህ 7 የስልጠና ዘዴዎች የፈለጉትን መርጠው አሰልጣኞች ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉና ይሄ ነው የተሻለው የሚባል የለም፤ ዋናው ነገር የትኛው የተጫዋችን የጨዋታ አረዳድ እና መጎልበት ያሳድገዋል የሚለውን መርጦ መጠቀሙ ነው።

✍️ በዮናታን አየለ የተፃፈ

ሰኔ 23,2017 አ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.