የላሊጋውን ጨዋታ ያስጀመረው ሰለሞን ባረጋ!

ከትላንትና በስቲያ በስፔን ሲቪያ በተካሄደው ” Zurich maratón de Sevilla” እየተባለ በሚጠራው አመታዊ የማራቶን ውድድር ላይ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ባለድል መሆኑ ይታወቃል። ሰለሞን ማራቶንን ሲሮጥ ለመጀመሪያው ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያ የማራቶንን ውድድሩን በድል ብቻ ሳይሆን ጥሩ ሰአት በማስመዝገብም ጭምር ነው። ሰለሞን ማራቶኑን የጨረሰበት ሰአት 2:05:15 ሲሆን እስከ 37ተኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ግን በ2:03:30 ውድድሩን እንደሚጨርስ ተተንብዮ ነበር፤ ሆኖም የነበረበትን ፍጥነት ማስቀጠል ባለመቻሉ 2:05:15 በሆነ ሰአት ውድድሩን አጠናቋል። ሰለሞን የመጀመሪያውን ግማሽ ማራቶን የሮጠበት የ61:44 ሰአት ማራቶኑን ከ2:03 በታች ለመግባትም እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር። በታሪክ ይህንን ማድረግ የቻሉት 12 አትሌቶች ብቻ ሲሆኑ ሰለሞን ያንን የታሪክ ሰሪዎች ቡድን በመጀመሪያ ማራቶኑ የመቀላቀል እድል ነበረው፤ ነገር ግን ሁለተኛውን ግማሽ ማራቶን ለመጨረስ የፈጀበት 63:31 ሰአት ያ እንዳይሆን አድርጎታል።
ሰለሞን ባረጋ ከውድድሩ በኋላ ከፎቶግራፈር አማን ጋር ባደረገው ቆይታ ” በመጀመሪያው የማራቶን ውድድሬ ብዙ ተምሬያለሁ፤ እና በቀጣይ የተሻለ ውጤትን ለማምጣት አልማለሁ። የሲቪያ ማራቶን አዘጋጆች ላደረጉልኝ ጥሩ አቀባበል ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ” ብሏል። አትሌቱ ከውድድሩ በኋላ በስፍራው ለሚገኙ ሚዲያዎች በሰጠው ሌላ አስተያየትም ” በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሬ ሰዎች ብዙ ከኔ ጠብቀው እንደነበር ይገባኛል፤ ግን እኔ በግሌ ባሳየሁት ነገር ደስተኛ ነኝ። ሲቪያ ፈጣን ሩጫ ለማድረግ ተስማሚ ከተማ ነች። ዛሬ ደግሞ በተለይ የማራቶንን ፈታኙን ደረጃ አውቄዋለሁ፤ 35 ኪሜ ላይ ስደርስ እጅግ ደክሜ ነበር። የሆነው ሆኖ የበለጠ ልምድ ወስጄ እመለሳለሁ” ሲል ተናግሯል።

በሲቪያ ማራቶን አጠቃላይ 14,000 የሚሆኑ ሯጮች የተሳተፉ ሲሆን ውድድሩ በቅርቡ በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች መሀል ተካቷል። ሰለሞን ከድሉ በኋላ በሲቪያ በተለያዩ አካላት ግብዣ የተደረገለት ሲሆን ትላንት ምሸት ደግሞ እውቁ የከተማው የላሊጋ ቡድን ሲቪያ እግር ኳስ ክለብ ራሞስ ሳንቼዝ ፒዥዋን በተሰኘው ስታድማቸው ግብዣ አድርገውለታል። ከክለቡ የተለያዩ ሰዎች ጋርም የመገናኘት እድልን ያገኘ ሲሆን ከነዚህ መካከል የቀድሞው የክለቡ ኮከብ ሄሱስ ናቫስ ይጠቀሳል።

ሰለሞን የእግር ኳስ ወዳጅ መሆኑንና ለሮናልዶ ደግሞ የተለየ አድናቆት እንዳለው በሚሰጣቸው ቃለ-ምልልሶች ላይ ሲናገር ተደምጧል። በትርፍ ጊዜውም ኳስ የመጫወት ልማድ እንዳለው ይነገራል። ሰለሞን ባረጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋቂ ወንዶች ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው በ2022 በአለም አቀፉ አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር ነበር። በቶክዮ ኦሎምፒክም በ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ሲቪያ ከ ሪያል ማዮርካ ያደረጉትን ጨዋታም በሜዳ ላይ ተገኝቶ በማስጀመር በስታድየሙ ለሚገኙት ሰዎች ሰላምታ እየሰጠ በሜዳው ላይ ሲሮጥ ተስተውሏል።

በሌላ በኩል በሴቶቹ ዘርፍ የሲቪያ ማራቶን ውድድርም የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎን ያደረገችው አንቺንአሉ ደሴ 2:22:17 በመግባት ውድድሩን አሸንፋለች።

አሁን አሁን በመካከለኛ እና ረጅም የትራክ ላይ ርቀቶች የምናውቃቸው አትሌቶች የጎዳና ላይ ሩጫን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል በቅርብ ጊዜ እንኳን በባርሴሎና የግማሽ ማራቶን ሪኮርድን ያሻሻለውን ኡጋንዳዊውን ጃኮብ ኪፕሊሞ መጥቀስ እንችላለን። በአትሌቲክሱ የሰለሞን የቅርብ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት የ10,000 ሜትር የአለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊም በቀጣይ ወር በፖርቹጋል ሊዝበን የመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን የሚያደርግ ይሆናል።
