ትራምፕ የተሸለሙበት የአለም ዋንጫ ምድብ ድልድል ትላንት ተካሄደ!
የ2026 የአለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት አካቶ ከሰኔ 4 እስከ ሀምሌ 12 2018 አ.ም ድረስ እንደሚደረግ ይታወቃል። ይህ አለም ዋንጫም 48 ሀገራት ከማስተናገዱ በላይ 3 ሀገራት በጣምራ የሚያዘጋጁት መሆኑ ለየት ያደርገዋል። ጨዋታዎችም በ16 የ3ቱ ሀገራት ከተሞች የሚደረጉ ሲሆን 11 የሚሆኑት በአሜሪካ ከተሞች ሲደረጉ የተቀሩት ሶስቱ በሜክሲኮ፣ ሁለቱ ደግሞ በካናዳ ይደረጋሉ።
በትላንተናው እለት ምሽት ላይም የቀድሞው የማንቺስተር ዩናይትድ ኮከብ ሪዮ ፈርዲናንድ የመራው የምድብ ድልድል ስነ-ስርአት የተካሄደ ሲሆን ከዚህ አስቀድሞ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፊፋ የሰላም ሽልማትን( FIFA Peace Prize) ሸልመዋል። ሽልማቱ ባሳለፍነው ወር የፊፋ ቦርድ ውሳኔ ሳይሰጥበት ተቋሙ በራሱ ተነሳሽነት ይፋ የተደረገ ሲሆን አላማውም ለአለማችን ሰላም እና አንድነት የሰሩ ሰዎችን እንሸልማለን የሚል ነው።
ይሄ ሽልማት ይፋ የተደረገበት ሰአት ኢንፋንቲኖ እና ትራምፕ ጥሩ ግኑኝነት በመሰረቱበት እና ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ የአለም የሰላም ኖቤል ሽልማትን ለመሸለም ባልተመረጡበት ወቅት ይፋ መደረጉ እና መሰጠቱንም ብዙዎች ነገሩን ከግኑኝነት ማጠናከሪያ አንፃር ማየታቸው አልቀረም። ፊፋ ምንም እንኳን ሽልማቱ እግር ኳስን የሚወዱ በአለም ያሉ ህዝቦችን ሁሉ ይወክላል ቢልም ባለ 8 ምክትል ፕሬዝዳንት እና 37 አባላት ያሉት ካውንስሉ በጉዳዩ ላይ አልተወያየበትም። ፕሬዝዳንቱም ከሽልማቱ በኋላ ” በኮንጎ፣ በፓኪስታን እና በህንድ የበርካቶችን ህይወት ታድገናል። አሁን ላይ አለማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በስርአት እየተመራች ነው። ይሄን የሰላም ሽልማት በህይወቴ ካገኘኋቸው ትልቅ ክብሮች አንዱ ነው። አንዳንድ ጦርነቶችን ሳይጀመሩ ጭምር ማቋረጥ ነበረብን” ብለዋል።
ከዚህ በመቀጠል የአለም ዋንጫው ምድብ ድልድል የተደረገ ሲሆን 48 ሀገራት በ12 ምድብ 4 4 ሀገራት ተደልድለዋል። እስካሁን 42 የአለም ዋንጫው ተሳታፊ ሀገራት የተለዩ ሲሆን 22 ሀገራት የሚሳተፉበት የ’ፕሌይ ኦፍ’ ጨዋታ ከተደረገ በኋላ ደግሞ ቀሪ ስድስቶቹ ተሳታፊዎች ይታወቃሉ። ከእያንዳንዱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡት ቀጥታ ወደ 32 ሀገራት ጥሎ ማለፍ ጨዋታ የሚያልፉ ሲሆን ቀሪ ስምንቱ ደግሞ ምርጥ 3ኛ ሆነው የ32 ሀገራት ጥሎ ማለፉን ይቀጥላሉ። በመቀጠልም የ16 ሀገራት ጥሎ ማለፍ፣ ሩብ ፍፃሜ፣ ግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። የምድብ ድልድሉ ከታች በምስሉ ላይ የምትመለከቱትን ይመስላል።

የአለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ሜክሲኮ ከ ደቡብ አፍሪካ በሚያደርጉት ጨዋታ በሀገረ ሜክሲኮ በስታድዮ አዝቴካ በሰኔ 4,2018 አ.ም ይደረጋል። ይሄ ጨዋታ ወደ 2010 አለም ዋንጫ መለስ የሚያርደርገን ሲሆን በዛን ጊዜሞ እንዲሁ የመክፈቻ ጨዋታው በደቡብ አፍሪካ እና በሜክሲኮ መሀል ተደርጎ 1-1 አቻ እንደተለያዩና ፒተር ዱሩሪ ” ሻባላላላላ፣ ጎል ባፋና ባፋና፣ ጎል ለደቡብ አፍሪካ፣ ጎል ለመላው አፍሪካ፣” ያለበት ኮሜንተሪ የሚዘነጋ አይደለም።

የአለም የእግር ኳስ ቤተሰብ ከአስር አመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሁለቱ የእግር ኳስ ክዋክብትን ሊዮነል ሜሲ እና ክሪስትያኖ ሮናልዶ የሚያገናኝ ጨዋታ በጉጉች የሚጠብቅ ሲሆን ሁለቱም ለአለም ዋንጫው ብቁ ሆነው የሚደርሱ ከሆነ ዘንድሮም እድል ያለ ይመስላል። አርጀንቲና እና ፖርቹጋል ምድባቸውን አሸንፈው 32 ሀገራት ወዳሉበት ጥሎ ማለፍ የሚገቡ ከሆነ እና እሱንም አልፈው 16 ውስጥ ከደረሱ እና ያንንም ካለፉ በ ሰኔ 11,2026 ሩብ ፍፃሜ ላይ በካንሳስ ሲቲ እንደሚገናኙ ይጠበቃል። የሁለቱ ሀገራት ታላላቅ የእግር ኳስ ጠበብቶች የሆኑት ሜሲ እና ሮናልዶም ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ እርስበእርስ የሚገናኙበት መድረክ ይሆናል።

የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ የሳበው ሌላኛው ጉዳይ አሁን ላይ ከፊት ሊጠቀሱ ሚችሉት የአለማችን ምርጥ አጥቂዎች ኪሊያን ምባፔ እና አርሊንግ ሀላንድ በምድብ 11 መገናኛታቸው ነው። ሀላንድ አሁን ላይ በሁሉም ውድድሮች በ24 ጨዋታዎች 33 ጎሎች ያስቆጠረ ሲሆን ምባፔም በተመሳሳይ 24 ጨዋታዎች 30 ጎሎች አሉት። ሁለቱ ተጫዋቾች ለአውሮፓ የወርቅ ጫማ እስከመጨረሻው እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

በዚህ አለም ዋንጫ ላይ ይኖራል ተብሎ ሚጠበቀው አዲሱ ነገር ልክ እንደ አሜሪካ የ’ Super bowl’ በጨዋታው አጋማሽ ላይ የሙዚቃ ድግስ እንዲኖር መደረጉ ነው።
አሜሪካ በዚህ አለም ዋንጫ 10 ሚሊዮን እንግዶችን የምታስተናግድ ሲሆን የቪዛ ጉዳይ ችግር እንዳይሆን ከፊፋ ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል። ይህም ለአሜሪካ ኢኮኖሚ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያመነጭ ይጠበቃል። 200,000 የስራ እድሎችም እንደሚፈጠሩ ከ’ Department of state’ ገፅ ላይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
