“ልቤን ከጊዮርጊሳዊነት የሚቀይርብኝ ማንም የለም እሰኪ አንዱ በኔ ቦታ ይቀመጥ “

አቶ አብነት ገብረመስቀል  የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት ናቸው። በእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ ውስጥ በበጎ ከሚነሱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደባሉ። በሚወዱት ክለባቸው ብቻ ሳይሆን ለውድ አገራቸው እግር ኳስ እድገት ያለመታከት የሚሠሩ አንጋፋ ባለፀጋ ሲሆኑ፤ ዘመኑን የሚመጥኑ የእግር ኳስ እድገት ቀያሽ መፍትሔ መንገዶችን ሲያመነጩ ቆይተዋል። በቅርቡም የሚወዱትን ክለባቸውን የበለጠ ወደ ስኬት ማማውና ዓለማቀፍ ጎዳና ያመራዋል ያሉትን ሀሳብ ከአጋሮቻቸው ጋር አመንጭተው እንካችሁ ብለዋል። በዚህ አዲስ የስፖርት እሳቤ እና በወቅታዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ዙሪያ ከ Ethiopians sport.com እና ኢትዮ ማዕድ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በጽ/ቤታቸው ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለምልልሱን ሁለተኛ ክፍል እነሆ!

ጥያቄ፦ በወቅታዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጉዳይ ከኢትዮጵያንስ ስፖርት ዶትኮም ድረ ገጽ እና ከኢትዮ ማእድ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር ቃለመጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ አብነት፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ

ጥያቄ፦ ምንግዜም ካፒታል አ/ማ ህዳር 12 ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ይፋ ሆኗል፤ በተደረገው ገለጻም አክሲዎኑ እና ክለቡ የየራሳቸው መተዳደሪያ እንዳላቸው እና ደጋፊውን በሙሉ የሚያሳትፉ መሆኑን ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። ቢሆንም አሁንም አንዳድ ደጋፊዎች በማህበራዊ ሚደያዎች ላይ ከባለቤትነት ልንወጣ ነው የሚል ጥያቄ አላቸው እና ለነዚህ ደጋፊዎች ስጋት መልስ ካለዎት?

አቶ አብነት፦ ይሄ አድካሚ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ነገር አሁን አይደለም የተጀመረው ከሁለት ከሦስት ዓመት ጀምሮ ገና ከጥንስሱ አንዳንዶች ጥሩውን ነገር ከማሰብ ይልቅ መጥፎ ጎኑን ነው ቀድመው የሚያዩት ለምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ይሄ ምናልባት ከደማችው ጋር አብሮ የመጣ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ቀና ነገሩን የማሰብ ሁኔታ በፍፁም በአንዳዶች ላይ አይታይም፡፡

ይህ ነገር ሁሉም የሚኮሩበትና የሚደሰቱበት መሆን አለበት። እንደዚህ ዓይነት ታሪክም ሲሰራ  የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ክለብ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ። በ1928 ዓ.ም በቡሄ ጭፈራ ሳንቲም በመለመን በተሰበሰበ ገንዘብ የተቋቋመ ክለብ ዛሬ ትልቅ አክሲዮን ድርጅት እንፍጠር ሲል ሁሉም መደሰት ነው ያለበት፡፡

እንኳን በህይወት ያሉት ይሄን ታሪክ ሳያዩ ያለፉት ሁሉ የሚያኮራ ይመስለኛል፡፡ ትልቅ ታሪክ እየሰራን ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ታሪክ ውስጥ ለመሳተፍ ደግሞ ቀላል ነው፡፡

