ለኤሌትሪክ መኪና ባለቤቶች ታላቅ ስጦታ ተበረከተ!
ኢትዮ ቴሌኮም ሦስተኛውን እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ ዛሬ በይፋ አስመርቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው እለት ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ ስራ ያስጀመረው ሦስተኛው ጣቢያ በአንድ ጊዜ 16 መኪኖችን የሚያስተናግድ እጅግ በጣም ፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ መሆኑን አሳውቋል።
ሰሚት ፍየል ቤት አካባቢ ስራ የጀመረው ሦስተኛው ጣቢያው እጅግ ፈጣን፤ ኃይል ቆጣቢ፣ ከፍተኛ ፍጥነት ያለውና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሰራ በመሆኑ፣ ባትሪዎች በሚችሉት ፍጥነት ዘላቂነት ባረጋገጠ መልክ ቻርጅ ያደርጋል በማለት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በሰፊው ማብራሪያ ተሰጥተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት አለሙ በሰጡት ማብራሪያ “ይህ ኢኒሼቲቭ፤ ሀገራችን በዲጂታል ጉዞ እያደረገች ያለውን ሁለገብ ለውጥ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት በኩል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያላትን ተምሳሌትነት ያሳየንበት ነው“ ብለዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ወይዘሪት ፍሬህይወት አለሙ አክለውም “በሀገራችን የኤሌክትሪክ መኪኖች በሰፊው እየተለመዱ መምጣታቸውን ተከትሎ ስነ-ምህዳሩንም በአረንጓዴ መሰረተ ልማት መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ፣ እነዚህን የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በአጭር ጊዜ ገንብተን ስራ ላይ እንዲውሉ አድርገናል” ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ሲል በአንድ ጊዜ 32 መኪኖችን ማስተናገድ የሚችሉ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ያስገባ ሲሆን፣ ከየካቲት 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ165 ሺህ የኤሌክትሪክ መኪኖች፣ 4,349,761.54 ኪሎዋት ኃይል መሙላት መቻሉንም ተገልጿል፡፡
ይህም 6,081,447.62 ኪ.ግ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ ማድረግ የቻለ ሲሆን፣ ከ30,444 በላይ ዛፎችን ከመትከል ጋር ይነጻጸራል በማለት ስራ ዋና አስፈጻሚዋ የገለጹ ሲሆን በተጨማሪም
ኩባንያው የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ በአረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ ለዘላቂ እድገት ቁልፍ ሚና መጫወቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡
✍ፈለቀ ደምሴ
