“ኢትዮጵያዊ” መፍትሄዎች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ: ከዶ/ር ጋሻው አብዛ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ

ለአመታት ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል። እግር ኳስ በኢትዮጲያ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ስፖርት ከመሆኑ አንፃር በይፋዊ ሚዲያዎችም ሆነ በማህበራዊ ብዙሀን መገናኛ መንገዶች ባለሙያውም ሆነ ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ይበጃል የሚለውን ሀሳብ ሲያጋራ ቆይቷል። በየጊዜው በሚመጡ የእግር ኳሱ አስተዳዳሪ አካላት ስር-ነቀል ለውጥ ባይታይም እንኳን የተወሰኑ ማሻሻያዎች ሲደረጉም አስተውለናል። ለአብነት ያህል ከጥቂት አመታት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የማስተዳደር ሚና ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ራሳቸው ሊጎቹ እንዲረከቡ የተደረገበት ውሳኔ ከበጎ ለውጦች መሀል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።

ክለቦች የራሳቸውን ሊግ በራሳቸው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላም ከሱፐር ስፖርት ጋር የተደረገውን ስምምነት ጨምሮ ሌሎች ሊጉን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስምምነቶች እንደተፈፀሙ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተመለከተ  በዶ/ር ጋሻው አብዛ በሚመራው ፊት ኮርነር የተሰራው ጥናት አንደኛው የለውጥ ጅማሮ ከታየባቸው ተግባራት መሀከል አንዱ ነበር። ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ካደረጉት ዶ/ር ጋሻው አብዛ ጋርም በዚህና በሌሎች የኢትዮጵያ እግር ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገናል።

ዶ/ር ጋሻው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ የሚገኘው ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ማኔጅመንት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በስፖርት ማርኬቲንግ፣ አስተዳደር እንዲሁም ቢዝነስ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን አድርገዋል። በ’ Human kinetics and Sport Management ‘ የፒኤችዲ ዲግሪ ያላቸው ዶ/ር ጋሻው በስፖንሰርሺፕ፣ ብራንዲንግ፣ ዲጂታል ሚዲያ እንዲሁም የፕሮፌሽናል ሊግ ልማት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎችንም አውጥተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጋባዥ ሪሰርቸር በመሆንም ያገለገሉ ሲሆን ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የመዋቅራዊ ‘ሪፎርም’ ፕሮጀክቶች አማካሪ በመሆንም መስራት ችለዋል።

ከዶ/ር ጋሻው ጋር ባደረግነው ቆይታ በመጀመሪያ ያነሳንላቸው ጥያቄም ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተመለከተ ሰርተው ለሼር ካምፓኒው ያስረከቡት ጥናት ውጤቶቹ ምን ይመስላሉ የሚል ነበር። እሳቸውም በምላሹ ” መጀመሪያ ጥናቱን ስንጀምር ለምንድነው ጥናቶች ተጠንተው በአግባቡ የማይተገበሩት የሚለውን ራሱን ነበር ያጠናነው። ሁለት ምክንያቶችንም ለይተናል” ካሉ በኋላ አስጠኚው አካል ጥናቱን በሼልፍ ላይ ብቻ አስቀምጦ ጥናቱ እንዳለው እያለ የራሱን ፍላጎቶች የሚያስፈፅምበት መሆኑ ቀዳሚው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ”  ሁለተኛ አጥኚዎቹ ራሱ የሚያቀርቡት ጥናት ከመፍትሄ ሀሳብ ማለትም አማራጭ መንገዶች ጋር ሚቀርቡ አልነበሩም። እኛ ሁለቱንም በሚያካትት መንገድ  ከጥናቱ በኋላ exit ስትራቴጂም አካተን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጋር ሰርተናል” ሲሉም ሀሳባቸውን ያስረዳሉ።