ሁሉም በአቅሙ ነው የሚሳተፈው፡፡ ሀብታምና ደሃ አይለይም፡፡ ጊዮርጊስ የሁሉም ክለብ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ወቅት ክለቡ ሊሸጥ ነው ሲሉ ከረሙ ክለቡ እንደማይሸጥ እንደማይለወጥ አድርገን አሳየናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ገንዘብ ያለውና የሌለው ክለቡ ሊዋጥ ይችላል በሚል ምናልባት ክለቡ የሚሸጥ የሚለወጥ ወይም ወደ ሀብታሞች ጎራ የሚገባ ይመስላቸዋል፡፡ ገንዘብ የሚጠላ ክለብ የለም፡፡ እግር ኳስ ከገንዘብ ውጪ የትም ሊሄድ አይችልም፡፡ ፋክቱ ይሄ ነው ይሄን መገንዘብ የማይችል ወደኋላ የቀረ አንዳድ ሰው ሁሉንም ወደኋላ ይዤ ልጎትት የሚል ከሆነ እኛ በምንም ዓይነት መንገድ ጊዮርጊስ የጀመረውን ጎዳና ይዞ ነው የሚቀጥለው፡፡

ስለዚህ ባለፈው ቅዳሜ ማታ በሸራተን የተካሄደው የምንጊዜም  ካፒታል ሰርቪስ አ.ማ. ምስረታ በጥሩ ሁኔታ ነው የተካሄደው 51% እና 49%።  49ኙ የኮርፖሬት ቢዝነስ ባለቤቶች እንዲሆን 51ዱ አብላጫው (Majority) የደጋፊው እንዲሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ህዝባዊነቱን ጠብቆ ባለቤትነቱን በምንም መንገድ የማያሳጣው ነው፡፡ ሁለት ብራንች አለ አንደኛው ብራንች የፉትቦሉን (የክለቡን) ሳይድ ይዞ የሚሄድ ነው፡፡ ክለቡ የራሱ የሆነ አሴት አለው፡፡ ወደ 94 ሚሊዮን ብር የተገመተ አለ የዛሬ 2 ዓመት እሱኑ ነው የተጠቀምነው። በአሁኑ ሰዓት ከ100 ሚሊዮን በላይ አሴት አለው ክለባችን፡፡ ያን ገንዘብ በሙሉ እዚህ ውስጥ አምጥቶ ከቶ ድንገት ይሄ ቢዝነስ ባይሆን እንዲጎዳ አንፈልግም ክለባችን ለዘላለም እንዲኖር ነው፡፡ እንደዚህ ነው  የተደረገው። እያንዳንዱ ስፖንሰር ለ15 ዓመት የሚሆን ውል ገብቷል፡፡ ይሄ የስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ነው፡፡ ያን ገንዘብ ማንም የሚነካው የለም፡፡ ሁልጊዜ ከስፖንሰሮቻችን ከሚቀጥሉት 15 ዓመታት ክለቡን እለት ከእለት ሥራውን፣ ደመወዝ እና የተለያዩ ወጪዎችን የሚሸፍነው ከዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ያለንበት ቦታ በጣም አስተማማኝ (Safe) ነን ማለት ነው።

ወደ ቢዝነሱ ውስጥ ስንገባ ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው ያዋጡት አሥር አሥር ሚሊዮን ያዋጡ ድርጅቶች ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከትርፉ የሚያገኙት ገንዘብ የለም፡፡ የሚያዋጣውንም ደጋፊ ጨምሮ ለክለቡ ለሚቀጥለው 10 ዓመታት ምንም ዓይነት የትርፍ ክፍያ የለውም፡፡ ዴቪደንድ አያገኙም ማናቸውም ያ ትርፉ እየተደመረ በ10 ዓመት ውስጥ ይሄ የተጠራቀመው ገንዘብ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ውስጥ በመግባት አትራፊ በሆኑ በጥናት በተደገፉ የቢስነዝ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የሚያተርፈውን ገንዘብ ወደፊት ለክለቡ እንደስቴዲየም ሌሎችም ቢዝነስ ውስጥ በመሳተፍ የዚህ ትርፍ ወደፊት ስፖርት ማህበሩን ይደግፈዋል፡፡

