” ከአለም ዋንጫ አሸናፊነት በላይ ልትጠይቀው ምትችለው ነገር የለም”- ሊዮነል ሜሲ
ሊዮነል ሜሲ በትላንትናው እለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ሌሎች የትላልቅ ድርጅቶች መሪዎች እና የተለያዩ ስፖርታዊ ተቋማት አመራሮች በተገኙበት የአሜሪካ ቢዚነስ ፎረም ተካፍሎ ነበር። ፎረሙ በማያሚ የተካሄደ ሲሆን በርካታ የቢዝነስ ሰዎች ተሳትፈውበታል። ሊዮነል ሜሲ ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

ሜሲ አለም ዋንጫን ተያይዞ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስም ” አለም ዋንጫን ማሸነፍ ትልቅ ስኬት ነው። ከአለም ዋንጫ ድል በኋላ ሌላ የምትጠይቁት ተጨማሪ ነገር የለም። የዛን ጊዜ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ከባድ ነው።በግሌ፣ እንደቤተሰብ፣ ለቡድን ጓደኞቼ እና ለሀገሬ ምን ማለት እንደሆነ ለኔ መግለፅ ከባድ ነው።ሀገሬው በሙሉ ደስታውን የገለፀበት መንገድ የሚዘነጋ አይደለም። ሁላችንም ከረጅም ጊዜ በኋላ ይሄ እንዲሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን።ከዛ በፊት በክለብ ደረጃ እና በግሌ ሁሉንም ነገሮች በማሳካቴ እድለኛ ነበርኩ። አንድ ነገር ብቻ ነበር የቀረኝ። ይሄ ዋንጫም የእግር ኳስ ዘመኔን ሙሉ አድርጎታል” ሲል መልሷል።

በሌላ በኩል አለም ዋንጫ ሲያሸንፍ የተሰማውን ስሜት ልክ ልጆቹ ሲወለዱ ከተሰማው ስሜት ጋር ተመሳሳይ እንደነበር መለስ ብሎ አስታውሷል። “በስፖርቱ ሁሉንም ነገር አሳክቻለሁ የሚለው ስሜት በአእምሮዬ ውስጥ መኖሩም በብዙ መልኩ ቀይሮኛል” ሲልም ሀሳሱን ያክላል።

ከዚህ በተጨማሪም ” ፈጣሪ መርጦኝ ስጦታ ሰጥቶኛል። ከልጅነቴ ጀምሮ ከተሰጥኦ ጋር ነው ያደኩት፤ ግን ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት መክፈል ግድ ብሎኛል። ፕሮፌሽናል ለመሆን ትልቅ መስዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል፤ እናም ያንን አላማዬ አድርጌ ተነስቻለሁ። መጀመሪያ ላይ እንዳልኩት ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ ምክንያቱም እጅግ ጠቃሚ ነገር ሰጥቶኛል” ብሏል።

በፎረሙ ዶናልድ ትራምፕ፣ ሴሪና ዊሊያምስ፣ ራፍየል ናዳል፣ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ኤሪክ ሽሚት( የቀድሞ የጎግል ስራ አስኪያጅ)፣ ቶኒ ሮቢንስ( የአመራር እና ቢዝነስ ስትራቴጂስት)፣ ኬን ግሪፍን( የሲታዲል መስራች እና አስኪያጅ) እና ሌሎችም እውቅ የቢዝነስ ሰዎች ተገኝተዋል።
