” አላለቀም”- ከድሉ በስተጀርባ

የጊዜ መቁጠሪያችንን ብዙም ሳናንሸራትት ልክ የዛሬ ወር አካባቢ በዛ የዋንጫውን መዳረሻ ይወስናል በተባለው ጨዋታ ማንቺስተር ሲቲ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ተቀናቃኙ አርሰናልን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸነፈ። በዚህ ወቅት ነበር “አርሰናል እና የሊጉ ዋንጫ ዘንድሮም ላይታረቁ ነው?” የሚለው ጥያቄ መነሳት የጀመረው፤ በዛን ጨዋታ ወቅት ግን የቡድኑ የመሀል ሜዳ ሚዛን ሞተሩ ዴክላይን ራይስ አንዲት ቃልን ተናግሮ ነበር ” አላለቀም( It’s not done)”

አዎ እውነትም አላለቀም ነበር። ቀጣዮቹ 4 ሳምንታት ዋንጫው መዳረሻ ለመወሰን ገና እንደሆነ ያሳዩ እና የአርሰናልን ተስፋ ያለመለሙ ሆነውም ቆይተዋል። በተለይም ደግሞ ማንቺስተር ሲቲ ከቶፊሶቹ ጋር ተጫውቶ ነጥብ የጣለበት ጨዋታ አርሰናልን በደንብ ለዋንጫው እንዲንደረደር ሲያደርገው ከዌስትሀም እና ትላንት ምሽት ደግሞ ከበርንሌይ ጋር የነበረው የጠባብ ውጤት የ1 ለ 0 አሸናፊነት የደጋፊዎችን ልብ ሰቅዘው የያዙ ጨዋታዎች ነበሩ።

ከድሉ መለስ ስንል ለዚህ ድል ዋነኛው ሰው ማነው ብለን ከቀዳሚዎቹ መሀከል ማይክል አማርቲያን አርቴታን ሳንጠቅስ ማለፍ አንችልም። ይህ ሰው በፔፕ ጋርድላ ስር በሲቲ ቤት ምክትል ሆኖ ቡድኑን ከመራ በኋላ በታህሳስ 2019 የአርሰናል ዋና አሰልጣኝ ተደርጎ በተሾመ ወቅት የቡድን የመጀመሪያ ስብሰባውን ሲያደርግ የስብሰባ መቀመጫ ወንበሮቹ ተዘቅዝቀው እንዲቀመጡ አድርጎ ተጫዋቾቹን ይጠብቃቸዋል፤ በሁኔታው ግራ የተጋቡት የወቅቱ የአርሰናል ተጫዋቾችንም እያንዳንዱን ወንበር እያነሱ ወደነበሩበት ትክክለኛ የአቀማመጥ ቅርፅ እንዲያስቀምጡ ካዘዛቸው በኋላ ስብሰባውን ሲጀምር ” ተዘባራርቆ/ ተገልብጦ ተቀምጦ የነበረው ወንበር በሜዳ ላይ ያለው ቡድናችንን ይወክላል” ሲል ነበር ንግግሩን የጀመረው።

አርቴታ በእርግጥም በወቅቱ ምሳሌው ትክክል ነበር። ከሜዳ ውጭ ያሉ ሁኔታዎችን ስንመለከት እሱ ቡድኑን ሲረከብ( ከ6 አመት ተኩል በፊት) ቡድኑ የፕሮፌሽናሊዝም ችግር ያለባቸው ኮከቦች የሚገኙበት እና እርስ በእርስ የማይዋደዱ/ የአንድነት ስሜት የሌለላቸው ተጫዋቾች የበዙበት ነበር። እንደውም እንደቴሌግራፍ ዘገባ በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ሁለት ተጫዋቾች አዘወትረው ከመጣላታቸው የተነሳ ” ውጭ እንገናኝ” አይነት መልእክቶችን በማስተላለፍ እርስበእርስ ሲዛዛቱ ከርመዋል። በሜዳ ላይም እንዲሁ ቡድኑ ቅርፅ አልባ ሆኖ የተመለከትንባቸው ጊዜያቶች ጥቂት አደሉም። ጠንካራ የቡድን መንፈስ መገንባት ከምንም ነገር በላይ እንደሚቀድም የተረዳው አርቴታም ገና ከመምጣቱ ይሄን ስሜት መፍጠርን ቀዳሚው ተግባሩ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል። ጎንለጎንም ታዲያ የሜዳ ላይ ክፍተቶች በታክቲካዊ አቀራረብም ሆነ በዝውውር መስኮቶቹ ቀስበቀስ በሂደት ተሸፍነው ቡድኑ የተሻለ እንዲሆን አድርጓል።