የኢትዮጲያ ፕሪምየር  ሊግን በተመለከተ በሰሩት ጥናት ላይም በእያንዳንዱ  አጀንዳ ላይ ከ46 በላይ የሚሆኑ ምክረሀሳቦች የ100 ሀገራት ተሞክሮ ከ200 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ከ90 በላይ ቀጥተኛ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ የፊፋ፣ የካፍ፣የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህግጋትን ያማከሉ ሀሳቦች መካታተቸውን በመግለፅ የኢትዮጲያ የሰራተኛ ህግን፣ ንግድ ፈቃድን እና የመሳሰሉትን አዎጆችን ያማከለ ሆኖ ተሰርቷል ሲሉ ስለጥናቱ ያብራራሉ። ጥናቱ ምን ያህል ተግባር ላይ ውሏል የሚለውን በተመለከተም ” 10 በመቶ እንኳን በሚሆን ተግባር ላይ ውሏል ለማለት ይከብደኛል። የሊጉ ሰዎች የራሳቸውን በጎ ነገር ለማረግ እየጣሩ እንዳሉ ይገባኛል ግን የመፍትሄ ሀሳብ ትግበራ ዙሪያ ላይ በጣም ብዙ ይቀረዋል” ብለዋል።

በጥናቱ ላይ ከቀረቡት ምክረ ሀሳቦች አንደኛው ከቆዳ ስፋት፣ ከፋይናንስ እና ከተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ምን አይነት የሊግ ፎርማት ለኢትዮጵያ ተስማሚ ነው የሚለውም ይገኝበታል። የሊግ ፎርማት አተገባበር አሁንም አንደኛው ችግር እንደሆነ ቢያነሱም ግን “ዋናው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር የባለቤትነት ችግር ነው” ይላሉ። “ከኢትዮጵያ ቡና እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጭ የባለቤትነት ፈቃድ ያለው ክለብ የለም” የሚለውን ሀሳብ ካነሱ በኋላም ባለቤትነት ህጋዊ ተጠያቂነትን እንደሚያመጣ በማብራራት ይጠቅሳሉ።

አብዛኞቹ ክለቦች ከመንግስት ቀጥተኛ ፋይናንስ እየተዳደሩ እንኳን ገንዘቡን በአግባቡ እየተጠቀሙት አለመሆኑም በተሰራው ጥናት ላይ ክለቦቹ በአማካይ ከአመታዊ በጀታቸው 75% የሚሆነውን የተጫዋች ደሞዝ ላይ ማዋላቸው ትልቅ ማሳያ እንደሆነም ዶ/ር ጋሻው ያስረዳሉ። ክለቦች በአካባቢያዊ መንግስታት ይዞታ ስር መገኘታቸውም የእግር ኳስ ስኬትን ከፖለቲካዊ የፉክክር ድል አንፃር ከመመልከት በዘለለ ስለእግር ኳስ ልማት እንዳያስቡ እንዳደረገም እንዲሁ በተያያዥነት ያነሱት ሀሳብ ነው።

የክለቦች ፈቃድ ( club licensing) ራሱ በሚገባ ያሟሉ ክለቦች ከተወሰኑት በስተቀር መጥቀስ እንደማይቻልም የሚያነሱት ዶ/ር ጋሻው የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ላይ 5 ቅድመ-ሁኔታዎች ተቀምጠዋል በማለት ያብራራሉ፤ እነዚህም አስተዳደራዊ፣ የፋይናንስ፣መሰረተ ልማትን፣ ህጋዊ ጉዳዮችን እንደሚያካትት በመጥቀስ “በየአመቱ ግን ለአፍሪካ ውድድሮች ሲያልፉ እንዳለፉ ተደርጎ ደብዳቤ ይፃፍላቸዋል፤ ለምን ከተባለ ደግሞ ብሄራዊ ጥቅም አንፃር እየተባለ ምክንያት ይሰጣል” ሲሉ ከክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት ያስረዳሉ። ” ኢትዮጵያ  ውስጥ የ25 ሰዎች ስብስብ ቡድን እንጂ ክለብ የለም። አብዛኞቹ ቢሮ እንኳን አልነበራቸውም። የማዘጋጃ ቢሮ ኮርነር ላይ ቢሮ ተሰጥቷቸው ነው ያሉት። መች ኮምፒውተር፣ ፀሀፊ፣ ስራ አስኪያጅ ወ.ዘ.ተ አላቸው? ደሞዝ ለመክፈል ብቻ የሚሰበሰቡ  ናቸው አብዛኞቹ፤ በተወሰነ መልኩ ፋሲል ይሻላል የተደራጀ ቢሮ አለው። ክለብ ተቋም ሲሆን ተቋም መኖሩ ደግሞ ስትራቴጂ እና ልማት ላይ ለመስራት ያስችላል” በማለት የመሰረታዊ ነገሮች ጉድለት እንዴት ጎሎቶ እይደሚታይ ይጠቅሳሉ።

