የዘንድሮው ማንቺስተር ሲቲ በሀላንድ ላይ ጥገኛ ይሆን?
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ ሀላንዴ በ12 ጨዋታዎች 8 ጎሎች ሲያስቆጥር ከሌሎች የማንቺስተር ሲቲ ተጫዋቾች ግን ከአንድ በላይ ጎል ያስቆጠረ የለም።
ይሄን ቁጥራዊ መረጃ ተንተርሶም የማንቺስተር ሲቲ ማጥቃት ሀላንድ ላይ ጥገኝነት አለው የሚለውን ጠቋሚ ነው ወይ በሚል ለጋድዮላ ጥያቄ ቀርቦ ” ከሀላንድ ውጭ ጥሩ ነገሮችን መስራት እየቻልን አደለም። ሌሎች ተጫዋቾቻችን መሻሻል ይኖርባቸዋል” ሲል መልሷል።

ሀላንድ በዚህ የውድድር ዘመን በ13 ጨዋታዎች 23 ጎሎች ያስቆጠረ ሲሆን 6 ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጎል በማስቆጠርም የጀሚ ቫርዲ የ11 ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል የማስቆጠርን ሪኮርድ ለመስበርም ተቃርቦ ነበር።
ፊል ፎደን ጥሩ ፈጣሪ ነው ግን ብዙም ጎል እያስቆጠረ አይደለም። ማትዌስ ኑኔስ ጥሩ እንቅስቃሴ አለው፤ የመጨረሻ ንክኪዎቹ ጥራት ይጎላቸዋል። ቲጃኒ ራይንደርስ ጥሩ ቦታ አያያዝ አለው፤ ግን ደግሞ አጋጣሚዎችን ወደጎል መቀየር (Conversion rate) ላይ ዝቅተኛ ነው። ራየን ቸርኪ ሪትሙን ለማግኘት እየተቸገረ ይገኛል፤ ወጥ አቋምም እያሳየ አይደለም። ሳቪንሆ እና ዶኩ የሆነ ብልጭታ ያሳያሉ፤ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ችግር ይታይበታል።
ለመሆኑ ማንቺስተር ሲቲ በሀላንድ ላይ ምን ያህል ጥገኛ ነው?፤ ቡድኖች በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ጥገኝንተ አሳዩ ሚባለውስ በምን ያህል መቶኛ ጥገኛ ሲሆኑ ነው?
በፕሪምየር ሊጉ በአንድ አጥቂ ላይ የታዩ ከፍተኛ በአንድ አጥቂ ላይ የተመረኮዙ የጎል ጥገኝነቶችን ከተመለከትን:
1. 1994/95 – አለን ሺረር( ብላክ በርን)- 42.5%
2. 2003/04- ቴሪ ኦንሪ( አርሰናል)- 41.1%
…. እያልን የጀሚ ቫርዲን የ2015/16 35.3%እና የመሀመድ ሳላህን የ2024/25 33% መጥቀስ እንችላለን። እስካሁን ባለው ማንቺስተር ሲቲ ደግሞ ጎልን በተመለከተ ሀላንድ ላይ በ64.7% ጥገኛ ነው። በዚሁ ከቀጠለ ይሄ ከሁሉም ከፍተኛ ያደርገዋል። በአማካይ ዋንጫ ያሸነፉ ቡድኖች አጥቂ ከቡድኑ የጎል መጠን በምን ያህሉ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለን ካየን ደግሞ 25.9% ሆኖ እናገኛዋለን። ይሄም የሀላንድ 64.7% በዚሁ ከቀጠለ እጅግ ከፍተኛ ጥገኝነት መሆኑን ያሳየናል።
ከጎሎች በተጨማሪ በጎል ሙከራ ራሱ ማንቺስተር ሲቲ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከመጫወቱ በፊት 105 የጎል ሙከራ ሲያደርግ 34ቱ በሀላንድ የተሞከሩ ናቸው። ይሄ ማለት 32.4% የሱ ሙከራ ነው። በዚህ ዘርፍ ደግሞ አማካዩ ቁጥር 20% ሆኖ ማግኘታችን የሀላንድ ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ እንደማሳያ ለማቅረብ ያሰችለናል።
ለሀላንድ ጎሎች መገኘት የሌሎች ተጫዋቾች ከኳስ ጋር ሆነም ከኳስ ውጭ ያላቸው እንቅስቃሴ ግን ወሳኝ መሆኑ መረሳት የለበትም። ዋናው የውጤት መገለጫ ግን ጎል ነውና በዚህ ዘርፍ የመጨረሻው አድራጊ( ጎል አግቢው) ትኩረት መሳቡ አይቀሬ ነው። በበርካታ ጎል አግቢዎች የሚታወቀው የጋርድዮላ ቡድን ደግሞ እንዲህ አይነት ቁጥራዊ መረጃዎች አንድ አጥቂ የሚያስመዝግበት ቡድን ሲሆን በወጥ ብቃት ጨዋታዎችን እያሸነፉ ለመሄድ አይቸገርም ወይ የሚለው ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል።
– ለዘገባው እንደዘአትሌቲክ እና ቴሌግራፍ ያሉ ገፆችን በዋቢነት ተጠቅመናል።
✍️ ዮናታን አየለ
