የ10ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር በባህር ዳር
1ኛው የኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ሦስተኛ መዳረሻውን ባህርዳር ላይ አካሂዶ ነገ ጠዋት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ይህ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ የሚገኝ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ተከታታይ ምዕራፍ አንዱ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ፉክክር በመቀሌ ተጀምሮ፣ ሁለተኛው መዳረሻውን በደቡቧ እምብርት ሐዋሳ ማድረጉ ይታወሳል። በሐዋሳው ውድድር ላይ ቻምፒዮን መሆን የቻለውን ሐጎስ ገብረህይወትን ጨምሮ በርካታ ከዋክብት አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ተራው የባህርዳር ሆኗል።
ለነገው ፍልሚያ 91 አትሌቶች ከ6 ክለቦች የተውጣጡና በግል የሚወዳደሩ ሯጮች (68 ወንዶች እና 23 ሴቶች) ተወዳዳሪ ይሆናሉ። 50 ዳኞችም ውድድሩን ይመራሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ጊዜ አድነው እና የኮሚኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያው አቶ መሐሪ ነጋሽ ባለፈው ሐሙስ በጋራ በሰጡበት መግለጫ ባህርዳር ላይ የሚደረገው ፉክክር ትልልቅ ስም ያላቸው አትሌቶችን እንደሚያሳትፍ ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት በጎዳና ላይ 10 ኪሎ ሜትር 28:02 የሆነ ፈጣን የግል ሰዓት ያስመዘገበው ብርቱ አትሌት ንብረት ክንዴ በዚህ ዓመት በሀገር ውስጥ ከትራክ እስከ ጎዳና ያላሳካው ድል የለም። ንብረት በቅርቡ በዘመናዊው ታይም ትሮኒክስ ዳኝነት በተካሄደው አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ ሜትር 28:39.49 በሆነ ሰዓት አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቁ ይታወሳል። የድል ጉዞው በዚህ አያበቃም፤ በዚሁ ዓመት ግንቦት ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የ”ዛይድ የደግነት ሩጫ” አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ባለፈው ሚያዝያ ደግሞ በ4ኛው “ኢትዮጵያ ታምርት” የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወክሎ ድል ቀንቶታል። ነገም ባህርዳር ላይ ለአሸናፊነት ቀዳሚው ግምት ቢሰጠው አያስገርምም።
ከወቅቱ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ንጉስ አትሌት ንብረት ባሻገር በረጅም ርቀትና በማራቶን ትልቅ ስም ያለው ጀማል ይመር ሌላኛው የነገው የድል ተፎካካሪ ነው። እኤአ በ2018 በአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ወርቅ ያጠለቀው ጀማል፣ በኋላ ላይ ፊቱን ወደ ማራቶን በማዞር በደቡብ ኮሪያው ታዋቂ የሴዑል ማራቶን ድንቅ ብቃት አሳይቶ በ2:06:8 በሆነ ፈጣን የግል ሰዓቱ ማሸነፉ ይታወሳል። በዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶንና የጎዳና ላይ ውድድሮች ሰፊ ልምድ ያለው ጀማል፣ የባህርዳርን ወርቅ ለመውሰድ ከሚፋለሙ ኮከቦች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሴቶቹ ወገን የሚደረገው ፉክክርም እኩል ትኩረትን የሚስብና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ሯጮችን የሚያገናኝ ነው። በርካታ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ ያላት አትሌት ውዴ ከፋለ የሴቶቹን ስብስብ በግንባር ቀደምትነት ትመራለች። ውዴ በአፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀች ኮከብ ከመሆኗ በተጨማሪ፣ በ2025 የመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሯን በኮፐንሀገን አድርጋ 1:05:21 በሆነ ግሩም ሰዓት 3ኛ ሆና አጠናቃለች። የ2026 የውድድር ዓመቷን በቫሌንሲያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር 29:55 በሆነ የግል ምርጥ ሰዓት 4ኛ ሆና በመጨረስ የጀመረችው ውዴ፣ ነገ የባህርዳርን አክሊል ለመድፋት ትሮጣለች።
ሌላኛዋ ዓለም አቀፍ ኮከብ አሳየች አይቸው የባህርዳር ጎዳናዎች እንግዳ እንደምትሆን ይጠበቃል። አሳየች በ2025 በቫሌንሲያ 10 ኪሎ ሜትር 29:43 በሆነ ሰዓት 4ኛ ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው ውጤት በርቀቱ ከዓለም አስር ፈጣን ሰዓቶች አንዱን አስጨብጧታል። የአሳየች የቅርብ ጊዜ ስኬቶችም አስደናቂ ናቸው፡-በ2025 የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ ስትሆን፣ በ2026 የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና (ቴላሀሴ) በግሏ 4ኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የቡድን ወርቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቷ አይዘነጋም።
ባለፈው ሚያዝያ በዋሺንግተን ዲሲ የ10 ማይል ውድድር በ50:37 በማጠናቀቅ አንደኛ የሆነችው ይህች ተስፈኛ ኮከብ፣ ከአንድ ወር በፊት በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር የግሏን ምርጥ ሰዓት ወደ 14:26:41 ያሻሻለች። በተለያዩ ርቀቶች ላይ ስኬታማ መሆን የቻለችው ኮከብ፣ ነገ ባህርዳር ላይ የምታደርገው የጎዳና ላይ ፍልሚያ ለተመልካች ትልቅ የዓይን ማረፊያ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዋቢ: ዘመን ስፖርት
✍️ ዮናታን አየለ
