ጃኮብ ኪፕሊሞ ሪኮርድ ሲሰብር ዮሚፍ እና መዲናም ባለድል ሆነዋል!
ዛሬ እሁድ ጥር 9,2017 አ.ም የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ተደርገዋል። በባርሴሎና በተደረገ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ተቋም ‘ ጎልድ ሌብል’ የግማሽ ማራቶን ውድድር በትራክ ውድድሮች የሚታወቀው ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ 56:42 በመግባት በዮሚፍ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ሪኮርድ በ48 ሴኮንድ ማሻሻል ችሏል።

በባርሴሎና የነበረው የአየር ንብረት ለሩጫ ተስማሚ የነበረ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የነበረው የሙቀት መጠንም 13 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ንፋስ አለመኖሩ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። ኪፕሊሞ ከ57 ሴኮንድ በታች ግማሽ ማራቶንን በመሮጥ ቀዳሚው ግለሰብ መሆን ሲችል 15 ኪሎሜትሩን የሮጠበት የ40:07 ጊዜም በግማሽ ማራቶን ታሪክ ፈጣኑ ሆኗል። አትሌቱ ሪኮርዱን ለመስበርም በሰአት 22.3 ኪሜ ፍጥነት እንደነበረው ተገልጿል።

ኪፕሊሞ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ” የተሳካ ውድድር ነበር። ሁሉም ነገር ከጠበኩት በላይ ጥሩ ሆኗል። በለንደን እስከምሮጠው የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሬ ድረስ ምንም አይነት ሩጫ አላደርግም” ሲል ገልጿል። ኪፕሊሞ አሁን ካሳየው አቋም አንፃር በመጪው የለንደን ማራቶን የርቀቱን ሪኮርድ በማሻሻል አዲስ ታሪክ ሊፅፍ እንደሚችል ከወዲሁ እምነት ተጥሎበታል። በተመሳሳይ ርቀት በሴቶቹ ደግሞ ኬንያዊቷ የቀድሞ ባለሪኮርድ ጆይክላይን ጄፕኮስጊ 1:04:13 በመግባት አሸንፋለች፤ አትሌቷ የገባችበት ርቀትም 7ተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዮሚፍ ቀጀልቻ እና መዲና ባለድል የሆኑበት የ10 ኪሜ ሩጫ

በስፔን ካስቴሎን በተካሄደ የ10 ኪሜ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ‘ ጎልድ ሌብል’ ሩጫ ዮሚፍ እና መዲና አሸናፊ ሆነዋል። በወንዶቹ በ8 ቀናት ልዩነት ሁለት ሪኮርዶቹ የተሰበሩበት ዮሚፍ ዮሚፍ ቀጀልቻ ካለበት ጥሩ አቋም አንፃር 26:30 የሆነውን የርቀቱን ሪኮርድ ያሻሽላለል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም አትሌቱ ግን ከሪኮርድ 6 ሴኮንዶች ዘግይቶ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቋል። ይህም የርቀቱ ሁለተኛ ፈጣን ሰአት ባለቤት አድርጎታል። ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ዮሚፍ ” ሪኮርዱን እንደምሰብረው ተማምኜ ነበር” ሲል በውጤቱ እንዳዘነ ገልጿል።

በሴቶቹ ደግሞ የአለም ከ20 በታች የ5 ኪሜ ባለሪኮርዷ ኢትዮጵያዊቷ መዲና ኢሳ በመጀመሪያ የውድድሩ ሩጫዋ 29:24 በመግባት እና የርቀቱን 4ተኛ ፈጣን ሰአት በማስመዝገብ በአንደኝነት ጨርሳለች።
