” የአሁኑ አሰልጣኝ ከብዙ ድርድር በኋላ ነበር የመጡት እንግዲህ አስረን አናስቀምጠውም ” አቶ አብነት ገብረመስቀል
አቶ አብነት ገብረመስቀል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት ናቸው። በእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ ውስጥ በበጎ ከሚነሱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደባሉ።
በሚወዱት ክለባቸው ብቻ ሳይሆን ለውድ አገራቸው እግር ኳስ እድገት ያለመታከት የሚሠሩ አንጋፋ ባለፀጋ ሲሆኑ፤ ዘመኑን የሚመጥኑ የእግር ኳስ እድገት ቀያሽ መፍትሔ መንገዶችን ሲያመነጩ ቆይተዋል።
በቅርቡም የሚወዱትን ክለባቸውን የበለጠ ወደ ስኬት ማማውና ዓለማቀፍ ጎዳና ያመራዋል ያሉትን ሀሳብ ከአጋሮቻቸው ጋር አመንጭተው እንካችሁ ብለዋል።
በዚህ አዲስ የስፖርት እሳቤ እና በወቅታዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ዙሪያ ከ Ethiopianssport.com (አትዮጵያንስ ስፖርት ) እና ኢትዮ ማዕድ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በጽ/ቤታቸው ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
የቃለምልልሱን የመጀመሪያ ክፍል እነሆ!
ጥያቄ፦ በወቅታዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጉዳይ ከኢትዮጵያንስ ስፖርት ዶትኮም ድረ ገጽ እና ከኢትዮ ማእድ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር ቃለመጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አብነት፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ
ጥያቄ፦ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኙ ኧርነስት ሚድንድሮፕ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ስላሳሰበኝና ቤተሰቦቼም በሁኔታው ግራ ስለተጋቡ በሚል ሰበብ ውሌን አፍርሼ እንድሄድ ይፈቀድልኝ ሲሉ ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል። ክለቡም ጥያቄያቸውን ተቀብሎታል ወይ? ከተቀበለውስ ክለቡ ከቅርብ ዓመታት ወዲሕ አሰልጣኞች ለረጅም ግዜ ሊቆዩለት አልቻሉም ይህ አንዴት ሊሆን ቻለ ?
አቶ አብነት፦ እንግዲህ የአሁኑ አሰልጣኝ ከብዙ ድርድር በኋላ ነበር የመጡት፡፡ አሰልጣኙ ያው ባደረግልናቸው አቀባበልና በስምምነታችን ውሉን ሲፈርሙ በጣም ደስተኛ ነበሩ ገንዘቡም ቢሆን እስከዛሬ ለአስልጣኞች ከሚከፈለው ሁለት እጥፍ የበለጠ ነበር ያደረግንላቸው የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ አሟልተን በቢሾፍቱ አካዳሚ ስራቸውን ጀመረው ነበር፡፡
ከጀመሩ በኋላ የመጀመሪያው ጥያቄያቸው ትንንሽ ልጆችን አልፈልግም ብለው ማሰናበት ነበር፡፡ ወጣቶቻችን ማሰናበታቸውን በቦርድ አየነውና በወጣት ላይ መስራት የማይፈልግ አሰልጣኝ ካሁኑ እንዴት ሊሆን ነው? ብለን ቅር ብንሰኝም ሙሉ ኃላፊነት ስለሰጠናቸው ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ካሰናበቷቸው አንዳንዶቹ እንዳውም ከ20 አመት በታች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው ወደ ታንዛኒያ የሄዱ ተስፋ የተጣለባቸው ልጆች አሉ፡፡
