የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የቀን 1 የኢትዮጵያውያን ውሎ፤ ዛሬስ ምን እንጠብቅ?
የ20ኛው የቶክዮ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትላንት በተለያዩ ውድድሮች መደረጉን ጀምሯል። ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም 3 የማጣሪያ እና 2 የፍፃሜ የውድድሮች ላይ ተሳትፈዋል።
ቀደም ብሎ ቀን 6:05 ሲል በጀመረው የ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ማጣሪያ ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወደፍፃሜ ያለፉበትን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በምድብ 1 ጌትነት ዋሌ 2ኛ፣ በምድብ 2 ሳሙኤል ፍሬው 3ኛ እንዲሁም የርቀቱ ፈጣን ሰአት ባለቤት የሆነው ለሜቻ ግርማ በምድብ 3 2ኛ በመሆን ወደቀጣዩ ዙር አልፈዋል። በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ለማምጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው ሚጠበቁት ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኮዊው ሶፍያን ኤልባካሊ በአንድ ምድብ ማጣሪያቸውን አድርገው ኤልባካሊ 1ኛ ለሜቻ 2ኛ መውጣት ችሏል።
ለሜቻ ውድድሩ እንደተጀመረ አካባቢ በተፈጠረ መጠላለፍ ወድቆ የነበረ ቢሆንም ዳግም በመነሳት ወደፍፃሜ ያለፈበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። አትሌቱ ከውድድሩ በኋላ በስፍራው ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስም መውደቁ በሩጫው ከሚኖር መተፋፈግ አንፃር በየትኛውም ሰአት የሚያጋጥም ነገር እንደሆነ በመግለፅ በፍፃሜው ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቅ ገልጿል። ከዚህ ቀደም በፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ለሜቻ ውድድሩን ማሸነፍ የሚያሰችለው ብቃት ላይ ሳለ መውደቁ አይዘነጋም፤ ይህንን አጋጣሚ ለመካሰም በምን አይነት ዝግጁነት ላይ ነህ ተብሎ የተጠየቀው ለሜቻ ” በኔ በኩል ጥሩ ዝግጅት አድሬያለሁ። ፈጣሪ ካለ ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ እጠብቃለሁ” ብሏል። ሌላኛው ወደፍፃሜው ያለፈው ሳሙኤል በበኩሉ “ለሜቻ ቢወድቅም ዋናው ነገር መልሶ ተነስቶ ወደፍፃሜ ማለፍ መቻሉ ነው፤ ተነጋግረን የተሻለ ውጤት እንደምናመጣ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል። የ3000 ሜ መሰናክል ፍፃሜ ሰኞ ይደረጋል።
በመቀጠል ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ውድድር የ1500 ሜትር ማጣሪያ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርቀቱ ጥሩ ብቃት እያሳየች ያለችው ፍሬወይኒ ሀይሉ በምድብ 3 1ኛ በመውጣት ወደግማሽ ፍፃሜ አልፋለች። ተጠባቂዋ ኬንያዊ አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎንም እንዲሁም ከምድብ 4 አንደኛ መውጣት ችላለች። የ1500 ሜትር ግማሽ ፍፃሜ ዛሬ በእለተ እሁድ ከቀኑ 9:07 ሲል ይጀምራል።
ተጠባቂ የነበረው የሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ ውድድር ላይም ኢትዮጵያ ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፎትየን ተስፋዬ እና ፅጌ ገ/ሰላማን አሰልፋ የነበረ ሲሆን ጉዳፍ ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያ የሆነውን ሜዳሊያ ነሀስ በማምጣት ማስመዝገብ ችላለች። ቤትሬስ ቺቤት በ30:37:61 አንደኛ፣ ናዲያ ባቶክሌቲ በ30:08:23 ሁለተኛ እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይ በ30:39:65 ሶስተኛ ወጥተዋል። ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት በሰአቱ የነበረው ሙቀት በአግባቡ እንዳትሮጥ እንቅፋት እንደሆነባት በመግለፅ ግን ደግሞ ይሄ ለሁሉም ተመሳሳይ በመሆኑ ያንን እንደሰበብ ማንሳት እንደማትፈልግ ገልፃለች።
ጉዳፍ ፀጋዬ ጠንካራ ጎኗ ዙር ማክረር ሆኖ ሳለ ለምን እስከመጨረሻው ሜትሮች ርቀት ድረስ በማፈትለክ ጎበዝ የሆነችው ቼቤት ጋር እንደሮጠች ስትጠየቅም ” 1000 ሜትር ላይ ዙሩን ለማፍጠን ሞክሬ ነበር ግን ሙቀቱ ከብዶኛል፤ ሙቀቱ ነው ፈተና የሆነብኝ፤ ደስ ብሎኛል፤ በአለም ሻምፒዮና 5ኛ ሜዳሊያዬን ነው ያገኘሁት። ይሄ ለአንድ አትሌት ቀላል አይደለም” ብላለች። ጉዳፍ ፀጋይ ከዚህ ቀደም በርቀቱ በቡዳፔስት ላይ ኢትዮጵውያን ተከታትለው ከ1-3 በመግባት ታሪክ በሰሩበት አመት የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ አይዘነጋም።
