በለንደን ማራቶን የማይቻል የሚመስለው ሆኗል!
በ2026 የለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ታሪክ የፃፉበት ውድድር ተካሂዷል።

በወንዶቹ ውድድር ኬንያዊው ሳባስትያን ሳዌ በአንደኛ ደረጃ ሲያጠናቅቅ ውድድሩን ለመጨረስ የወሰደበት ጊዜ ከ2 ሰአት በታች 1:59:30 መሆኑ ደግሞ በይፋዊ ውድድሮች ታሪክ የተመዘገበ ሪኮርድ ፈጣን ሰአት እንዲሆን አድርጎታል።


ከሰባስትያን 1:59:30 አስደናቂ ድል በተጨማሪ የመጀመሪያ ማራቶኑን የሮጠው ዮሚፍ ቀጀልቻም እንዲሁ ከ2 ሰአት በታች 1:59:41 በመግባት እሱም እንዲሁ ከዚህ በፊት ያልተፈፀመውን በማድረግ ባለታሪክ መሆን የቻለበትን አጋጣሚ መፍጠር ችሏል። በዚህ ሳያበቃም ኡጋንዳዊው ኪፕሊሞ 2:00:28 መግባቱን ተከትሎ ይሄ ሰአቱ ከዚህ ቀደም 2:00:35 በመግባት ኬሊቪን ኪፕቱም ይዞት የነበረውን ሪኮርድ ካሻሻሉት ሶስት አትሌቶች መሀል እንዲሆን አድርጎታል። ኬንያዊው አትሌት ኪፕቱም ሀገሩ ብዙ የእሱን ድሎች እየጠበቀች ባለችበት ሰአት በመኪና አደጋ ህይወቱ ማለፉ አይዘነጋም። አሁን ላይም ታዲያ ሶስቱ አትሌቶች የማራቶኑን ከ1-3 ያለውን ፈጣን ሰአት መቆናጠጥ ችለዋል።

ከሁለት ሰዓት በታች ማራቶንን ማጠናቀቅ በሩጫው ዓለም እንደ ትልቅ ህልም የሚታይ ግብ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ በ2017 እና 2019 ይህንን ለማሳካት ሁለት ሙከራዎችን አድርጎ በቪየና በተካሄደው ሁለተኛ ሙከራ 1፡59፡40 በመግባት ተሳክቶለት ነበር። ነገር ግን እነዚያ ውድድሮች በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሕግጋት መሠረት እንደ ይፋዊ የዓለም ክብረ ወሰን ሊመዘገቡ አልቻሉም፤ ምክንያቱም ኪፕቾጌን በየተራ እየተቀያየሩ የሚረዱት (pacemakers) አትሌቶች የታከሉበት በመሆኑ ነው።
ሳዌ እስከ 25 ኪሎ ሜትር ድረስ አሯሯጮች (pacers) የነበሩት ቢሆንም፣ አሯሯጮቹ ከወጡ በኋላ ግን በበለጠ ፍጥነት ሮጧል። የመጀመሪያውን ግማሽ ማራቶን በ60፡29፣ ሁለተኛውን ደግሞ በ59፡01 አጠናቋል ። ይህም በማራቶን ታሪክ ፈጣኑ የሁለተኛ አጋማሽ ሩጫ ሆኗል። ቀደም ሲል ፈጣኑ የነበረው ኬልቪን ኪፕቱም በ2023 ለንደን ማራቶን ያስመዘገበው 59፡45 ነበር ። በአጠቃላይ የመጨረሻውን 12.195 ኪሎ ሜትር በየማይሉ በአማካይ በ4፡24.3 ፍጥነት (በ1፡55፡30 የማራቶን ፍጥነት) ሮጧል።

ሳዌ ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ (BBC) በሰጠው አስተያየት “በጣም ደስተኛ ነኝ። ለእኔ የማይረሳ ቀን ነው” ብሏል። አክሎም “ወደ ውድድሩ ማብቂያ አካባቢ ብርታት ይሰማኝ ነበር፤ ኢትዮጵያዊው ተፎካካሪዬ (ዮሚፍ) በጣም ጠንካራ ነበር፣ እሱም ብዙ እንደረዳኝ አስባለሁ። በመጨረሻም የፍጻሜውን መስመር ስረግጥ ሰዓቱን አየሁ፤ ዛሬ የዓለም ክብረ ወሰን በመስበሬ በጣም ተደስቻለሁ። የዛሬው ውጤት ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ያሳየኛል፤ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
የሳዌ ክብረ ወሰን ሌላው ትኩረት የሚስብበት ምክንያት፣ ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት በራሱ ፍቃድ በ’Athletics Integrity Unit’ ጥብቅ የዶፒንግ ምርመራ ሲያደርግ በመቆየቱ ነው። ለዚህም ስፖንሰሩ አዲዳስ (adidas) ለተጨማሪ ምርመራዎች በዓመት 50,000 ዶላር ወጪ ሲያደርግ ቆይቷል።