እንግዲህ የአሰልጣኙን ፍላጎት ማሟላት አለብን በሚል እና ትልቅ አሰልጣኝ ስለሆኑ ተቀብለን በስራቸው ጣልቃ ሳንገባ ሁሉንም ለሳቸው ትተንላቸው ነበር፡፡ ይሄም በእንዲህ እያለ አሰልጣኙ ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጠየቁኝ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያው እንደሌላው ሀገር አንድ አንድ ጊዜ ችግር ይገጥማታል አሁን ችግር አለ 1000 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው ችግሩ ያለው እዚህ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት እና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጽህፈት ቤቶች ያሉባት ከተማ ናት እንደ ኒው ዮርክ ከተማ ማለት ናት ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉ፣ አምባሳደርስ፣ ዲፕሎማት፣ ሁሉ እዚህ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ሁኔታ ሊያስፈራህ ወይም ሊያሳስብህ አይችልም፡፡ ይሄ ደግሞ በአጭር ጊዜ የሚያልቅ ነው ስለተባለ ስራህ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገህ ስራህን ቀጥል ብዬ በሚገባ አስረድቸዋለሁ፡፡
እሺ ምንም ችግር የለም በማለት ተስማምቶ ስራውን ከቀጠለ በኋላ ልጆቹ ደክሟቸዋል እረፍት ያስፈልጋቸዋል በማለት ለ6 ቀን ተጨዋቾቹን አሰናብቷቸዋል፡፡ አሁንም በምንም ዓይነት በአሰልጣኙ ሥራ ውስጥ አንገባም በሚል አልፈነው ነበር ስድስት ቀን እረፍት ሰጣቸው ተጨዋቾቹም አዲስ አበባ መጡ ቀጠለና ግድያ የሚፈፀምበት አገር ውስጥ ሆኜ ለማሰልጠን ባለቤቴም እኔም አልተመቸንም አለ፡፡
ከኳሱ ጋር እንደማይገናኝ በሚገባ አስረዳነው አንተ የኳስ አሰልጣኝ ነህ አክቲቪስት አይደለህም ለምን እዚህ ውስጥ ትኩረት ታደርጋለህ በማለት በድጋሚ አስረድተነው ከሄደ በኋላ አምባሳደራችንን አግኝቼ በጣም አስጊ ቦታ ላይ ነው ኢትዮጵያ ያለችው አለኝ በማለት ለአቶ ነዋይ ለቦርድ ፀሐፊያችን በቴክስት ይልክለታል፡፡
ይሄ ዳር ዳሩ አላማረንም ይሄ ሰውዬ ምን ሰበብ ነው የሚፈልገው በማለት ቢሮ ጠራሁትና ምንድን ነው የምትፈልገው አንደኛ ለተጫዋቾቹ እረፍት ሰጠህ ይህን ያደረከው ገና 15 ቀን እንደተለማመዱ እኔ በኳስ ውስጥ ያሳለፍኩ ሰው ነኝ ይሄ አልገባኝም ስለው የኔ አሰራር ይሄ ነው አለ፡፡ እሺ ተቀብዬሃለው አልኩትና ተለያየን፡፡
እሱ ተጨዋቾቹን ካሰናበተ በኋላ እዚህ ሳምንቱን ሙሉ ሌላ ስራ ሲሰራና ሌላ ክለብ ሲያመቻች ከርሞ በተጨማሪ ደመወዝ ለመሄድ እና አሰልጣኝ ካባረረ ክለብ ጋር ተነጋግሮ ሳውዝ አፍሪካ ለመሄድ መወሰኑን ሰማን። እንግዲህ እጅና እግሩን አስረን አናስቀምጠውም ነፃ የሆነ ሰው ነው፤ መሄድ ካለብህ በገባህበት ኮንትራት መሰረት የሁለት ወር ደመወዝህን ከፍለህ 6ቱ ቀን ደግሞ ልጆቹን እዚህ ካለአግባብ ቫኬሽን የሰጠኸው ሰበብ ስለሆነ እሱንም ደመወዝህ ተቆርጦ ያለውን ልዩነት ስትከፍልና ስትፈርም መልቀቂያህን እንሰጥሃለን ብለን ሸኝተነዋል፡፡ ኤጀንቱ ጋርም ደውለን ለመሄድ ሲፈልግ ለምን በጀርመን አምባሳደር ማሳበብ እንደፈለገ በደብዳቤ እንጠይቃለን፡፡ ይህ የትም ሀገር ቢሄድ ስፖርትና ሌላ ነገርን እየደባለቀ የሚያምታታ ሰው በመሆኑ ለሌሎችም ክለቦች ሼር የምናደርገው ነገር ይሆናል አፍሪካ ውስጥ እሱ እስካለ ይህንን በሌሎች እንዲደግም አንፈቅድለትም፡፡
ጥያቄ፡- ይህንኑ ለካፍ እና ለፊፋ እንዲሁም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቃችኋል?
