የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በሞሮኮ በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሥም የተሰየመውን ስታዲየም ጎበኙ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በካሳብላንካ የሚገኘውና በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሥም የተሰየመውን ስታዲየም በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ባደረጉት ንግግር ይህ በይድነቃቸው ተሰማ የተሰየመው ስታዲየም ትልቅ ትርጉም ያለው እና ለቡድናቸው አባላት የሚያስተላልፈው ቁም ነገር ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል። የቡድኑ አባላትም የ30 ሰከንድ ጭብጨባ በማድረግ ለአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።

በስታዲየሙ መግቢያ ላይ ስለ ስታዲየሙ በፍሬንች እና አረብኛ ቋንቋዎች አጭር መግለጫ የተቀመጠ ሲሆን ” እ.ኤ.አ በ1988 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት በሞሮኮ ንጉሥ ሐሰን ዳግማዊ በተሰጠ መመርያ ይህ ስታዲየም ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ይድነቃቸው ተሰማ ሥም እንዲሰየም ማርች 1988 ላይ ተወስኗል። ” የሚል መግለጫን ይዟል።

ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ እግር ኳስ እድገት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አመዛኙ የህይወት ዘመናቸውን ባሳለፉበት እግር ኳስ በተጫዋችነት ፣ አሰልጣኝነት እና አመራርነት እ.ኤ.አ በ1987 ህልፈተ ሕይወታቸው እስከተሰማበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ አበርክቶ የነበራቸው ታላቅ የእግር ኳስ ሰው ነበሩ።

 

ምንጭ 👉የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published.