የውድድሩ ሌላኛው ክስተት የግማሽ ማራቶን ባለሪኮርዱ ዮሚፍ ቀጀልቻ ሲሆን በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩ ከ2 ሰአት በታች ገብቶ ማጠናቀቁ አለምን አስገርሟል። ዮሚፍ በትላልቅ ውድድሮች ላይ አስደናቂ ብቃት እያሳየ ግን ደግሞ የሚያሳየውን አስደናቂ ብቃት የሚሸፍኑ ሌሎች ከሱ በጥቂት ላቅ ያሉ አትሌቶች እያሸነፉ በተደጋጋኒ ጊዜ ሁለተኛ እየወጣ መቀጠሉ ምናልባትም ስለእሱ ብዙ እንዳይወራ ምክንያት የሆነ ይመስላል። በተለያዩ ርቀቶች የኢትዮጵያ ክብረ-ወሰንን እያሻለለ ግን ደግሞ አሸናፊ ሳይሆን ሁለተኛ ሲወጣ ይሄ ቢያንስ ለ4ተኛ ጊዜ ነው። አንዳንድ አለም አቀፍ ፀሀፊያን እንደውም ” Mr. Silver” የሚለው ተቀፅላ ለዮሚፍ ይገባዋል በማለት ሲፅፉም ይታያል። አትሌቱ በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩ ይሄን ማድረግ መቻሉ ቀጣይ ውድድሮቹን ተጠባቂ አድርጓቸዋል።

በሴቶቹ ደግሞ ታሸንፍ ይሆን ወይ? ሳይሆን ሪኮርድ ትሰብር ይሆን ወይ? በሚል ስትጠበቅ የነበረችው ትግስት አሰፋ እንደተጠበቀው የራሷን የሴቶች ብቻ የማራቶን ሪኮርድ ዳግም በማሻሻል አሸንፋለች። ከውድድሩ አስቀድሞ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዘንድሮ ልምምዷ ከአምናም የተሻለም እንደሆነ እና የተሻለ ውጤት እንደምትጠብቅ ማንሳቷ የሚታወስ ሲሆን በለንደን ጎዳናዎች ያሳየችውም ይህንኑ ነው።
ትግስት አሰፋ 2:15:41 ስትገባ ብርቱ ተፎካካሪዎቿ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት ኬንያዊያኑ ሄለን ኦብሪ እና ብሪጅ ጄፕኮስጊ ደግሞ 2:15:53 እንዲሁም 2:15:55 በሆነ ሰአት ተከታትለው ገብተዋል። ሁለቱም አትሌቶች ለኬንያ የሴቶች ብቻ ማራቶን ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ ችለዋል።

በሁለቱም ፆታ በነበረ ውድድር በ2003 2:15:25 በመግባት ፓውላ ራድክሊፍ በዚያው በለንደን የያዘችው የቦታው ሪኮርድ ግን አሁንም ሳይሰበር ቀጥሏል። ትግስት ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገችው ቆይታ “የአለም ሪኮርድ እንደሰበርኩ ሳውቅ ጮህኩኝ። ዛሬ ጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ ነበርኩ እንዲሁም ደግሞ በልምምድ ወቅት ፍጥነቴ ላይ ይበልጥ ሰርቻለሁ። በመጨረሻም ጠንካራው ልምምዴ ዋጋ ከፍሎኛል። ፈጣሪዬን እንዲሁም በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፉትን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ። አብዛኞቹ ጓደኞቼ ናቸው እናም ጥሩ ስራ ሰርተዋል” ብላለች።

የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ማለትም የትግስት እና የዮሚፍ አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎም በአትሌቲክስ አፍቃሪያን ዘንድ አሸናፊ አትሌቶችን ደጋግሞ ማብቃት በመቻሉ እየተመሰገነ ይገኛል። ገመዶ ከቅርብ ጊዜ በማራቶን የሚያሰልጥናቸው አትሌቶች በተለያዩ ቦታዎች በሚዘጋጁ ውድድሮች በአስደናቂ ብቃት ባለድል እየሆኑ እንዳለ ይታወቃል።
