በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ ውድድሮች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል!

በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ከተሞች ማራቶን እንዲሁም ግማሽ ማራቶን ውድድሮች የተደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

በአየር ላንድ ዋና ከተማ ደብሊን በሚደረገው የደብሊን ማራቶን ዳንኤል መስፍን የተሰኘ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው አትሌት 2:08:51 በመግባት አንደኛ ሲወጣ ከሱ 18 ሴኮንዶቾን በመዘግየት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ማናዞት ስዩም ሁለተኛ ወጥቷል። ሳሙኤል ፀጋዬ የተባለ ስዊድናዊ ደግሞ 2:09:29 በመግባት ውድድሩን በሶስተኝነት ጨርሷል። ሩጫውን ሙሉ ኮፍያ አድርጎ ሲሮጥ የነበረው አሜሪካዊው መስፍን ለRTE Sport እንደገለፀው ከሆነ በወቅቱ የነበረው የአየር ሁኔታ ፈታኝ ነበር። አትሌቱ ከ2 ሳምንታት በፊት በሩጫው ሰአት ሊኖር የሚችለውን የአየር ትንበያ መረጃ ተንተርሶ ከውድድሩ ለመውጣት እና ሌላ ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ የሚችልባቸውን ሩጫዎች በመፈለግ ላይ እንደነበር የገለፀ ሲሆን በስተመጨረሻ ግን በውድድሩ ተካፍሎ ማሸነፍ ችሏል።

በሴቶቹ ዘረፍ ደግሞ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጠችው ኤቢሴ አዱኛ የተሰኘች አትሌት በ2:26:28 አንደኛ ስትወጣ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ኬና ግርማ እና አፀደ ባይሳ ተከታትለው ገብተዋል።

በጣሊያን ቬነስ ከተማ በተደረገው የቬነስ ማራቶን ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ባለድል ሆነዋል። በወንዶቹ 2:08:58 በመግባት ድርቤ ሮቢ አንደኛ ሲወጣ ኬንያዊው አይዛክ ቼሉኮ እና ሀሚንግቶን ኪማዮ ደግሞ 2ኛ እና 3ኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል። በሴቶቹ ዘርፍ ዘበናይ አሹማር በ2:27:29 አንደኛ፣ አዛለች መርሻ ደግሞ በ2:30:41 ሁለተኛ ስትወጣ ዴዚ ጀሙታይ ከኬኒያ 3ኛ ወጥታለች።

በጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶንም ኢትዮጵያኑ ባለድል ሆነዋል። በወንዶቹ የ29 አመቱ ኢትዮጵያዊ በላይ አስፋው እምብዛም የአሸናፊነት ቅድመ-ግምት ሳይሰጠው 2:06:16 በመግባት አሸናፊ ሲሆን ተሬሳ ቤኩማ ደግሞ በ2ተኝነት ውድድሩን አጠናቋል። በ2017 የውድድሩ አሸናፊ የነበረው ሹራ ቂጣታ በበኩሉ 3ኛ መውጣት ችሏል። በሴቶቹ ደግሞ ቡዜ ዲሪባ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ውድድሩን በራሷ ቁጥጥር ማድረግ ችላ ነበር። በስተመጨረሻም 2:20:00 በመግባት  የ42ኛው የማኖቫ ፍራንክፈርት ማራቶን አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።

በፖርቹፓል ሊዝበን በተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ በወንዶቹ ኢማኑኤል ዳውዲ ዲንዴይ በ1:00:30 አሸናፊ ሲሆን  ኢትዮጲያዊው ሚኪያስ ባረጋ በ1:01:55 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በሴቶቹ ዘርፍም እንዲሁ ሳይንቲሀ ቼሌንጋት ከኬንያ በ1:07:20 አንደኛ በመውጣት ውድድሯን ስታጠናቀቅ ኢትዮጵያዊቶ ጫልቱ ዲዳ ደግሞ የግል ፈጣን ሰአቷን በማስመዝገብ 2ኛ መውጣት ችላለች።

በስፔን ቫሌንሺያ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ከዚህ በኋላ ፊቱን ወደጎዳና ላይ ውድድሮች እንደሚያዞር የተናገረው ዮሚፍ ቀጀልቻ 58:02 በመግባት ውድድሩን በመሪነት አጠናቋል። በሴቶቹ ደግሞ ንጌቲች ከኬንያ በ1:03:08 አንደኛ ሰትወጣ ኢትዮጵያዊቷ ፎትየን ተስፋይ በ1:05:11 2ኛ ወጥታለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published.