የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል
ኦሌጎናር ሶልሻየር የማንቺስተር ዩናይትድ እቅድ አልባ አጨዋወት በሀገራት የጨዋታ ካላንደር ምክንያት ያገኘውን እረፍት ተጠቅሞ መልክ አስይዞት ከሆነ የሚያሳይበት ከባድ ፈተናን ሊቨርፑልን በመግጠም ያሳያል፡፡ የዩናይትድ አለቆች ክረምቱን በተለይ በአካል ብቃት እና ፊትነስ ጋር የተያያዘ ጠንካራ ዝግጅት ስናደርግ ነበር ቢሉም በየጨዋታው የተጫዋቾች ጉዳት ማስተናገዱን ቀጥሎበታል ከሳውዝሀምፕተን ጋር በተደረገው ጨዋታ ጉዳት ያጋጠማቸው ሉክ ሾው እና ማርሻል እስከአሁን ያልተመለሱ ሲሆን ለእሁዱ ጨዋታም መድረሳቸው አጠራጥሯል፤ በተጨማሪም ዴቪድ ዴሂያ ሃገሩ ስፔን ከስዊድን ጋር በነበባት ጨዋታ በ59ው ደቂቃ ተጎድቶ የጉዳት ዝርዝሩን ከፍ ያደረገው ሲሆን ለሁለት ወራት ከሜዳ እንደሚርቅ መነገሩ ለሶልሻየር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎበታል፡፡
የማንቺስተር ዩናይትድ ፊዚዮ ሩም እንደተናገረው ሉክ ሾው፣ አንቶኒ ማርሻል፣ አሮን ዋንቢሳካ፣ ሊንጋርድ፣ ግሪንዉድ፣ ጆንስ እና ዳሎት ለእሁዱ ጨዋታ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን የኤሪክ ቤሊ፣ ዴቪድ ዴሂያ፣ ፖል ፖግባ እና ፎንሱ ሜንሳህን ግልጋሎትን ግን ክለቡ አያገኝም፡፡ ይህም ከአስር በላይ የዋናው ቡድን ተጫዋቾች በአንድ ጊዜ መጎዳት በአሰልጣኞች ቡድኑ የአካል ብቃት ዲፓርትመንት ላይ ትልቅ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
ማንቺስተር ዩናይትድ በክረምቱ የተከላካየች ሪከርድ በሆነ ሂሳብ ያስፈረመው ሀሪ ማጓየር የማኔ፣ ፈርሚኒዮ እና ሳላህን ጥምረት ለማቆም ትልቅ ሀላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ግቡን አርጀንቲናዊው ሮሜሮ ይጠብቀዋል፡፡ በዚህኛውም ጨዋታ የናይትዶች ከታዳጊዎቻቸው ብዙ ይጠብቃሉ፡፡
የየርገን ክሎፑ ሊቨርፑል በዘንድሮ የውድድር ዘመን እስከአሁን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ያሸነፈ ሲሆን ከአምናው የውድድር ዘመን ጀምረው ያሸነፉባቸውን ተከታታይ ድሎች 17 አድርሰውታል፡፡ በእሁዱ ጨዋታ ድል የሚቀናቸው ከሆነ ይህን ቁጥር በአንድ በማሳደግ በማንቺስተር ሲቲ የተያዘው ሪከርድን የሚጋሩ ይሆናል፡፡
በሊቨርፑል ቤት የሚነፍሰው አየር የተረጋጋና ሰላማዊ ይመስላል፤ አዲስ ጉዳት የለም፣ የሚባረር የለም፣ ችግር የለም ሰላም ይመስላል፡፡ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ሞሀመድ ሳላህ ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር እና ጁዬል ማቲፕ ከጉዳት የተመለሱ ሲሆን በአሰልጣኙ ብቁ ናቸው ተብሎ ከታመነባቸው ሊሰለፉ ይችላሉ፤ የሻኪሪ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ ለሊቨርፑል ወጥ አቋም አሰልጣኙ ቋሚ አሰላለፋቸውን ማወቃቸው ዋናው ምክንያት መሆኑ በበርካቶች የታመነበት ሲሆን ፤ ለክሎፕ የሚያስጨንቃቸው ነገር ቢኖር በመሀል ሜዳው ላይ ከሄንደርሰን፣ ሚለር እና ዊናልደም ሁለት ተጫዋቾችን መርጦ ከፋቢኒዮ ጋር ማጣመር ነው፤ ኢክስሌድ ቻምበርሊን፣ ላላና እና ኬዬታ ለሁለቱ ቦታ በሚደረገው ፉክክር መኖራቸው ሳይረሳ፡፡ እንደተለመደው ሁሉ በዚህም ጨዋታ ሊቨርፑል ከሶስቱ የፊት መስመር ተጫዋቾቹ ብዙ ነገር ይጠብቃል፡፡
✋?ከጨዋታው መሐል ፡- ኦሊጎናር ሶልሻየር
የማንቺስተር ዩናይትዱ አሰላጣኝ ኦሊጎናር ሶልሻየር የመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል ወይ የሚለው ከጨዋታው ይጠበቃል፡፡ አሰልጣኙ ግልፅ የሆነ የአጨዋወት ፍልስፍና የሌለው ከመሆኑ በተጨማሪ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ እንኳን የማያውቅ ቡድን ሰርቷል ተብሎ በበርካቶች እየተተቸ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በክረምቱ ላጣቸው እንደ ሉካኩ፣ ሳንቼዝ፣ ሄሬራ እና ፌላይኒ አይነት ተጫዋቾች ተተኪ አለማምጣቱ ታክሎበት የዮርክሻየሩን ቡድን በ2 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ በማድረግ 12 ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡ ስሙ ከበርካታ አሰልጣኞች ጋር ከወዲሁ እየተያያዘ ለሚገኘው ማንቺስተር ዩናይትድ በእሁዱ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የማይችል ከሆነ ምናልባትም ከሶልሻየር ጋር ጋብቻውን ሊያፈርስ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ ሊቨርፑል በጆዜ ያደረገውን በመድገም አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ይሆናል፡፡
?ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አሰላለፍ
ማንቸስተር ዩናይትድ፡- ሮሜሮ፣ ተንዝቢ፣ ሊንደሎፍ፣ ማጓየር፣ ያንግ፣ ማክቶሚናይ፣ ፍሬድ፣ ፔሬራ፣ ጄምስ፣ ማታ፣ ራሽፎርድ
ሊቨርፑል፡- አድሪያን፣ አ. አርሎንድ፣ ቫንዳይክ፣ ማቲፕ፣ ሮበርትሰን፣ ሄንደርሰን፣ ፋቢኒሆ፣ ዊናልደም፣ ማኔ፣ ፈርሚኖ፣ ሳላህ