ሁለቱ ዘመን አይሽሬ ክዋክብት በለንደን ማራቶን!

የለንደን ማራቶን ሙሉ አሰላለፍ ይፋ ሲሆን የዘመናችን ክዋክብቶች በሁለቱም ፆታ ተሰባስበዋል።

በአለም ላይ ከሚደረጉ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው በእንግሊዝ ለንደን የሚደረገው የለንደን ማራቶን ዘንድሮም እንደሁልጊዜው የቀረው የማራቶን ኮከብ ያለ አይመስልም። በወንዶቹ ዘርፍ ትላንት አመሻሹን የአለም ሶስተኛ የማራቶን ፈጣን ሰአት ባለቤቱ ቀነኒሳ በቀለ እንደሚሳተፍ ይፋ የሆነ ሲሆን ከትላንት ቀደም ብሎ በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድሮች መንገስ የቻለው እና ሁለተኛ ፈጣን ሰአት ያለው ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ፣ የፓሪስ ኦሎምፒክ አሸናፊው ታምራት ቶላ እንዲሁም የአምና የውድድሩ አሸናፊው አሌክስ አንደር ሙቲሶ ሙንያዎን ጨምሮ በርካታ ሌሎች ክዋክብቶች እንደሚሮጡ ይፋ ተደርጓል። በመካከለኛ እና ረጅም ርቀቶች ጥሩ ስኬቶች ያስመዘገበውና ከትላንት በስቲያ የግማሽ ማራቶንን ሪኮርድ የሰበረው ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞም የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን የሚያደርገው በዚሁ በለንደን ማራቶን ነው።

ባሳለፍነው አመት በተደረገው የለንደን ማራቶን ከ19 አመቱ አሌክስ አንደር ሙቲሶ ሙንያዎ በመከተል 2:04:15 የገባው ቀነኒሳ በቀለ ከ40 አመት በላይ በዚህን ያህል ፈጣን ሰአት ማራቶንን የጨረሰ ባለመኖሩ የማስተርስ ሪኮርድን የግሉ ማድረጉ ይታወሳል። ከ12 አመታት ቆይታ በኋላም ወደኦሎምፒክ ተመልሶ በፓሪስ ማራቶን ላይ እንደተመለከትነውም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።ለ20 አመታት በዘለቀ የሩጫ ህይወቱ ቀነኒሳ 17 ጊዜ አለም አቀፍ የትራክ ውድድሮች ባለድል መሆን የቻለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 3 የኦሎምፒክ እና 2 የአለም ሻምፒዮና ወርቆቹ ይጠቀሳሉ። ቀነኒሳ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ይፋ ከሆነ በኋላም ” የለንደን ማራቶን በአለማችን ላይ ያሉ የማራቶን ክዋክብትን የሚያሰባስብ የተለየ ውድድር ነው፤ እና የዚህ አካል መሆኔ ያስደስተኛል። ከኤሉድ ጋር በድጋሚ መሮጣችንም ልዩ ያደርገዋል። ለ22 አመታት የማይረሱ ጊዜያትን አሳልፈናል፤ ያንን በመጪው የለንደን ማራቶን እንደምናስቀጥለው እምነት አለኝ” ሲል ተናግሯል።

በሴቶቹ ደግሞ በማራቶን ሁለተኛ ፈጣን ሰአት ያላት እና የፓሪስ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ትግስት አሰፋ፣ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ ሲፋን ሀሰን፣ የአምና የውድድሩ አሸናፊ ፔሬስ ጄፕቸርችር እንዲሁም ሌሎች የወቅቱ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉ ይሆናል።

ትግስት አሰፋ እና ሲፋን ሀሰን በፓሪስ ኦሎምፒክ ያሳዩትን ተፎካካሪነት በለንደንም እንደሚደግሙት ይጠበቃል። ኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቸርችርም የአምና አሸናፊነቷን ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር እንደምታደርግ ከወዲሁ ቅድመ-ግምት ተሰጥቷል።

የለንደን ማራቶን እ.ኤ.አ  በወርሀ ሚያዚያ 27,2025 በእለተ እሁድ ይደረጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.