ይሄ በአርሰናል ቤት የሰጠው የመጀሪያው የምሳሌ ትምህርት ይሁን እንጂ ከዛ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን መጠቀሙን የምንዘነጋው አይደለም። በቅርብ የነበሩትን እንኳን ብናስታውስ: ፕሮፌሽናል ኪስ አውላቂዎችን መቅጠሩ፣ የቀድሞ የእንግሊዝ የአየር ሀይል አባልን ቡድኑን እንዲያስተምር መጥራቱ፣ በልምምድ ሜዳ ላይ የአንፊልድን ድባብ ለማምጣት በሚል ‘ You will never walk alone’ የሚለው የክለቡ የህብረት መዝሙር መክፈቱን እናስታውሳለን። አርቴታ በእርግጥም ልክ አብሮት እንደሰራው ፔፕ ጋርድዮላ ሁሉ ለጥቃቅን ነገሮች የሚጨነቅ እና ቀስ በቀስ በሂደት በሚፈጠር የቡድን ግንባታ እንደሚያምን ከእለት ወደእለት እያሳየ ባመጣው ውጤት ይንፀባረቃል።

ይሄም ብቻ ሳይሆን አርሰናል ለተከታታይ ጊዜያት ለዋንጫ እየደረሰ ባዶ እጁን በተመለሰባቸው አመታት ” Trust the Process” በሚለው ቃሉ ለደጋፊዎች እምነት እንዲጥሉበት ደጋግሞ ገልጿል። አሁን ያ ልታመንበት ይገባል ያለው ሂደት ፍሬ አፍርቷል እና ከአንገቱ ቀና ብሎ የሚራመድበት ጊዜ ደርሷል። ገና ደግሞ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እንዳለበት ሲታሰብ እሱን ካሳካ በክለቡ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የማይፋቅ ደማቅ አሻራ መፃፉን እንደሚያረጋግጥ እሙን ነው።

ከአርቴታ በተጨማሪ ግን አሁን ላይ አሰልጣኞችን ለወራት እንኳን ማይታገስ የዘመናዊ እግር ኳስ አስተዳደር በነገሰበት ሰአት አርቴታ በእርግጥም አሸናፊ ቡድን እየገነባ ነው ብለው በማመን ለአመታት ለዋንጫ እየደረሰ ሲመለስ ታግሰው ፍላጎቱን አሟልተው በቡድኑ እንዲቆይ ያደረጉትን አመራሮች አለማድነቅም አይቻልም። በአርሰናል ቤት አመራሮቹ ይውጡልን በሚል ተቃውሞ የሚነሳባቸው ጊዜያቶች ሩቅ አልነበሩም። አርቴታም እንዲሁ ” Out” የሚል ባነር በደጋፊዎች ተይዞበት ተገብቶ ያውቃል። አመራሮቹም ሆነ አርቴታ ግን በስክነት ነገሮችን ማስኬዳቸው ለዛሬዋ ለቡድኑ ልዩ የድል ቀን እንዲበቁ ምክንያት ሆኗል።

በሜዳ ላይ አርሰናል ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችል ጥሩ ቡድን ነበረው። የዘንድሮው ልዩነት ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ስኳድ (squad depth) መኖሩ ነው። አርሰናል አሁን ላይ በአመት እስከ 4 ዋንጫዎች ለማሳካት የሚፎካከር ቡድን ከመሆኑ አንፃር የቡድኑን የተለያየ መድረኮች ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ ” የቡድን ጥልቀት” ወሳኝ ነውና ይሄ ጉዳይ በተለይም ባለፈው የዝውውር መስኮት በአግባቡ ሊቀረፍ መቻሉን የዘንድሮው የወድድር ዘመን የቡድኑ ጉዞ ያመላክታል። ባለፈው ክረምት በዝውውር መስኮቱ ላይ የተደረገው ትኩረት በጥልቀት ላይ እንጂ የአንድ ቡድንን ጣሪያ ከፍ ለማድረግ አለመሆኑ ለዘንድሮው የ22 አመታትን የዋንጫ ጥም ለቆረጠ ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ለዛሬ እዚህ ጋር ይብቃን በሌላ ፅሁፍ ስለድሉ እንመለሰበታለን። ላለፉት 22 አመታት ይህቺን ቀን ስትጠብቁ ለነበራችሁ የአርሰናል ደጋፊዎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ።

በራይስ ንግግር ፅሁፉ እንደተጀመረው ሁሉ ራይስ አርሰናል ሻምፒዮን መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባሰፈረው ፅሁፍ እናብቃ

” ነግሬያችሁ ነበር…ተጠናቋል።”

ሰናይ ለሊት!

✍️ በዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.