የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል!
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደጋግመው የነገሱበት 20ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በጃፓን ቶክዮ መደረጉን ጀምሯል። ውድድሩ ከዛሬ አንስቶ እስከ መስከረም 11 2018 ድረስ የሚደረግ ሲሆን 198 ሀገራት እና ከ2200 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። 49 የተለያዩ ውድድሮችም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ድምቀት ይሆናሉ።ቶክዮ ከ1991 በኋላ ይህንን ውድድር ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ለቶክዮ 2020 ኦሎምፒክ ዳግም ተገንቦት አገልግሎት የሰጠው የጃፓን ናሽናል ስታድየምም ውድድሮቹን ለማስተናገድ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ኢትዮጵያም ከ800 ሜ አንስቶ እስከ ማራቶን ድረስ የሚወክሏትን አትሌቶች ወደስፍራው የላከች ሲሆን ዛሬ በሶስት ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። ከቀኑ 6:05 ሲል በወንዶች 3000 ሜ መሰናክል ማጣሪያ ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬው የሚሳተፉ ሲሆን ለሜቻ ግርማ የ3000 ሜ መሰናከል የአለም ሪኮርድ ባለቤት እንደሆነ ይታወቃል። በፍፃሜው ውድድር ላይ ከሞሮኮዋዊው ሶፍያን ኤልባካሊ ጋር የሚኖራቸው ፉክክር የአለምን ትኩረት የሚስብ እንደሚሆን ከወዲሁ ይጠበቃል።

ሌላው ዛሬ ሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከቀኑ 7:50 ሲል የሚጀምር ሲሆን ፍሬወይኒ ሀይሉ እና ሳሮን በርሔ ኢትዮጵያን ወክለው ይወደዳራሉ። ከዚህ ቀደም በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማግኘት የቻለችውና በርቀቱ ስትጠበቅ የነበረው ድርቤ ወልተጂ የቡድኑ አካል የነበረች ቢሆንም ትላንት ከውድድሩ መታገዷ ተገልጿል።
ድርቤ በምን ምክንያት ታገደች የሚለውን በዝርዝር ስንመለከት የአለም አቀፉ ፀረ-አበረታች መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሁለት አይነት የፀረ-አበረታች መድሀኒት ምርመራ ሂደቶች አሉት። አንደኛው አትሌቱ ውድድር ካደረገ በኋላ ወዲያውኑ የሚደረግ ምርመራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አትሌቱ ከውድድር ውጭ ባለበት ሰአት በየትኛውም ጊዜ ሳይነገረው ሊደረግ የሚችል ምርመራ ነው። አትሌቱ በተለይም በአለም አቀፍ የሩጫ ደረጃው ጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ከሆነ ከፍተኛ ትኩረት ይደረገብታል። በዚህም የተነሳ አንድ አትሌት ይሄንን የፀረ-አበረታች መድሀኒት ለመቆጣጠር ወደተቋቋመው አለም አቀፉ ‘ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት’ ወይም ደግሞ የየሀገሩ የፀረ-አበረታች መድሀኒት ተቋም ቋት ውስጥ ይመደባል። ይህ ከውድድር ውጭ የሚደረግ ምርመራ አትሌቱ ሳያውቅ በድንገት የሚደረግ በመሆኑ አንድ አትሌት ያለበትን ቦታ፣ የልምምድ ሁኔታውን፣ የት እንደሚያድር እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በተዘጋጀው ‘ whereabouts information’ ፎርም ላይ መሙላት ይኖርበታል። በዚህም መሰረት ታዲያ የሀገሪቷ ፀረ-አበረታች መድሀኒት ተቋም ወይም አለም አቀፍ ተቋም አትሌቱን ለምርመራ ሲፈልገው በቀላሉ ማግኘት ይችላል ማለት ነው።

