ኢትዮ ቴሌኮም እና አዋሽ ባንክ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ያለተያዥ የብድር አገልግሎት ሊሰጡ ነው!
አንጋፋዎቹ ኢትዮ ቴሌኮም እና አዋሽ ባንክ
በቴሌብር አማካኝነት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽነት እና አካታችነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸውን ህዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚዬም አዳራሽ ይፋ አድርገዋል።

ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር እና በአዋሽ ባንክ ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ በ16 ወራት የሚከፈል እስከ 1 ሚሊዮን ብር ብድር ያለተያዥ የሚያገኙበት አገልግሎት መጀመሩ በእለቱ ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከአዋሽ ባንክ ጋር በአጋርነት “ጥላ” የተሰኘ ያለዋስትና የዲጂታል ፋይናንስ እና የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎቶችን በቴሌብር በይፋ አስጀመርዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከአዋሽ ባንክ ጋር ከሚሰጡአቸው አገልግሎቶቹ ውስጥ የግለሰብ ደንበኞች፣ የተቋማት ሠራተኞች፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አነስተኛ ብድር እንዲያገኙ ያስችላሉ ተብሏል ፡፡

በተጨማሪም ከሚሰጡአቸው አገልግሎቶች አንዱ ደንበኞች በረጅም ጊዜ ክፍያ የስማርት ስልክ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አንዱ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።
በተጨማሪም በስማርት ስልኮች ዋጋ ከፍተኛ መሆን ምክንያት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የስልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
በዚህም የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ሳይሆን በቆየባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖረው ማህበረሰባችን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል ።
እንዲሁም ደንበኞች በቴሌብር ያለካርድ ከአዋሽ ባንክ ኤቲኤም (ATM) ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ከዚህም በተጨማሪም በቴሌብር ሱፐርአፕ የአዋሽ ባንክ ስኩል ፔይን በማካተት የትምህርት ቤት ክፍያዎችን ለመፈጸም የሚያስችል አሰራርም ተግባራዊ መሆኑን ይህም ለወላጆች ቀላልና የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በሁለቱ ታላላቅ ድርጅቶች በኢትዮ ቴሌኮም የበላይ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዋሽ ባንክ በሰፊው ማብራሪያ ተሰጥቶበታል ።
✍️ ፈለቀ ደምሴ