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር ሌላኛው የሚነሳው ጉዳይ እግር ኳስ ክለቦች ለምን በራሳቸው በሚያመነጩት ገንዘብ አይተዳደሩም የሚል ነው። ይሄ ጥያቄ ሲነሳም እግር ኳስ ክለቦች ወደቢዝነስ መሰማራት እንዳይችሉ ህጉ ይገድባቸዋል የሚል ሀሳብ ይነሳል፤ ሆኖም ግን ህጉ ይህን እንደማይከለክል ዶ/ር ጋሻው ይገልፃሉ። “በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ክለቦች የመንግስት አልነበሩም። በንጉሱ ጊዜ በግል ተቋማት የተመሰረቱ ነበሩ፤  ሌሎቹ ደግሞ ስፖርቱን ለማበረታት በመንግስት በኩል አየር መንገድ፣ ምድር ባቡር፣  መብራት ሀይል  እያለ የመጣው እነዛ ተቋማት አትራፊ ስለነበሩ እና ከንግዱ ጋር ተቀራራቢ ስራ ስለሚሰሩ ነው” ካሉ በኋላ በደርግ ዘመን ያለው የመንግስት ስርአት ክለቦቹን ሙሉበሙሉ በመንግስት ስር እንዲገቡ እንዳደረጋቸው እና ይሄ ደግሞ ‘ ክለቦች የግል አይሆኑም’ የሚለውን እይታ አሁን ድረስ እንደፈጠረ ይናገራሉ።

አሁን በተሻሻለው ፖሊሲም ሆነ ከዚህ ቀደም በነበረው የስፖርት ፖሊሲ የክለቦች ባለቤት ህዝብ ነው የሚል ፅሁፍ እንደተቀመጠ በመግለፅም “ክለቦች  ንግድ ፈቃድ ላውጣ ቢሉ ችግር የለውም። በአንድ ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያወጣ ሲንቀሳቀስ ነበር ግን ‘ስፖርት ክለብ’ በሚል ነበር ማውጣት የፈለገው የትኛውም አለም ላይ እንደዚህ የለም። ቢዝነስህ ምንድነው ነው ተብሎ ተጠይቆ በዛ መሰረት ነው ንግድ ፈቃድ የሚወጣው። ለምሳሌ አንደኛ ስፖንሰርሺፕ ፣ሁለተኛ ትኬት ሽያጭ፣ ሶስተኛ የክለቡ አርማ ያረፈባቸው ቁሳቁሶች፣ አራተኛ ደግሞ  ከመገናኛ ብዙሀን ዙሪያ ሊሆን ይችላል። እነአርሰናል እኮ ሆስፒታል አላቸው። ሁሉም እነዚህ ዝርዝር ቢዝነሶች ታዲያ የራሳቸው የሆነ የንግድ ፈቃድ ላይ ቁጥር አላቸው” ሲሉም ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት ቢዝነሱን ጥንቅቅ አድርጎ ሚያውቅ ባለሙያ አለመኖሩ እግር ኳስም ሆነ ሌላ ስፖርት ትርፋማ እንዳይሆን እንዳደረገው ይገልፃሉ። ሌላው ደግሞ በቆይታችን ከቢዝነሱ አንፃር በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረው ሀሳብም ታላቁ ሩጫን እንደምሳሌ በማድረግ ነበር። ” ታላቁ ሩጫ በአንድ ቀን ዝግጅት በርካታ ሚሊዮን ብሮች እየሰራ አመቱን ሙሉ የሚካሄደው  የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ገንዘብ መስራት አለመቻሉ ዘርፉ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያመላክታል” ይላሉ።