ድርቤ ወልተጂም በወርሀ ግንቦት በኢትዮጲያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አማካኝነት ከውድድር ውጭ ላለ የፀረ-አበረታች መድሀኒት ምርመራ ተጠይቃ የነበረ ቢሆንም በቂ ምክንያት ሳታቀርብ ለምርመራው ፈቃደኛ አለመሆኗን ትገልፃለች። በፀረ-አበረታች መድሀኒት ህግ መሰረት ደግሞ ናሙና ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን ትልቅ የህግ ጥሰት ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚህ በኋላም በወርሀ ነሀሴ አትሌቷ ለኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ቀርባ በማስረዳቷ ባለስልጣኑ ከህግ ጥሰት ነፃ አድርጎ ያሰናብታታል። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር ቅድስት ታደሰ እንደምትገልፀው ከሆነም ድርቤ ዘንድሮ ተደጋጋሚ ምርመራ ተደርጎላት ከፀረ-አበረታች መድሀኒት ነፃ መሆኑ ተረጋግጧል።
ከዚህ በኋላ ታዲያ በፈረንጆቹ መስከረም 1 2025 የድርቤን ጉዳይ የያዘ ፋይል ከኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የተቀበለው ‘ አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት( AIU)’ ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ እና ነገሩ ሙሉበሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድርቤ ከውድድር ታግዳ እንድትቆይ ለአለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት( CAS) አቤቱታውን ያቀርባል። ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ‘ CAS’ም ትላንት አትሌቷ ከቶክዮ አለም ሻምፒዮና እንድትታገድ ውሳኔ አሳልፏል።
በሌላ በኩል የአትሌት ድርቤ ወልተጂ ጠበቃ(የህግ ባለሙያ) አቶ ይገርማል መልካም “ብዙ ሠው ነገሩ አሁን የተጀመረ መስሏቸው የተሳሳተ መረዳት ውስጥ ናቸው፤ነገሩ የተጀመረው አሁን ሳይሆን እ.ኤ.አ ፌብርዋሪ 25/2025 ነው”በተጠቀሠው ጊዜ ሶስት አባላትን የያዘ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ቡድን ወደ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ቤት በጠዋት ሄዱ፤በዛን ሠዓት አትሌቷ ልምምድ ሠርታ በቂ እረፍት ለማድረግ ላይ እንቅልፍ ላይ ስለነበረች ባለቤቷ ወጥቶ ይቀበላቸዋል፤ምን ልታዘዝ ሲላቸው ‘ለምርመራ ነው የመጣነው’ ይሉታል፤በዚህን ጊዜ እረፍት ላይ መሆናንና መተኛቷን ሲነግራቸው ‘ቀስቅሳት’ ይሉታል በዚህ ጊዜ ውስጥ ስትነሳ ሁለት ደቂቃ ብቻ ጠብቀው ይሄዳሉ፤በዚህ ሳታበቃም እየተከተለች ለምን ቀሠቀሳችሁኝ ለምን ሳትመረምሩኝ ትሄዳላችሁ?ብትልም ሰሚ አላገኘችም ይሄም አለም አቀፍ ህጉን የጣሠ ነው። ሲጀመር ድርቤ አልመረመርም አላለችም አለም አቀፉ ህግ የሚያስቀምጠው ብዙ ዝርዝር ነገሮች ስታንዳርዶች አሉ፤በሁለት ደቂቃ ያንን ሁሉ ማየት አይችሉም፤እነሱ ላቀረቡት ክስ ፕሮቶኮሉን ጥሠዋል፤አንድን እንቅልፍ ላይ ያለችን አትሌት ቆይተው ያለውንና የሚያመጣውን ችግር አስረድተው እምቢ ብትል እንኳን እምቢታዋን የሚያረጋግጥ ወረቀት ላይ እንድትፈርም አለም አቀፉ መመሪያ በሚጠይቀው መሠረት መሄድ ሲገባቸው ይሄንን ሳያደርጉ ነው የሄዱት፤በዚህም ፕሮቶኮሉን ጥሠዋል። ቀደም ሲል ይግባኝ ማለት ይችሉ ነበር፤ቀደም ብሎ ይግባኝ ቢጠየቅ እኛም የምናስብበት ሁኔታ ይኖር ነበር፤መልስ መስጠት በማንችልበት፣በተጣበበ ሁኔታ የቀረበ ጊዜያዊ ዕገዳ ከአለም አቀፍ አሠራር ጋር የሚፃረርም ነው”በማለት ተናግረዋል።”የቪዲዮም የተለያዩ ማስረጃዎች አሉን ቢሉም አንድም ማቅረብ እንዳልቻሉ በመግለፅ በአስተያየታቸው የቀጠሉት የህግ ባለሙያው”አለም አቀፉ መመሪያ በሚጠይቀው መመሪያ መሠረት መሄድ ሲገባቸው ሳይጠይቁ ነው ይሄ የተደረገው”ብለዋል።

በአትሌት ድርቤ ወልተጂ ከዚህ በኋላ ባላት የአትሌቲክስ ህይወት ላይ ምን ይወሰናል የሚለውን ተከታትለን የምናቀርብላችሁ ይሆናል። ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ የነበረ ሲሆን ይሄ ጉዳይ ተቋማቱ ችላ የማይሉትና አትሌቶች በብዛት ከገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍል በመምጣታቸው በባለሙያዎች ስለጉዳዩ በቂ ገለፃ እና እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል ሲል እሱ በሩጫ ዘመኑ እነዚህ የምርመራ ጊዜያት እንዳያልፉት ምን ያህል መስዋእትነት እየከፈለ ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር በሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ ላይ ቀርቦ አስረድቷል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚጠበቁበት የፍፃሜ ውድድር ደግሞ ከቀኑ 9:30 ይደረጋል። ። በርቀቱ በ1999 ሲቪያ ላይ በተካሄደ ውድድር ወርቅ ያመጣችው ጌጤ ዋሚ ስትሆን ከሷ በመቀጠል በ2003፣ በ2005 እና በ2007 ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ2017 ለንደን ላይ ደግሞ በማይረሳ አሯሯጥ አልማዝ አያና፣ በ2022 ለተሰንበት ግደይ፣ በ2023 ደግሞ ጉዳፍ ፀጋይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችለዋል።

የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ልዩ ዘገባችን እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።
በዮናታን አየለ የቀረበ
