ካታሎናውያን ጮቤ የረገጡበት 249ኛው የኤልክላሲኮ ጨዋታ።
▪️29ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የስፔን ላሊጋ ምሽቱን ተጠባቂ የነበረውን የኤል-ክላሲኮ ጨዋታ አስተናግዷል። ሪያል ማድሪድ 120ኛ አመት የክለብ ምስረታውን ምክንያት በማድረግ በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቦ ጥቁር ማልያ ፣ ጥቁር ቁምጣ እንዲሁም ጥቁር ገምባሊያ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
▪️ብሉግራናዎቹም ቢሆን ባልተለመደ መልኩ በ3ኛ ማልያቸው ማለትም ሴንዬራ እየተባለ የሚጠራውን የካታላን ባህል እና ዘይቤ የተወሰደ ማልያ ማለትም ቢጫ ማልያ ፣ ቢጫ ቁምጣ እና ቢጫ ገምባሊያ በመልበስ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
▪️ጨዋታውን ኳስ በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ የነበሩት የዣቪ ቡድን ባርሴሎና የመጀመሪያውን ጎል ለማግኘት 28 ደቂቃዎች ብቻ ጠብቀዋል። ከዴምቤሌ የተሻገረለትን ኳስ ኦባምያንግ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ አደረገ።
▪️ካሪም ቤንዜማን በጉዳት ማሰለፍ ያልቻሉት ሎስ ብላንኮዎቹ በማጥቃቱ ረገድ በጣም ተዳክመው ታይተዋል። ቪኒሺየስ ጁኒየር 36ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ወርቃማ እድል መጠቀም አልቻለም። ባርሴሎናም 37ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የማዕዘን ምት የ23 አመቱ ኡራጋዊ ሮናልድ አራውሆ አስቆጥሮ የጎል ልዩነቱን ወደ 2 ከፍ አደረገ። የመጀመሪያው አጋማሽም በዚ መልኩ ተጠናቋል።
▪️ከእረፍት መልስ ካርሎ አንቼሎቲ ካማቪንጋ እና ማሪያኖ ዲያዝን በ ካርቫሀል እና ቶኒ ክሮስ ተክተው አስገብተዋል። ግን ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም ከእረፍት መልስ ገና ሁለት ደቂቃ ከመጫወታቸው ጋቦናዊው የቀድሞ የአርሰናል አጥቂ ኦባምያንግ አስደናቂ በሆነ መልኩ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ፌራን ቶሬስ ከመረብ በማዋሀድ 3ኛውን ጎል ለባርሴሎና አስገኘ።
▪️ይህ ግብ ከተቆጠረ በኋላ የማጥቃት ፣ ኳስን የመቆጣጠር ተነሳሽነታቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የወረደው ሪያል ማድሪዶች ሉካስ ቫስኬዝ እና ማርኮ አሴንሲዮን ተክተው ቢያስገቡም ኦባምያንግ ጎል ከማስቆጠር ወደኋላ እንዲል አላደረገውም ለራሱ 2ኛ ለቡድኑ 4ኛ የሆነች ድንቅ ግብ ኮርቱዋ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል። ኦባምያንግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈበት የኤልክላሲኮ ጨዋታ ላይ 2 ጎሎች እንዲሁም 1 ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በአጠቃላይ ለባርሴሎና ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
▪️በብሉግራናዎች ቁጥጥር ስር የነበረው እና የአንድ ቡድን የበላይነት የተንፀባረቀበት የኤል ክላሲኮ ጨዋታ በባርሴሎና 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተጠናቋል። ዣቪ በ134 ቀናት ውስጥ ቡድኑ ላይ የፈጠረው ለውጥ እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው። በአሰልጣኝነት የመጀመሪያ ኤል ክላሲኮ ጨዋታውንም በአሸናፊነት አጠናቋል።
ሚካኤል ደጀኔ