ስፖንሰርሺፕን በተመለከተም በክለቦች እና በተቋማት መካከል የሚደረግ ስምምነት እንደተቋማቱ ልግስና እንደሚታይ እና ተቋሙ ከስምምነቱ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ሚሆንበት መንገድ በዝርዝር አለመዘጋጀቱም በቆይታችን የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ነው። የስፖንሰርሺፕን አስፈላጊነት ሲያነሱም በአለም ላይ ባሉ የእግር ኳስ ክለቦች በተለይም በሰለጠነው አለም ላይ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የገቢ ምንጭ እንደሆነም አስረድተዋል። በቀዳሚነት የገቢ ምንጭ የሚጠቀሰው ከጨዋታ ቀጥታ ስርጭት( ስትሪሚንግ) የሚገኝ ገቢም እንዲሁ በትኩረት ከተሰራበት ከፍተኛ የእይታ ፍላጎት ከመኖሩ አንፃር ነገሮችን እንደሚለውጥ ያምናሉ። በተለይም የአሜሪካን ፉትቦል ሊግ ( NFL) ልምድን ሲያነሱ “ስትሪሚንግ ካምፓኒዎች ሲመጡ የNFL ብሮድካስቲንግ ስምምነት ከ6 ቢሊየን ወደ 10 ቢሊየን አድጓል። ይሄ የአንዳንድ ሀገራት የግማሽ አመት በጀት ሊሆን ይችላል” በማለት ዘርፉ ሚያንቀሳቅሰውን ከፍተኛ ገንዘብ አስረድተዋል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ ምን አይነት መፍትሄ መውሰድ ይገባል በሚለው ላይ የትኛውንም አይነት እርምጃ ሲታሰብ እና ተግባር ላይ ሲውል ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን እና ሌሎችም ነባራዊ ሁኔታዎች ከግንዛቤ መግባት አለባቸው የሚለውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ክለቦችን ባለቤትነትን በተመለከተም የ140 ሀገራትን ልምድ በጥናታቸው እንደቃኙ በመግለፅ “ባየርመኒክን ብንወስድ አዲዳስ እና መርቼዲስን ትልቅ የክለቡ አጋር ተደርገው ሚወሰዱት ለረጅም አመታት የክለቡ ደጋፊ ሆነው ስለቆዩ ያላቸው የባለቤትነት ድርሻ ትልቅ እንዲሆን ተፈቀደላቸው” የሚለውን ምሳሌ ካነሱ በኋላ በሊጉ ጥናት ስር ምክረ- ሀሳብ ላይ የተቀመጠውን የመፍትሄ ሀሳብ ማብራራታቸውን ሲቀጥሉ ” መንግስትን ዝም ብለህ ውጣ አይባልም። ስፖርቱን ለረጅም ጊዜ ደግፏል፤ ስለዚህ የማህበረሰብ ይሁን ሲባል ሶስት ድርሻ አለ።   30- መንግስት 40- ህዝብ 30- የተመዘገበ ደጋፊ የተመዘገበ ደጋፊ” በማለት ገልፀዋል። የ30% ቦታ የተመዘገበ ደጋፊ የተባለበት ምክንያትም እስከዛሬ ክለቡን ያቆመ ደጋፊ ከሌላው ህዝብ( ከሰፊው ደጋፊ) በተለየ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ስለሆነ በማስረዳት ከሶስቱም ባለድርሻ አካላት ሰዎች ቦርድ ላይ አስቀምጦ ውሳኔዎችን መምራት እንደሚቻል አብራርተዋል።

በመጨረሻም አሁን ላይ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር የተወለዱ የዘር ሀረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዝ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን ለመጠቀም እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ደረጃዎች ላይ እንደደረሰ በተለያዩ አጋጣሚዎች መገለፁን ተከትሎ ይሄ የብሄራዊ ቡድናችንን እድገት ምን ያህል ይቀይረዋል ብለው ያምናሉ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ቁጥራዊ መረጃዎችን በማጣቀስ “ኮንጎ 79%፣ አልጄሪያ 57% ፣ቱኒዚያ 43% ፣ሴኒጋል 43%፣ ማሊ 29% የሚሆኑ ተጫዋቾች ከውጭ ሀገር የመጡ ናቸው” እያሉ የሌሎችንም ሀገራት የውጭ ተጫዋቾች ምጣኔ በማንሳት እንቅስቃሴው ውጤታማ የመሆኑ እድል ሰፊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.