ታምራት ቶላ- ማራቶንን ወደቤቱ የመለሰ ጀግና
አበበ ቢቂላ ማራቶንን አንዴ ሳይሆን ሁለቴ በማሸነፍ በርቀቱ ያለውን የበላይነት ለአለም አስመሰከረ፤ የአበበን የድል ዱላ ማሞ ተቀበለ፤ የ1968ቱ ኦሎምፒክም ኢትዮጵያን የማራቶን ድል ያላባሰ ሆኖ አለፈ።
ከ1968 በኋላ ለአመታት በአበበ ምክንያት የኢትዮጵያ የተሰኘው ማራቶን ከቤቱ ርቆ ቆየ፤ በ2000 ከወደ ሲድኒ ግን ያልተጠበቀው አትሌት ገዛሀኝ አበራ ማራቶኑን ወደቤቱ መለሰ። በመላው ኢትዮጵያም ታላቅ ደስታ ሆነ። የኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ በገጠራማ አካባቢዎች እንደመኖሩና ለመኖር ሲል በፅናት ብዙ ነገሮችን እንደማለፉ ከማራቶን ጋር ልዩ ቁርኝት እንዲኖረው ያደረገ ይመስላል፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ማራቶንን የኛ በሚል ስሜት ይከታተላል።
ከገዛሀኝ አበራ በኋላ ወርቁ ጠፍቶ ሁለት አስርት አመታት ተቆጠሩ፤ ይባስ ብሎ በቶክዮ ኦሎምፒክ ሶስቱም አትሌቶቻችን አቋረጡ። የቶክዮ ኦሎምፒክ ከተደረገ በኋላ በአመቱ ታምራት ቶላ በማራቶን በደማቁ የተዋወቀበትን ድል በኦሬጎን አለም ሻምፒዮና ሪኮርድ በመስበር ጭምር አስመዘገበ፤ ታምራት በሪዮ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ነሀስ ያገኘ አትሌት ቢሆንም ስሙ የገነነው ከኦሬጎኑ የአለም ሻምፒዮና በኋላ ነው።
ይሀው አሁን ወደፓሪሱ ኦሎምፒክ ስንመጣ አትሌቱ ዘንድሮ በተወዳደረባቸው ውድድሮች ያለው ሰአት ከሌሎች አትሌቶች ጋር ሲነፃፀር በ4ተኛ ደረጃ የሚያስቀምጠው በመሆኑ በተጠባባቂነት ተያዘ። ከ1-3 ፈጣን ሰአት ያላቸው ቀነኒሳ፣ ሲሳይ እና ዴሬሳም ኢትዮጵያን በማራቶን የሚወክሉ አትሌቶች ሆነው ተመረጡ።
ከ2 ሳምንታት በፊት ግን አንደኛው ተመራጭ ሲሳይ ለማ እንደተጎዳ እና በሱ ቦታ ታምራት እንዲወዳደር የሚገልፅ ማመልከቻ አስገባ። የማራቶን የወንዶቹም የሴቶችም አብዛኛው የቡድኑ አባላት ምንም እንኳን በአንድ አሰልጣኝ ባይሆንም አንድ ላይ መሰልጠናቸው ከሌላው ርቀት ይልቅ አትሌቶቹ እርስበእርስ የመተዋወቅ እና የመተጋገዝ ስሜት እንዲኖራቸው ያደረገ ይመስላል፤ ለዛም ነው ሲሳይ ጉዳቱን ደብቆ ኦሎምፒክ ላይ በመሳተፉ ብቻ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ ሲጋበዝ በተሳትፎ ብቻ የሚያገኘውን ገንዘብ ከፍ ከማድረግ ይልቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ፤ ሀገር ሙሉበሙሉ ጤናማ በሆነ አትሌት ብትወከል ይሻላል ብሎ ማመልከቻ ያስገባው።
