1000 ጨዋታዎች የደረሰው የእግር ኳስ ቀማሚ!

እግር ኳስ ቲያትር ከተባለ ከውብ ተውኔቶች ድርሰት ጀርባ ፔፕ ጋርድዮላን አለማንሳት አይቻልም። የዘመናዊ እግር ኳስ ምርጥ አሰልጣኞች ተርታ የሚሰለፈው በስፔን በጀርመን እና በእንግሊዝ ደጋግሞ የሚያሸንፍ ቡድን መገንባት የቻለው ፔፕ ጋርድዮላ እነሆ ዛሬ 1000ኛ ጨዋታውን ይመራል።

ጋርድዮላ እስካሁን ከመራቸው 999 ጨዋታዎች 715 የሚሆኑትን በድል መወጣት የቻለ ሲሆን አሸናፊ ቡድኖችን መገንባት ከመቻሉ በተጨማሪ የሚያዝናና ጥጡረ የጨዋታ ፍሰት ያለው እግር ኳስን ለአመታት ሲያስመለክተን ቆይቷል።

” በአሰልጣኝነት 1000 ጨዋታዎች ላይ መድረስ ለኔ ልዩ አጋጣሚ ነው” የሚለው ጋርድዮላ ” ከአመታት በፊት በባርሴሎና ቢ ቡድን ማሰልጠን ስጀምር 1000 ጨዋታዎች ላይ ስለመደረስ አስቤ አላውቅም። ፍላጎቴ ጥሩ ስራ መስራት፣ እግር ኳስን በትክክለኛው መንገድ መጫወት እና ሚፈጠረውን ማየት ነበር። በሶስት አስደናቂ ክለቦች ውስጥ በመስራቴ እድለኛ ነኝ” ሲልም ይህ አጋጣሚ ለሱ ምን ማለት እንደሆነ ያስረዳል።

ጋርድዮላ 40 ትላልቅ ዋንጫዎች ማሳካት የቻለ ሲሆን ይህም ከአማካይ በ25 ጨዋታዎች 1 ዋንጫ ያገኛል እንደማለት ነው። ከአሁኑ ክለቡ ከማንቺስተር ሲቲ ጋርም በ549 ጨዋታዎች 18 ዋንጫዎችን አሳክቷል። ፔፕ ከክለቡ ጋር 6 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን ማሳካት መቻሉም አይዘነጋም። የመጀመሪያው የሊግ ዋንጫ ስኬቱ ማንቺስተር ሲቲ 100 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻለበት ሲሆን ይህም እንደሪኮርድ ተቀምጧል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ ሱፐር ካፕ እና ፊፋ አለም ክለቦች ዋንጫን በማሳካት የማንቺስተር ሲቲን አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ስኬት ከፍ አድርጓል። በተለይም ደግሞ የክለቡ ደጋፊዎች ለአመታት ሲጠይቁት የነበረውን የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማሳካት መቻሉ ታሪክ ከማይረሳቸው የክለቡ አሰልጣኞች መሀል በቀዳሚነት እንዲጠቀስ ያስችለዋል።

ጋርድዮላ ” ስማቸው ተጠርቶ በግል መመስገን ያለባቸው ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ባለፉት 18 አመታት አብረውኝ የሰሩትን ሰዎች ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ። በመንገዴ ሁሉ ለሚያበረታቱኝ ቤተሰቦችም እንዲሁ ምስጋናዬ ይድረስ” ሲልም ምስጋናውን አድርሷል። ማንቺስተር ሲቲ ከ ሊቨርፑል ምሽት 1:30 ሲል የሚገናኙ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.