ከ10 ዓመት በኋላ ህዝቡም፣ ደጋፊው ያዋጣውም በስራው ተደስቶ ኩባንያዎቹም በስራው በውጤቱ በአትራፊነቱ ተደስተው ሊቀጥሉበት ይችላሉ ወይም ትርፋችንን እንፈልጋለን ሊሉ ይችላሉ እንደ ማንኛውም ሼር ካምፓኒ፡፡ ከሌላው የሚለየው  በየዓመቱ የሚያገኘውን ትርፍ ይሰበስባል ይሄ ለሚቀጥለው 10 ዓመት ምንም ዓይነት ገንዘብ አይነካም፡፡

በደጋፊው በኩል ልዩነት አያመጣም ሁሉም በአቅሙ እየተደራጀም ቢሆን 10 ሺህ ብር እንዲያወጣ  ሲባል አይሆንም ተባለ 5ሺ ሲባልም አይሆንም ተባለ ባይሆን እንደማንኛውም እንደ ባንኩ አሰራር በ1ሺ ብር አድርጉልን የሚል ሃሳብ ተቀባይነት አገኘና በደጋፊው ሃሳብ ተወሰነ፡፡ በአንድ ሺህ ብር አንድ ሰው ለብቻውም ሆነ በጋራ መግዛት ይችላል የፈለገ ደግሞ 1 ሼር 1ሺ ብር ከሆነ የፈለገውን ያክል ሼር ሊገዛ ይችላል፡፡ ገንዘብ ያለው እስከ 10 ሺህ ሼር ሊገዛ ይችላል፡፡ ስለዚህ እኛ ደጋፊው 51% እንዲሞላ ለማድረግ በጠቅላላው እኛ ደጋፊዎቹ ሁላችንም  ከኩባንያዎች ሳይድ ከምንሆን ከደጋፊው ጋር በመሆን ከፍተኛ የሆነ ሼር ከደጋፊው ጋር አብረን ገዝተናል፡፡

ወደፊትም ሰዎች አሉ የሚመጡ ከደጋፊው ጋራ ሆነው ያንን 51%  ለማጠናከር፡፡ እና ጥሩ ነገር ነው ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ምንጊዜም ካፒታል ነው፡፡

ክለቡን ማንም የሚያነቃንቀው ሰው የለም፡፡ በየዓመቱ ከየድርጅቶቹ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የተፈራረምነው ውሎች አሉ፡፡ እነዚህ ገንዘቡን ይከፍላሉ እኛ ማኔጅ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ያ እየተሰበሰበ ግን ዝም ብሎ ማጥፋት ሳይሆን አንድ ቀን ምን እንደሚያጋጥም ስለማናውቅ ይሄ ድርጅት ደግሞ አትራፊ እየሆነ በጎን ክለባችንን ሁሉ ሊጠቅም የሚችል ነገር ቢዝነስ እየከፈተ ሊጎለብት ይችላል፡፡ ጥሩ ነገር ነው ትዕግስት ያስፈልጋል ግን፡፡ እኛም ሁላችንም ደግሞ በቅንነት መረዳት ያስፈልገናል፡፡

ጥያቄ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርንም በገንዘብ ደረጃ አብዛኛው ወጪ ሲሸፈን የኖረው በእርስዎና  ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚወዱ ጥቂት የልብ ደጋፊዎችና ስፖንሰሮች መሆኑ ይታወቃል።  አሁንም የተመሰረተው ምንግዜም ካፒታል አ/ማ አብዛኛው ወጪ ሊሸፈን የሚችለው በተመሳሳይ ነው እና ይህንን አክሲዮን ለማቋቋም የተፈለገው ለምንድን ነው ?

