የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

▪️ቅዳሜ,ጥቅምት13
2 ጨዋታዎች ሲካሄዱ አዳማ ከነማ 20ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ባስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 አሸንፏል።አመሻሽ 12:00 ላይ ወላይታ ዲቻ ከ ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ ወላይታ ዲቻ ሀብታሙ ንጉሴ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።
▪️እሁድ እንዲሁ 2 ጨዋታዎች ሲከናወኑ አዲስአበባ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ ሲገናኙ ሁለቱ ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉ ክለቦች ጨዋታቸውን 8:00 አካሂደው አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ባስቆጠራቸው 2 ግቦች 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ቀጥሎም 12:00 ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
▪️ሰኞ ሀድያ ሆሳዕና ከ ባህርዳር ከተማ 9:00 ሲል ጨዋታቸውን አከናውነው ባህርዳር ከነማ የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በኦሴ ማውሊ ጎል አሸንፎ መውጣት ችሏል።ይህ ጨዋታ ከመጠናቀቁ በኋላ የጀመረው የወልቂጤ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ የአምናው ሻምፒዮን ፋሲል በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ግብ 3ነጥብ ይዞ ከሜዳ ወጥቷል።
▪️ዛሬ ሰበታ ከነማ ከመከላከያ  ጨዋታቸውን አከናውነው ነበር 9:00 ሲል በጀመረው ጨዋታ መከላከያ 1-0 ሲያሸንፍ ለዮሀንስ ሳህሌው ቡድን አቤል ነጋሽ የጎሏ ባለቤት ነው።
▪️12:00 ሲል የጀመረው እና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በቅ/ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል።የካሳዬ አራጌው ቡድን በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ጥሩ የነበረ ቢሆንም ሙከራ ማድረግ ላይ ቀዝቀዝ ብሎ አምሽቷል። በአንፃሩ ዋና አሰልጣኙን ሰርቢያዊ ዝላትኮ በቤተሰብ ምክንያት ሳይዝ ወደሜዳ የገቡት ፈረሰኞቹ ድንቅ እንቅሰቃሴ ሲያደርጉ እና በተደጋጋሚ ሙከራዎችንም በማድረግ ተጠምደው አምሽተዋል።ሙከራቸውም ፍሬ አፍርቶ በ ኢስማኤል ኦሮ ግብ ቀዳሚ ሆነው ለዕረፍት ወተዋል። ከእረፍት መልስ ቡልቻ ሆራ መሪነቱን ወደ 2 ያሰፋ ጎል አስቆጥሯል።ቡናማዎቹ ከእረፍት መልስ ከራስ ሜዳ በመውጣት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።በ59ደቂቃም በእንዳለ ደባልቄ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በነበረው አማካዩ ሀይደር ሸረፋ የ79 ደቂቃ ግብ ልዩነቱን እንደገና ሰፍቷል።ከዚህች ጎል በኋላ ተነሳሽነታቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የወረደው ቡናዎቹ 84 ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት አስተናግደዋል። ሀይደር ሸረፋም በምሽቱ ለራሱ 2ኛውን ለቡድኑ ደሞ አራተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው በ ጊዮርጊስ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
▪️የደረጃ ሰንጠረዡን ባህርዳር ከነማ ፣ፋሲል ከነማ ፣መከላከያ በእኩል 6 ነጥብ በ ግብ ተለያይተው ከ 1-3 ያለውን ደረጃ ሲይዙ ቅ/ጊዮርጊስ በ 4 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል። ወራጅ ቀጠናውን ጅማ አባ ጅፋር፣ሀድያ ሆሳዕና ፣ አዲስአበባ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ምንም ነጥብ ሳይኖራቸው የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።

ሚካኤል ደጀኔ።

Michael dejene

Michael dejene Bsc in computer science Born in october 12,1998 Age 23 Editor of ethiopianssport.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.