” ሴኒጋሎች ጉዳዩን ወደ ስፖርት ግልግል ከወሰዱት ውሳኔው ይቀለበሳል”- የህግ ‘ ኤክስፐርት’

ለሊቱን የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ የ2026 የአፍሪካ ዋንጫን ከሴኒጋል በመነጠቅ ለሞሮኮ እንዲሰጥ የሚያዝ ውሳኔ እንዳሳለፈ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ካፍ ሴኒጋል ዋንጫውን መነጠቅ አለባት የሚል ውሳኔ ላይ የደረስኩት በመተዳደሪያ ደንባችን ላይ ያለው አንቀፅ 82 በመጣሱ ነው ሲል አስቀምጧል። አንቀፅ 82 የትኛውም ቡድን ያለዳኛ ፈቃድ ከሜዳ እንዳይወጣ የሚደነግግ ሲሆን ይሄን ተላልፎ የተገኘ ቡድን በሌላኛው በአንቀፅ 84 ላይ በተቀመጠው መሰረት የ3 ለ0 ፎርፌ እንዲሰጥበት ያዛል።

ሴኒጋሎች ጎል ከተሻረባቸው በኋላ ሞሮኮዎች ፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ ውሳኔው ተገቢው አደለም ብለው በማመናቸው በአሰልጣኛቸው መሪነት ወደመልበሻ ክፍል አምርተው እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም ግን ጨዋታው በዛው ተቋርጦ ሳይቀር ተመልሰው መቀጠላቸው እና ሴኒጋሎች ባለድል መሆናቸው ይታወሳል። ካፍም ይሄ ከሆነ ከወራት በኋላ ጉዳዩን መርምሬ ድሉን ለሞሮኮ ሰጥቻለሁ ሲል አሳውቋል።

የካፍ ውሳኔ ትክክል ነው?

በአፍሪካ በስፖርት ህግ ዘርፍ ከሚጠቀሱት ጥቂት ምሁራን መሀል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ስሙ የሚነሳው ፒውስ ንዱቦኩው ለSABC በሰጠው አስተያየት የካፍ ውሳኔ የራሱን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰ እና ተገቢ ያልሆነ ነው ብሏል። ንዱቦኩው እንደሚለው ከሆነ አንቀፅ 82 እና 84 በካፍ በአግባቡ አልተተረጎሙም። የአንድ ቡድን ጉዳይ በአንቀፅ 82 የሚታየው ቡድኑ ጨዋታውን አቋርጦ ወጥቶ በዛው ከቀረ እንጂ ተመልሶ የቀጠለ ጨዋታ ላይ ተግባራዊ መሆን አይችልም ሲልም ያስቀምጣል።

ለዚህም እንደማሳያ የ2019 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ ኤስፐራንስ ዴ ቱኒዝ ከ ዋይዳድ ጋር እየተጫወቱ ባለበት ሰአት ዋይዳዶች በመልሱ ጨዋታ በ59ኛው ደቂቃ ከ1 ለ 0 ተመሪነት ወደ አቻ ውጤት የሚወስዳቸውን ጎል ሲያስቆጥሩ ከጨዋታ ውጭ በሚል ዳኛው መሻራቸውና ቫር በወቅቱ በስራ ላይ አልነበረም ብለው ውሳኔያቸውን ማፅናታቸው ዋይዳዶችን በተቃውሞ ከሜዳ እንዲወጡ የሆነበትን አጋጣሚ አንስቷል። በዚህ ጨዋታም ዋይዳዶች ተመልሰው ጨዋታውን ባለመቀጠላቸው በአንቀፅ 82 መሰረት 3 ለ 0 ፎርፌ ተሰጥቶባቸው ዋንጫው ለኤስፔራንስ ተሰጥቶ እንደነበር የሚያብራራው ንዱቦኮው በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ላይ ግን ተጫዋቾቹ ወደሜዳ በመመለሳቸው ይህ ህግ ተግባራዊ መሆን አይችልም ይላል።

ንዱቦኮው ሀሳቡን ሲደመድምም ሴኒጋሎች ጉዳዩን ወደአለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድቤት( CAS) ከወሰዱት የካፍ ውሳኔ የመቀልበሱ ነገር ሰፊ ነው ብሏል።

በስተመጨረሻም ካፍ ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት አወዛጋቢ ጉዳዮችን ህጋዊ መሰረቱን በተከተለ አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት በተቋሙ ውስጥ ያሉት የህግ ሰዎች ከአጠቃላይ የህግ ትምህርት በዘለለ ከስፖርት ህግ ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን በአግባቡ ሊወስዱ ይገባል ብሏል።

ከውሳኔው በኋላ የተሰጡ ግብረመልሶች?

ሴኒጋሎች ፈፅሞ ውሳኔውን እንደማይቀበሉት ያሳወቁ ሲሆን ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ ስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት እንደሚወስዱትም አስታውቀዋል። አንዳንድ ተጫዋቾቻቸውም በማህበራዊ ድረ-ገፆቻቸው ላይ የስላቅ መልእክቶችን ሲያስተላልፉ ተስተውሏል።

ከ58 ቀናት በኋላ የተወሰነው ይህ ውሳኔ በቀጣይ በCAS ይቀለበሳል ወይስ እንደፀና ይቀጥላል የሚለውን የምንመለከተው ይሆናል።

✍️ ዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.