አቶ አብነት፦ እንግዲህ አንድ ቢዝነስ ስታቋቁም ለመክበር ነው ለመበልፀግ ነው፡

ጊዮርጊስ እንዲበለፅግ ነው፣ ጊዮርጊስ እንዲያልፍለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ኩባንያ ወደፊት ሆቴል ሊገዛ ይችላል፣ ቢራ ውስጥ ኢንቨስት ሊያደርግ ይችላል፣ ባንክ ውስጥ ኢንቨስት ሊያደርግ ይችላል፣ መንገድ ላይ ትራንስፖርቴሽን ላይ ቢዝነስ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ አትራፊነቱ ጥሩ በሆኑ ቢዝነስ ላይ ኢንቨስት እያደረገ ይሄ 150 እና 244 ሚሊዮን ብር የሚዋጣው ቶታሉ የአክሲዮን ካፒታሉ 244 ሚሊዮን ነው የታሰበው፡፡ ይሄን 244 ሚሊዮን ይዘን መታቀፍ አይደለም 244 ሚሊየኑን ሁለት ቢሊየን እንዲሆን ነው እምንፈልገው። ሁለት ቢሊየን ደግሞ ሲደርስ 4 ቢሊዮን እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ከተማ ውስጥ ፎቅ መግዛት እንፈልጋለን፣ የራሱ የጊዮርጊስ አፓርትመንቶች እንዲኖሩትና ከማንም ጥገኝነት እንዲላቀቅ እንፈልጋለን፡፡ ብዙ ነገር ነው እኛ እንጀምራለን የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ ይጨርሳል፡፡ ዋናው መንገድ መጥረግ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ባቡር ላይ ያለነው ሰዎች በየቦታው የምንጠባጠብ ከሆነ አደጋ አለው፡፡ ግን ተያይዘን የምንሄድ ከሆነ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ ነው የምገምተው፡፡

ጥያቄ፡- ምንግዜም ካፒታል አ/ማ ህዳር 12 ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ይፋ በሆነበት ስነስርአት ላይ መጠራት የነበረባቸው አባላት ተረስተዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያው አንዳንድ ወገኖች እየወቀሱ ነው፤ የተጠሩት እነማን ናቸው መስፈርቱስ ምን ነበር ?

አቶ አብነት፡- ምንግዜም ካፒታል አ/ማ መክፈቻ ላይ በዋናነት ትላልቅ አክሲዮን የሚገዙ አጋሮቻችን መቅረት አልነበረባቸውም እነሱ ተጠርተዋል። ሌላውን ግን በተወሰነ ቁጥር በየአቅጣጫው ባላንስ አድርገው እንዲጠሩ ለሚመለከታቸው ኮሚቴዎች ሰጥተናል እኛ ሁሉ ቦታ ገብተን መስራት አንችልም፡፡ ቢሆንም ማን ተጠራ ማን ቀረ ሳይሆን ዋና አላማውን ማሳካት ነው። በኮቪድ ምክንያት ሁሉንም መሰብሰብ ስለማይቻል በናንተ በሚዲያው በኩሉ ምንግዜም ካፒታል አ/ማ ይፋ ለማድረግ እና ባለሃብቶችን ቃል ለማስገባት ነው እሱንም አሳክተናል፡፡

በቀጣይ ደግሞ ያቀድነው ብዙሃኑን ደጋፊ ሰፊ ሜዳ ላይ አንሰበስባለን ያንግዜም እጅግ በርካታ የሆነውን ደጋፊ በኮቪድ ምክንያት  በሙሉ አጭቀን መሰብሰብ አንችልም ፡፡