በውድድሩ ላይ የኪኘችጌ እና የቀነኒሳ መሳተፍ ትኩረትን ስቦ ስለነበር ስለሌሎቹ አትሌቶች ያን ያህል አልተነገረም፤ ውድድሩ በጀግናው አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ አማካኝነት ተጀመረ።ሩጫውም ተከናወነ፤ አስደናቂ አሯሯጥ ያሳየን እና ነገ 33 አመት የሚሞላው ታምራትም ብዙም ሳይባልለት በ32ተኛ አመቱ የመጨረሻ ቀን ምርጡን ስኬት አስመዘገበ። 2:06:26 በመግባትም የኦሎምፒክ ሪኮርድን በ6 ሴኮንዶች ማሻሻል ቻለ። ይህ ሲሆንም ከ16 አመት በኋላ ነው፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ በወንዶች ማራቶን ይህ ድል ሲገኝ ከ24 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ታምራት ቶላም ስሙን ከአበበ፣ ማሞ ወልዴ እና ገዛሀኝ አበራ ተርታ ማሳለፍ ቻለ። የታምራት ድል ብዙ ሊባልለት የሚችል ድል ነው፤ በተለይም ብዙዎች ስለፓሪሱ የማራቶን መሮጫ አስቸጋሪ መልክአ-ምድር ሲያወሩ የነበረ ሲሆን ታምራት ግን በሚገባ ተቆጣጥሮታል።
አንድ የ ‘x’ ተጠቃሚ 70% የሚሆኑት የአፍሪካ ተራሮች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፤ 16% የሚሆነው የፓሪስ ማራቶን መሮጫ ቦታም አቀበታማ ነበር ይሄም ኢትዮጵያዊው ተፋላሚን የወርቅ ሜዳሊያ እንዲያገኝ ረድቶታል ሲል አሰፈሯል፤ ታምራት ከዚህ አስቸጋሪ የመሮጫ ስፍራ ጋር በፅናት ታግሎ ለኢትዮጵያ የድል ብስራት ሆነላት።
የመጨረሻው ኦሎምፒክ እንደመሆኑ እና አንጋፋም ስለሆነ ከውድድሩ በፊት ብዙ የተባለለት ቀነኒሳ 39ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የሚከተለውን ተናገረ
” ኢትዮጵያ ውድድሩን ማሸነፏ ድንቅ ነው፤ ታምራት ጠንካራ አትሌት ነው፤ እናም ለእሱ ደስ ብሎኛል፤ ሰዎች ስለእኔ እና ኪኘቾጌ ብዙ ሲሉ ነበር፤ ግን ዛሬ የወጣቱ ትውልድ ሩጫ ህኖ አልፏል፤ እነሱ ከኛ የተሻሉ ናቸው፤ ከነሱ ጋር መሮጥ ከባድ ነበር።”
ሌላኛው አንጋፋ አትሌት እና ያለፉት ሁለት ኦሎምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ኤሉድ ኪኘቾጌ 31 ኪ.ሜ ላይ ለማቋረጥ ተገደደ፤ ” ከሮጥኳቸው ሩጫዎች ሁሉ መጥፎው” ሲልም ገለፀው።
የታምራት አሰልጣኝ ገመዶ ዴዴፎ ከውድድሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት በድሉ እንደተደሰቱ በመግለፅ ለድሉ የሲሳይ ለማ ታምራት ይሩጥ ማለት ወሳኝ እንደነበር ጠቁመዋል። ታምራት ከዘንድሮ ጀምሮ ባሉት የአትሌቲክስ ኦሎምፒክ ውድድሮች የገንዘብ ሽልማት መካተቱን ተከትሎ፤ የ50,000 ዶላር አሸናፊም መሆን ችሏል።ኢትዮጵያ በፓሪስ 2024 የናፈቃትን ወርቅም በኦሎምፒኩ መገባደጃ እነሆ በማለት ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር አስፈነደቊል።በቀጣይ በ1500 ሜትር ሴቶች፣ በ5000 ሜትር ወንዶች እና በሴቶች ማራቶን ቀሪ የፃፍሜ ወድድሮች ይከናወናሉ፤ ይህ ድልም ለቡድኑ ትልቅ መነሳሳት እንደሚሆን እምነት ተጥሎበታል።