የቦትስዋና አበበ ቢቂላ- ሌትስሌ ቶቤጎ

” የእናቴን ህልፈት እንደሰማሁ የአትሌትነት ዘመኔ ያበቃ መሰለኝ”-ሌትስሌ ቶቦጎ- አዲሱ የ200 ሜትር ሻምፒዮን

በትላንትናው እለት በተደረገ የ200 ሜትር የኦሎምፒክ የፍፃሜ ውድድር ቦትስዋናዊው ሌትስሊ ቶቦጎ በውድድሩ በብዙ የተጠበቀውን የ100 ሜትር ሻምፒዮኑን አሜሪካውዊውን ላይልስ በመቅደም ጭምር ለቦትስዋና ብሎም ለአህጉራችን አፍሪካ አዲስ ታሪክ ፅፏል። ላይልስ በውድድሩ ሶስተኛ ሆኖ እንደጨረሰ ይታወቃል።

ቶቤጎ 19 ሴከንድ ከ 49 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ነው ውድድሩን ያሸነፈው። አትሌቱ ከጥቂት ወራት በፊት አትሌቲክስ ለማቆም ያሰበበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ ያስታውሳል። ” የእናቴን ህልፈት ስሰማ የአትሌቲክስ ህይወቴ ያበቃ መሰለኝ፤ ስለአትሌቲክስ ከማሰብ የምርቀበትን መንገዶች ማሰብ ጀመርኩ” ይላል ቶቤጎ፤ እናቱ በግንቦት 19,2024 ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለዩት።

ይህ የ21 አመት አትሌት ሀዘኑን ከባድ ያደረገበት የ43 አመቷ እናቱ ሴራቲዋ ከማለፏ በፊት የነበራት የጤና ሁኔታ መሻሻል አሳይቶ ስለነበር እና ህልፈቷን የጠበቀው ባልመሆኑ ነው። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜም ቡድኑ ከሱ ጎን መቆሙንም ይናገራል። ” ቡድኑ በዙሪያዬ ነበር፤ አሰልጣኜ እና የቡድን ጓደኞቼ እያንዳንዷን ቀናት ለመመለስ የማደርገውን ጥረት ይከታተሉ ነበር” ሲል እንዴት እንዳገዙት ያስታውሳል።

የአለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ቶቤጎ እናቱ የጥንካሬው ምንጭ በመሆኗ የሷ ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ህልፈት አትሌቲክስን እንዲያቋርጥ ሊያደርገው የነበረ ቢሆንም ጠንክሮ ልምምድ በመስራት በጥቂት ወራት ልዩነት ውስጥ ይህን ጣፋጭ ድል ሊያስመዘግብ ችሏል።

ሀገረ ቦትስዋና በፕሬዝዳንቷ አማካኝነት አርብ ከሰዓት ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በይፋ አውጀዋል፤ ምክንያቱም አትሌቱ ለሀገሩ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያዋን የወርቅ ሜዳሊያ እንድታገኝ አድርጓልና። በአጭር አገላለፅ ቶቤጎ ማለት ለቦትስዋና ዜጎች ልክእንደ አበበ ቢቂላ ነው፤ አበበ ለኛ የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘልን አትሌት መሆኑ ይታወቃል። የቶቤጎ ድል የዓለማችን 5ኛው ፈጣኑ ሰው መሆን እንዳስቻለውም ተነግሯል።

አትሌቱ ቦትስዋና ውስጥ በፈለገው ቦታ ባለ 5 መኝታ ትልቅ መኖሪያ ቤት በሀገሪቱ መንግስት ወጭ እንዲሰራለትም ውሳኔ መተላለፉ ተሰምቷል።

የቦትስዋና የወጣቶች ሚንስትር ራክጋሬ በበኩላቸው ከተለያዩ አካላት ቃል የተገቡ ሌሎች የገንዘብ እና የአይነት ሽልማቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የሀገሪቱ መንግስት የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለመሸለም መወሰኑን አስታውቀዋል።

አሜሪካዊው ላይልስ በበኩሉ ኮቪድ-19 ይዞኝ ነው የሮጥኩት፤ ያ ደግሞ ብቃቴ ላይ ጫና አሳድሯል ሲል ተደምጧል።

ያም ሆነ ይህ ግን በረጅም ርቀት ለምትታወቀው አፍሪካ አዲስ የአጭር ርቀት የድል ጮራ ከወደ ቦትስዋና ፈንጥቆላታል። ሌትስሌ ቶቤጎንም ታሪክ ሲያስታውሰው ይኖራል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.