አሁንም ለምን አልተጠራሁም ብሎ የሚያኮርፍ መኖር የለበትም። ዋናው የጊዮርጊስ ደጋፊ አላማው ላይ አተኩሮ ጊዮርጊስን ራሱን ማስቻል አለበት። በትንንሽ ነገር ላይ ማተኮር የለበትም እኔ ለምሳሌ ባልጠራ ብጠራ ልቤን ከጊዮርጊሳዊነት የሚቀይርብኝ ማንም የለም እሰኪ አንዱ በኔ ቦታ ይቀመጥ። ከተወሰነ ቁጥር በላይ ቦታ ከሌለው እኔን ቢተውኝ ለጊዮርጊስ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ቦጣም ትኩረት ሰጥቼ አልጨነቅበትም። ዋናው ባለሃብቶቹን ከያዝንና ጊዮርጊስን ማቆም ከቻልን እኛ እኮ በጊዮርጊስ የተሳሰርን ቤተሰቦች ነን የትም አንሄድም፤ ቦታው ላይ ባንገኝም ብንገኝም ጋባዥም ተጋባዥም እኛው ነን፤ እኔ ቤተሰብ ውስጥ ለየት ያለ ግብዣ ጠርቼ ቦታ ቢጠበኝ የማይቀየሙኝን ቤተሰቦቼን ቆርጬ ነው የማስቀረው። ስለዚህ ትክክለኛ የጊዮርጊስ ደጋፊም እንደዛው ነው የሚረዳው። ነገር ግን ነገሩን የሚያራግቡት የጊዮርጊስን ሰላም የማይፈልጉ ጥቂት አነብናቢዎች ናቸው እነሱን ለማቆም አይቻልም ፡፡

ጥያቄ፦ አንዳንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደርስዎ እንዳደርስላቸው ያቀረቡት ሀሳብ አለ። በኮቪድ ምክንያት ስራ ያጡ እና ወጣት ተማሪዎች ለረጅም ግዜ ክፍያ ባለመክፈላቸው አዲሱን መጣወቂያ መውሰድ አልቻልንምና ለኛ ምን ታስቧል ይላሉ?

አቶ አብነት፦ እንዳልከው ኮቮድ የሁሉንም ቤት ነው ያንኳኳው። አቅም አጥተውም ያልከፈሉ ይኖራሉ፤ እያላቸውም እየተዘናጉ ሳይከፍሉ ቆይተው ኮቪድን ሰበብ የሚያደርጉም አሉ።

ይህንን በማጣራት ቢሯችን የሆነ መፍትሄ ይሰጣል። በሽታው አስከፊ ነው ሁለተኛ ኢኮኖሚው ተመቷል ስለዚህ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት አልከፈሉም ብለን አናባርራቸውም እነሱም ራሳቸውን ገምግመው ተጋግዘን እናልፈዋለን፡፡

ጥያቄ፦ ለነበረን ቆይታ በአድማጮቻችንና በድረ ገጻችን አንባቢያን ስም እናመሰግናለን።

አቶ አብነት፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ማስታወሻ፦ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ከክለብ መሪነታቸው ባለፈም ታላቁን ሚድሮክ ኢትዮጵያን በዋና ስራ አስፈጻሚነት የሚመሩ መሆኑ ይታወቃል። በርካታ ማህበራዊና ሀገራዊ ጉዳይ ላይም ሚናቸው የሚፈለግ ስለሆነ በተጣበበ ጊዜያቸው ላይ ለሰጡን አጠር ያለ መግለጫ እያመሰገንን  በቀጣይም ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን።

አቶ አብነት ገብረመስቀል  የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት ጋር የነበረንን ቆይታ በዚሁ ፔጅ በክፍል አንድ ፖስት ላይ ስለወቅጣዊው የአሰልጣኞች ጉዳይ ይዘን ቀርበናል

ይመልከቱት

በተጨማሪም ሙሉ ቃለምልልሱን ከራሳቸው አንደበት በተወዳጁ ብስራት ኤፍኤም 101.1 ላይ በኢትዮ ማእድ ፕሮግራም

One thought on ““ልቤን ከጊዮርጊሳዊነት የሚቀይርብኝ ማንም የለም እሰኪ አንዱ በኔ ቦታ ይቀመጥ “

Leave a Reply

Your email address will not be published.