ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ቅርስን ተረከበ
ዛሬ በአዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በተገኙበት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ‹ውድድር› ዘርፍ፣ የዓለም አትሌቲክስ ቅርስን (Heritage Plaque) ተቀብሏል፡፡
ይህ የዓለም አትሌቲክስ ቅርስ (Heritage Plaque) ፣ ተሸላሚዎቹ በሚገኙበት ስፍራ ‹‹ለመም (ትራክ) እና ሜዳ አትሌቲክስ እንዲሁም እንደ ሀገር አቋራጭ፣ ተራራ፣ ጎዳና፣ ጫካ፣ እና ለመሳሰሉት ከስታዲየም ውጪ የሚከናወኑ የአትሌቲክስ ዘርፎች ዓለም አቀፍ ታሪክ እና እድገት የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ›› የሚሰጥ ክብር ነው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚደንት ሎርድ ሴባስቲያን ኮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቀዳሚውን የኢትዮጵያ የሩጫ ሁነት ‹‹ከአፍሪካ ታላቅ ስኬታማ የስፖርት ታሪኮች አንዱ›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡
ሴባስቲያን ኮ ቀጥለውም ‹‹ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ቅርስ (Heritage Plaque) በትክክል ይገባዋል፡፡ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እንኳን ደስ ያላችሁ›› ብለዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አትሌቲክስ በተለይም ሩጫ በኢትዮጵያ ያለውን ትልቅ ቦታ ጠቅሰው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቲክስም ሆነ ለከተማዋ ላደረገውን አስተዋፅኦ አመስግነዋል። ‹‹ይህን ውድድር በደመቀ ሁኔታ ሲያካሂዱ የቆዩትን ኃይሌ ገብረስላሴ እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ማመስገን እወዳለሁ›› ያሉት ክብርት አዳነች ሲቀጥሉም ‹‹እንደ ውድድሩን የምታዘጋጅ ከተማ ይህን ክብር ከዓለም አትሌቲክስ በማግኘታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፡፡ ውድድሩን ከዚህም በበለጠ ለማሳደግ እና ብዙ የውጪ ሀገር ተሳታፊዎችን ወደከተማችን እንዲያመጣ ተባብረን እንድንሰራ እውቅናው የበለጠ ያበረታናል›› ብለዋል፡፡
የውድድሩ መስራች አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ ‹‹ይህ ሽልማት ለውድድራችን እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ለስራችን ዕውቅና ለሰጠን የዓለም አትሌቲክስ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሽልማት በብሔራዊ ሙዚየም ቦታ አግኝቶ የሚታይ መሆኑም ለኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የተለየ ያደርገዋል›› ብሏል፡፡
የአለም አትሌቲክስ ከዚህ ቀደም ለጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ክብር ያዘጋጀው ተመሳሳይ ቅርስ (Heritage Plaque) በተቋሙ ኃላፊ አማካኝነት ዛሬ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተረክቧል።

በዛሬው የክብር ስነ ስርዓት ላይ የዓለም አትሌቲክስ Heritage Plaque የተሰጠው በዓለም አትሌቲክስ የቅርስ (Heritage Plaque) ዳይሬክተር ክሪስ ተርነር ሲሆን፣ ከንቲባ አዳነች እና ኃይሌ ገብረሥላሴ በተገኙበት በብሔራዊ ሙዝየም ተቀምጧል።
Via Great Ethiopian Run
✍️ ዮናታን አየለ