በለሊቱ መርሀግብር ደግሞ 7:30 ሲል የሴቶች ማራቶን ውድድር ተደርጎ የነበረ ሲሆን ትግስት አሰፋ፣ ትግስት ከተማ እና ሱቱሜ አሰፋ ኢትዮጵያን መወከል ችለው ነበር። ትግስት አሰፋ እና ፔሬስ ጄፕቼርቼር እልህ አስጨራሽ ፉክክር ባደረጉበት በዚህ ሩጫ ልክ መካከለኛ ርቀት በሚመስል መልኩ በ2 ሴኬንዶች ብቻ ተቀዳድመው ፔሬስ በ2:24:43 1ኛ፣ ትግስት ደግሞ በ2:24:45 2ኛ ወጥተዋል። የኡራጋይ ዜግነት ያላት ጁሊያ ፓተሪኒያን በበኩሏ በ2:27:23 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ትግስት አሰፋ ሪኮርድ ልታሻሽልበት የምትችለውን የበርሊን ማራቶን ወደጎን በማድረግ ነው እዚህ ውድድር ላይ የተካፈለችው። የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ኔዘርላንዳዊት ሲፋን ሀሰን በሲድኒ ማራቶን ላይ ለማተኮር በሚል ከአለም ሻምፒዮና ራሷን ማግለሏ አይዘነጋም። በውድድሩ የተሳተፈችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሱቱሜ አሰፋ 27ኛ ስትወጣ ትግስት ከተማ ደግሞ ውድድሩን አቋርጣ ወጥታለች።
የ1500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ለሊት 9:00 የተደረገ ሲሆን ሁለቱም አትሌቶቻችን ኤርሚያስ ግርማ እና መለስ ንብረት በማጣሪያው ተሰናብተዋል። በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ጃኮብ ኢንግብሪንግስተንም እንዲሁ ከማጣሪያ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።
ዛሬም ኢትዮጵውያን የሚጠበቁበት ውድድር በአለም ሻምፒዮናው የሚደረግ ሲሆን ቀን 9:30 በፓሪስ ኦሎምፒክ 1 የብር ሜዳሊያ እንድናመጣ ያደረገው ቡድን በ10,000 ሜትር ወንዶች ፍፃሜ ይሮጣል። ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋ እና ቢኒያም መሀሪ በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ይሰለፋሉ። ዮሚፍ በ2016 እና በ2018 የአለም የቤት ውስጥ ሻምፓዮና በ3000 ሜትር ወርቅ እና በ2019 የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ10,000 ሜትር ብር ማምጣት የቻለ አትሌት እንደሆነ ይታወቃል። በሌላ በኩል በሪሁ አረጋዊ በዚሁ ርቀት በፓሪስ ኦሎምፒክ ብር ማምጣቱን የምናስታውሰው ነው። ሰለሞን ባረጋ ደግሞ በ2020 በተደረገው በቶክዮ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን መቻሉ አይዘነጋም። የቀድሞው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ወንድም ልጅ የሆነው ቢኒያም መሀሪ ደግሞ በተጠባባቃነት አለ፤ ቢኒያም 18 አመቱ ላይ ሲገኝ በቅርብ ጊዜ ጥሩ ተስፋ እያሳዩ ካሉ አትሌቶች መሀል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ባሳለፍነው የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ አትሌቶቹ ብቃት እያላቸው በታክቲክ ስህተት ወርቁ ከእጃችን ቢወጣም እንኳን በስተመጨረሻም በሪሁ አረጋዊ ባደረገው ተጋድሎ የብር ሜዳሊያውን ማግኘታችን አይዘነጋም። በውድድሩ ላይ የሚታየው የታክቲክ አቀራረብ ዛሬም ኡጋንዳዊያን እና ሌሎች ሚጠበቁ አትሌቶችን ቀድሞ በመግባት ለማሸነፍ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌላ በኩል የወንዶች ማራቶን ከለሊቱ 7:30 የሚደረግ ሲሆን ደሬሳ ገለታ፣ ተስፋዬ ድሪባ እና ታደሰ ታከለ ኢትዮጵያን ወክለው ይሮጣሉ። በዚህ ርቀትም ኢትዮጵያ ሜዳሊዬ ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል። ታደሰ ታከለ በውድድር ዘመኑ 2ኛ ፈጣን ሰአት ያለው ሲሆን ደሬሳ ደግሞ 5ኛ ፈጣን ሰአት አለው፤ ተስፋዬ ድሪባም በበኩሉ ዘንድሮ( 2025) 8ኛ ፈጣን ሰአት ያለው አትሌት ነው። ተስፋዬ ድሪባ በዘንድሮው የፈረንጆቹ አመት 2025 ባርሴሎና ላይ የማራቶን ባለድል ነበር። ታደሰ ታከለም በ2025 እዚያው ቶክዮ ላይ በተደረገ ውድድር የማራቶን ባለድል መሆን ችሎ እንደነበር አይዘነጋም። ደሬሳ ገለታም በ2024 የተደረገውን የሲቪያ ማራቶን ማሸነፍ ችሏል።
ለሊት 10:30 እንዲሁ የ3000 ሜ መሰናክል ማጣሪያ ሲደረግ አለምናት ዋለ፣ ሲምቦ አለማየሁ እና ሎሚ ሙለታ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
በዮናታን አየለ የቀረበ