አቶ አብነት፦ አሁን እሱ የሚፈርመው ወረቀት አለ ዛሬ ይሄን ሁሉ አድርገህ መሄድህ አግባብ ባይሆንም በስምምነታችንና በተነጋገርነው መሰረት ውል ማፍረስህን ፈርመህ እንለቅሃለን ብለነዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ውል ማፍረሻውን በውሉ መሰረት የማይሰጠን ከሆነ ወደ ፊፋ እንከሳለን ወደ ካፍም እናመለክታለን፡፡ ይሄ ቀላሉ ነገር ነው፡፡ ዋናው በቃል የተነጋገርነውን ስምመነት እንዲፈርም ነው፡፡
ጥያቄ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደፊት ወደ ሃገር ውስጥ አሰልጣኞች የመመለስ ሃሳብ አለው?
አቶ አብነት፦ አሁን ባለው ሁኔታ የኔንም ሆነ የቦርዱ ሀሳብ የሚያስቀይር አሰልጣኝ ሀገር ውስጥ የለም፡፡ ጊዮርጊስን የተሻለ ደረጃ ላይ እናደርሳለን ብለን ካሰብን የተወሰኑ አሰልጣኝ ብቻ ያለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው ማለት ከፍተኛ የኮቺንግ ትምህርት ቢወስዱና ራሳቸውን ቢቀይሩ ቢያሻሽሉ ጥሩ ነው ለኛም ደስ ይለናል፡፡
የድሮዎቹ ደግሞ ያው እድሜ አለ ትምህርቱም ደግሞ ጀርመን ሳይዋሃድ ሄደው የወሰዱት ትምህርት ነው አልፏል፡፡ በእድሜያቸው ሰርተዋል አሁን ግን የምንፈልገው ትልልቅ ቡድን ነው ኢንቨስት የሚያደርጉትን ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ክለቦች ሊጋቸው ጠንካራ ነው እነሱ ሊግ ውስጥ ሄዶ መጫወት የሚፈልግ ብዙ ተጫዋች አለ፣ እነሱ ሊግ ውስጥ ሄዶ ማሰልጠን የሚፈልግ ትልልቅ አሰልጣኝ ግን ብዙም አላየንም፡፡
ሁላችንም ልባችን እያወቀ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት አሰልጣኞች በእውነት መቀየር መቻል አለባቸው፡፡ የተሻለ ትምህርት መውሰድ አለባቸው ማንበብ አለባቸው ዓለም የደረሰበት የአሰለጣጠን ደረጃ ላይ መድረስ አለባቸው እና ይሄን ሳያደርጉ ግን በኢትዮጵያዊነት ብቻ ኢትዮጵያዊ አይሆንም ወይ ማለት ለእኔ ትክክል አይደለም፡፡
የምንፈልገውን ነገር ያስፈፀሙልናል ወይ አያስፈፅሙልንም ካላስፈፀም እንዴት አድርገን ነው በሙከራ (try and error) እድሜ ልካችንን አንደሄድም፡፡ የውጭ አሰልጣኙም የምንሞክረው ለዚህ ነው፡፡
የውጭ አሰልጣኙም ልክ ነው ብዙዎቹ እየመጡ ይሄዳሉ የጠበቅነውን ያህል ለውጥ የለም ነገር ግን ቢያንስ በነሚቾ ግዜ ያየነው የእግር ኳስ ለውጥ ትልቅ ነው ከዛም በነ ማርትኖይ እና በሌሎችም የተወሰኑ ለውጦችን አይተናል ስለዚህ ቀስ በቀስ ያሰብነው ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡
እናም ለተጨዋቾች ከፍተኛ ወጪ እያወጣን አፍሪካ ውስጥ ካሉ ታላላቅ ክለቦች ለመፎካከር እያቀድን በተሻለ አስልጣኝ ለመስራት ማሰባችንና መድከማችን ምንም ስህተት የለውም ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ሊጋችንም ከፌዴሬሽን ወጥቶ በሼር ካምፓኒ መመራት ከጀመረ በኋላ ውድድሮቹ በዲኤስ ቲቪ የመታየት እድልም ሊያገኙ ስለሆነ በዚህ ውድድር ተጨዋቾችና አስለጣኞች ከሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ተመጣጥነው ካልታዩ የተገኘው አድል ይመክናል፡፡ አሁን ላይ በርትተን መስራት አለብን አሰልጣኞቻችንም በርትተው መስራት አለባቸው ለውጥ ካለና ብቁ ከሆኑ እኛም በደስታ እንቀበላለን፡፡
ጥያቄ፦ ዋና አሰልጣኙ ኧርነስት ሚድንድሮፕ አሁን ስራቸውን ለቀዋል ቡድኑ በቀጣይ በማን እየሰለጠነ ነው የሚቀጥለው ?
አቶ አብነት፦ ለጊዜው ምክትል አስልጣኙ ማሂር ዴቪድስ አለ እሱ እየሰራ ነው፡፡ ሌሎች አስልጣኞች ከትናንትናው እለት ጀምሮ ከመላው ዓለም ሲቪያቸውን እየላኩ ነው።
እዚህ አጠገቤ እንኳን ባሳይህ ከስድስት የሚበልጡ ሲቪዎች አሉ። ግን ችግሩ እነሱ የሚፈልጉን ሳይሆን እኛ የምንፈልጋቸው ትልልቅ ሲቪ ያላቸው አሰልጣኞች መምጣት ይፈልጋሉ ወይ? አይፈልጉም፡፡
አጥር የሌለውና የማይከበር ሜዳ ውስጥ እየተጫወትን ጩቤና ድንጋይ ሜዳ ይዞ እየተገባ እንደዚህ አይነት ህግ የማይከበርበት ሊግ ውስጥ ጥልቅ ሲቪ ያለው አሰልጣኝ ይመጣል ብለህ ታስባለህ? እንኳን አሰልጣኝ ተጨዋችም አማራጭ ካላጣ አይመጣም፡፡
እዚህ ያለው ተጨዋችና አሰልጣኝ እንኳን እየተሰደበ እየተረገመ የሚያጸይፍ ስድብ እየተሰደበ አይደል እንዴ የሚሰራው፤ እዚህ ላይ በሰፊው ካልተሰራ ምኞታችንና አቅዳችንን ለማሳካት ከባድ ነው፡፡ መጀመሪያ አጥር ያለውና ህግ የሚከበርበት ስቴዲየም ውስጥ እንጫወት፤ ዳኝነት ፍትሀዊ ይሁን፤ ቆራጥ የሆነ ውሳኔ አሰጣጥና አስተዳደር ይኑረን ዝም ብሎ በግሩፕመመራረጥ አይደለም። እግር ኳሱን በሚያውቁ ሰዎች መመራት ይጀመር፤ የዛን ግዜ እግር ኳሱም ያድጋል ክለቦችም ብሄራዊ ቡድኑም ያሰብነው ቦታ ይደርሳሉ፡፡
አቶ አብነት ገብረመስቀል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት ጋር የነበረንን ቆይታ በዚሁ ፔጅ በክፍል ሁለት ፖስት ላይ ይዘን እንቀርባለን በተጨማሪም ሙሉ ቃለምልልሱን ከራሳቸው አንደበት በተወዳጁ ብስራት ኤፍኤም 101.1 ላይ በኢትዮ ማእድ ፕሮግራም በዛሬው እለት የምናቀርብ ስለሆነ ከምሽት 12.40 እስከ ሁለት ሰአት ባለው ፕሮግራማችን ይጠብቁን