“ጋብሬል ማጋሌሽ ቀይ ካርድ ሊያይ ይገባ ነበር”- ፕሪምየር ሊግ
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በየጊዜው ቁልፍ የሆኑ የጨዋታ አጋጣሚዎች ላይ የሚያደርገው የፓናል ውይይት አለ። በዛሬው እለትም ታዲያ በተደረገው ግምገማ ላይ መለስ ብለው ከተቃኙ አጋጣሚዎች አንዱ ጋብሬል ማጋሌሽ እና ሀላንድ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግብግብ ነው። የጨዋታው ዋና ዳኛ የነበሩት አንቶኒ ቶለር በሰአቱ ሁነቱን በቢጫ ካርድ ነበር ያለፉት፤ ሆኖም ግን ሁኔታው መለስ ብሎ ሲገመገም ማጋሌሽ ጭንቅላቱን ወደሀላንድ ያስጠጋበት እንቅስቃሴ የህግ ጥሰት ስለሆነ ቀይ ካርድ ይገባው እንደነበር በድምፅ ብልጫ ወስነዋል።

ሁነቱን ከገመገሙት 5 የሊጉ አባላት መሀከል ሶስቱ ቀይ ካርድ ይገባዋል ያሉ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ማጋሌሽ ላይ የሚጣል ምንም አይነት ቅጣት አይኖርም። በጨዋታው ላይ የነበሩት ዋና ዳኛ ምናልባትም የቀይ ካርድ ውሳኔ አስተላልፈው ቢሆን ኖሮ ማጋሌሽ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ከመሆኑ አንፃር በክለቡ ወሳኝ የሊጉ ጨዋታዎች ተፅእኖ ሊፈጥር ይችል እንደነበር እሙን ነው።
ማንቺስተር ሲቲ እና አርሰናል አሁን ላይ የ3 ነጥብ ልዩነት ያላቸው ሲሆን ማንቺስተር ሲቲ 1 ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ብዙዎችም በዚህ ሰአት የሊጉ ዋንጫ ማረፊያ ማንቺስተር ወይስ ለንደን የሚለውን ለመመልከት ጓጉተዋል። በዚህም ሳምንት በእለተ ሰኞ ማንቺስተር ሲቲ ከ ኤቨርተን ሲጫወት አርሰናል ደግሞ ነገ ምሽት 1:30 ሲል ከፉልሀም ጋር ይጫወታል።
✍️ ዮናታን አየለ
