ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ በኒውዮርክ ማራቶን ይገናኛሉ!

በእግር ኳስ የሁለት ሰዎችን የረጅም ጊዜ ፉክክር ካነሳን ክሪሰትያኖ እና ሊዮነል ሜሲ ቀድመው አእምሮሯችን ላይ እንደሚመጡት ሁሉ በአትሌቲክስ የረጅም ርቀት ታሪክ ከትራክ እስከ ጎዳና የዘለቀ ተፎካካሪነትን ያሳዩን ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ በኒውዮርክ ማራቶን ይፎካከራሉ።

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የኒውዮርክ ማራቶን ነገ የሚደረግ ሳይሆን ለ55ኛ ጊዜ በሚካሄደው ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ ግምት አግኝተዋል፡፡

ነገ በሚደረገው የኒው ዮርክ ማራቶን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከኬንያዊው ኢልዩድ ኪፕቾጌ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ የሚጠበቅ ሲሆን በማራቶን ታሪክ 3ኛው ምርጥ ሰዓት ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ ዛሬም ለሌላ ፈተና ራሱን አዘጋጅቷል፡፡ በ2019 በርሊን ማራቶን የገባበት 2 ሰዓት 01.41 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው፡፡

43ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ቀነኒሳ በ2025 ምንም አይነት ሩጫ ያላደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተወዳደረበት የለንደን ማራቶን 2ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ አትሌት ቀቀኒሳ በቀለ ሀገሩን በወከለበት ፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ከኪፕቾጌ ጋር ሮጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በመኪና አደጋ ህይወቱ ካለፈው የሀገሩ ልጅ ኬልቪን ኪፕቱም በመቀጠል በማራቶን 2ኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ኢልዩድ ኪፕቾጌ በኒው ዩርክ ማራተቶን ለመጀመርያ ጊዜ ይወዳዳራል፡፡ ትላልቅ ማራቶኖችን በማሸነፍ የሚስተካከለው የሌለው ኬንያዊው አትሌት 2 ሰዓት 01.09 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው፡፡

የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ኪፕቾጌ 11 ትላልቅ ማራቶኖችን አሸንፏል፡፡ የ40 ዓመቱ አትሌት ለ12ኛ ጊዜ ለማሸነፍ በሚወዳደርበት መድረክ ከሀገር አቋራጭ ኮከብ ከነበረው ቀነኒሳ በቀለ ጋር ትልቅ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ከሁለቱ ስመ ጥር አትሌቶች በተጨማሪ የቦስተን፣ ቺካጎ እና ቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ቤንሶን ኪፕሩቶ እንዲሁም የለንደን ማራቶን አሸናፊው አሌክሳንደር ሙቲሶ ሌሎች ጠንካራ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡

በሴቶች አትሌት ጎቲቶም ገ/ ስላሴ ትጠበቃለች፡፡ የ2022 ኢዩጂን ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ ጎቲቶም በውድድሩ ከሚሳተፉት አትሌቶች 5ኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት፡፡

2 ሰዓት 18.11 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት የሆነችው ጎቲቶም ገ/ስላሴ ከኬንያውያን እና ከሌሎች አትሌቶች ጋር ትልቅ ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡ የኒው ዮርክ ማራቶንን በሴቶች ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችው አትሌት ፍሬህይዎት ዳዶ ከ14 ዓመት በፊት እነንደነበር ይታወሳል፡፡

ኒዘርላንዳዊቷ ሴፈን ሀሰን ትልቅ ግምት አግኝታለች፡፡ የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ሲፈን ፊቷን ወደ ማራቶን ካዞረች በኋላ ስኬታማ መሆኗን አሳይታለች፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለንደን፣ ሲድኒ እና ቺካጎ ማራቶኖችንም አሸንፋለች፡፡

የ2025 የኒውዮርክ ማራቶን ከወዲሁም የበርካቶችን ትኩረት ስቧል

Leave a Reply

Your email address will not be published.