በበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያኑ ደመቁ!

በታሪካዊው እና 50ኛ አመቱን እያከበረ ባለው የበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ፆታ ድል አድርገዋል።

በወንዶች ሚልኬሳ መንገሻ 2:03:17 በመግባት ውድድሩን ሲያሸንፍ ሀይማኖት አለው ደግሞ 2:03:31 በመግባት በሶስተኝነት ውድድሩን ጨርሷል። ሚልኬሳ ካሸነፈ በኋላ ስሜታዊ ሆኖ ሲያለቅስ ተስተውሏል።

በሴቶች ደግሞ በመካከለኛ ርቀት የምትታወቀው ገንዘቤ ዲባባ ወደውድድር በመመለሷ ትኩረትን ስቦ የነበረ ሲሆም አትሌቷ ግን ውድድሩን መጨረስ ሳትችል ቀርታለች፤ ሆኖም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ትግስት ከተማ 2:16:14 በመግባት ስታሸንፍ መስታወት ፍቅር እና ቦሰና ሙላቴ በ2:18:48 እና በ2:19:00 ተከታትለው ገብተዋል።

የውድድሩ አሸናፊዎች እያንዳንዳቸው 22,600 ዶላር የሚሸለሙ ሲሆን ሁለተኛ የወጡት 11,300 ዶላር እንዲሁም ዶላር ሶስተኛ የወጡት 8475 ዶላር እያለ ይቀጥላል። ሚልኬሳ መንገሻ ፣ ትግስት ከተማ እና መስታወት ፍቅር ተጨማሪ ሽልማቶች አላቸው። አዘጋጆቹ ባስቀመጡት መሰረት ለወንዶች ከ2:03:30 በታች ለገባ 33,900 ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ የሚበረክትለት ሲሆን በሴቶቹ ደግሞ 2:17:30 በታች ለገባ ተጨማሪ 33,900 ዶላር እንዲሁም ከ2:03:30 በታች ለገባ ተጨማሪ 16,950 ዶላር የሚበረከትለት ይሆናል፤ በዚህም መሰረት ሶስቱ አትሌቶች ባላቸው ሰአት ምክንያት ተጨማሪ ገንዘብ እንዳስመዘገቡት ውጤት የሚያገኙ ይሆናል።

ሚልኬሳ መንገሻ በበኩሉ በሽልማት ብቻ 56,500 ዶላር የግሉ አድርጓል። ትግስት ከተማም በተመሳሳይ 56,500 ዶላር ማግኘት ችላለች።

የበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትግሰት አሰፋ የሴቶች የማራቶን የአለም ክብረ ወሰንን የሰበረችበት እንደሆነ ይታወቃል። አትሌቷም በእንግድነት በበርሊን ተገኝታ ውድድሩን ተከታትላለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published.