የአመቱ ምርጥ አትሌት የመጨረሻ እጩዎች ተለይተው ታውቀዋል!
የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ተቋም( World Athletics) በየዘርፉ ሁለት ሁለት የመጨረሻ የአመቱ ምርጥ አትሌት እጩዎችን ይፋ አድርጓል።
ሁለት ሁለት እጩዎች የተመረጡትም ከአለም አቀፉ አትሌቲክስ ካውንስል፣ ከአለም አቀፉ አትሌቲክስ ቤተሰብ እና በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰጡ ድምፆች መሆኑ ታውቋል።
የአመቱን ምርጥ አትሌት ለመለየትም በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከህዳር 4-10 የድምፅ መስጠት ሂደቱ ይከናወናል።
ኢትዮጵያ ከነዚህ የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ ያካተተችው አንድ አትሌቷን ብቻ ነው። እርሱም በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ የውድድሩን ሪኮርድ ጭምር በማሻሻል ያሸነፈው ታምራት ቶላ ነው። ታምራት ቶላ የወንዶች ከስታድየም ውጭ የተደረጉ ውድድሮች ምርጥ አትሌት በሚለው ከኦሎምፒክ የ20 ኪ.ሜ የእርምጃ ውድድር አሸናፊው ብሪያን ፒንታዶ ጋር የመጨረሻ እጩ ሆኖ መቅረብ ችሏል። ታምራት ባሳለፍነው እሁድ በተደረገው የኒውዮርክ ማራቶን ቢሳተፍም ድል እንዳልቀናው ይታወሳል።
በሌላ በኩል የወንዶች የአመቱ ምርጥ የትራክ አትሌት የሚለውን ለመለየት አዳጋች ይመስላል፤ ምክንያቱም የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት በአመቱ እጅግ ድንቅ አቋም ሲያሳዩ የነበሩት ጃኮብ ኢንግብሪግስተን እና ሌትስሌ ቶቤጎ የመጨረሻ እጩ ሆነው በመቅረባቸው ነው። ጃኮብ ኢንግብሪግስተን የ5000 ሜትር የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንደነበር ይታወሳል። ሌትስሌ ቶቤጎ በበኩሉ ለሀገሩ ቦትስዋና የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ የጃማይካ እና የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ነው ተብሎ በሚጠበቀው የ200 ሜትር ርቀት እንዳመጣ ይታወሳል።
በሴቶች ከስታድየም ውጭ የተደረጉ ውድድሮች እጩ አትሌቶች ደግሞ የአለም የማራቶንን ሪኮርድ ያሻሻለችው ኬንያዊቷ ሩት እና ትውለደ ኢትዮጵያዊቷ ለኔዘርላንድ ምትሮጠው የኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ሲፋን ሀሰን ሆነው ቀርበዋል።
በአጠቃላይ ምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪው ዱፕላቲንስን ጨምሮ ሌሎች የአመቱ ምርጥ አትሌቶች በየዘርፋቸው የመጨረሻ ሁለት እጩዎች ውስጥ መካተት ችለዋል።
በ 6 ዘርፎችም 12 አትሌቶች ለአሸናፊነት በመጨረሻ እጩዎች ውስጥ ተካተዋል።
የየየዘርፉ አሸናፊዎችም እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከህዳር 14 በኋላ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።