ዲያስፖራ ተጫዋቾችን በተመለከተ አዲስ ንድፈ-ሀሳብ ለፌዴሬሽኑ ቀረበ!

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን(ኢ.እ.ፌ)  በውጭ ሀገር የሚኖሩ የዘር ሀረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዝ ተጫዋቾችን ወደ ብሔራዊ ቡድን ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል አዲስ የረጅም ጊዜ ፕሮግራም እያዘጋጀ ነው፡፡ ይህንን የገለጹት የፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ ስካውቲንግ ኃላፊ አቶ ዴቪድ በሻህ ናቸው፡፡ ዴቪድ በሻህ ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ንድፈ-ሀሳብም በመጪዎቹ ሳምንታት ውይይት ይደረግበታል። አቶ ዴቪድ በሻህ ለገፃችን እንደገለፁት በቃል ደረጃ ፌዴሬሽኑ ይህን ንድፈ-ሀሳብ ለመቀበል እንደተዘጋጀ የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ።

የ”ኢ.እ.ፌ ዲያስፖራ ኢሊት እግር ኳስ ፕሮግራም” የተሰኘው ይህ ፕሮግራም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ ዘላቂ ቦታ እንዲኖረው ተደርጎ የተነደፈ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፕሮግራም “የኢ.እ. ፌ ዲያስፖራ U17 ኢሊት ካምፕ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከአውሮፓ የተውጣጡ ወደ 15 የሚጠጉ የተመረጡ ተጫዋቾችን በአራት ቀናት ውስጥ በይፋዊ የፌዴሬሽኑ አሰልጣኞች የሚመራ ካምፕ ያካትታል፡፡

ይህ ፕሮግራም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ለማጠናከር ሲጠቀሙበት የቆዩትን ስልት የተከተለ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ሀገራት በውጭ የሚገኙ ተጫዋቾቻቸውን ገና ከጅምሩ በመለየት  ከተጫዋቾቹና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር እንዲሁም ወደ ብሔራዊ ቡድናቸው ግልጽ የመግቢያ መንገድ በመዘርጋት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን አሳድገዋል፡፡ ፌዴሬሽኑም ይህንኑ አካሄድ በመከተል የራሱን ስልት ለመዘርጋት አቅዷል፡፡

በንድፈ-ሀሳቡ( ፕሮፖዛሉ) ላይ እንደተቀመጠው ከሆነ ካምፑ አምስት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት፡- በአውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዝርያ ያላቸውን ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾችን መለየት ፤ተጫዋቾቹን ከኢ.እ.ፌ እና ከብሔራዊ ቡድን ከባቢ ጋር ማስተዋወቅ፤ በፌዴሬሽኑ ስር ያሉ  አሰልጣኞች የእያንዳንዱን ተጫዋች ቴክኒካዊ ብቃት፣ ታክቲካዊ ግንዛቤ፣ አካላዊ ብቃት፣ ስብዕናና የወደፊት አቅም በቅርበት እንዲገመግሙ ማስቻል፤ በዲያስፖራ ተጫዋቾችና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድኑ እቅድ ማውጣት የሚያገለግል ዘላቂ የዲያስፖራ ተጫዋቾች የመረጃ ቋት መገንባት ናቸው፡፡

በዚህ እቅድ ላይ አንድ ትልቅ ጥያቄ አሁንም ተንጠልጥሎ ይገኛል፤ ተጫዋቾቹ ለብሔራዊ ቡድን ለመወዳደር የሚያስፈልጋቸው የብቁነት ማዕቀፍ እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡ ንድፈ-ሀሳቡ ይህንን በግልጽ አምኖ የተቀበለ ሲሆን የብቁነት ማዕቀፉ ተጠናቅቆ ሲወጣ ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ተግባር መሸጋገር እንድትችል፣ አሁን ላይ ተጫዋቾችን መለየትና ግንኙነት መገንባት ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡

ከገንዘብ አንጻር ፕሮግራሙ በንግድ ስፖንሰርሺፕና በስትራቴጂክ አጋርነት እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ የተዘጋጀ እንጂ በፌዴሬሽኑ በጀት የሚሸፈን እንዳልሆነ ተቀምጧል፡፡ ከፌዴሬሽኑ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር የድጋፍ ደብዳቤ መፈረም ብቻ ሲሆን በዴቪድ በሻህ የቀረበው ንድፈ-ሀሳብ ላይ ይህ ደብዳቤ ከስፖንሰሮችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ለሚያደርጉት ውይይት ተአማኒነትን እንደሚጨምርላቸው ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያው ካምፕ ስኬታማ ሆኖ ከቀጠለ  ፕሮግራሙ ከመጀመሪያው ቡድን አልፎ እንዲያድግ ማቀዱን ገልጿል፡፡ ይህንን ፕሮግራም ወደ ተጨማሪ የዕድሜ ክልል ምድቦች፣ ወደ ሴቶች እግር ኳስ፣ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ወደሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች ጭምር ትኩረቱን ለማስፋት ታቅዷል፡፡ የፕሮግራሙ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ግን በዚህ የሙከራ ካምፕ ውጤትና በትይዩው በሚካሄደው የብቁነት ድርድር ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.