ትግስት አሰፋ በለንደን ሪኮርድ ትሰብር ይሆን?

የትኛውም የማራቶን ውድድር የ2024 የፓሪስ የኦሎምፒክ እንዲሁም የ2025 የቶክዮ አለም ሻምፒዮና አሸናፊዎቹን አሳትፋለሁ ካለ በኋላ አትሌቶቹን በጉዳት ካጣ ተጠባቂነቱ እንደሚቀንስ እሙን ቢሆንም ይሄ የለንደን ማራቶን ስለሆነ የክዋክብት እጥረት የለበትምና አሁንም በሁለቱም ፆታዎች የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች በጉጉት ይጠበቃሉ።

የ2026 የለንደን ማራቶን የፊታችን እሁድ የሚካሄድ ሲሆን በወንዶቹም ሆነ በሴቶቹ ተጠባቂ አትሌቶች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ለንደን ከትመዋል።

በወንዶቹ ዘርፍ የአምናው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሳባስትያን ሳዌ፣ የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩን የሚያደርገው ዮሚፍ ቀጀልቻ እንዲሁም አምና በመጀመሪያ  የማራቶን ውድድሩ 2ኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀው የቶክዮ ኦሎምፒክ የወንዶች 10,000 ሜትር አሸናፊ ጃኮብ ኪፕሊሞ እና ጀርመናዊው አማኑኤል ጴጥሮስ ተጠባቂ ናቸው።

ጃኮብ ኪፕሊሞ መጀመሪያ የለንደን ማራቶንን አምና ሲሮጥ አላማው የመጨረሻውን መስመር ማለፍ እንደሆነ ገልፆ ባገኘው የሁለተኝነት ውጤት እንደተደሰተ ያነሳል። ከዛ በኋላ በተሳተፈበት የቺካጎ ማራቶን ያሸነፈው አትሌቱ ” ወደማራቶን መምጣት ብዙ ስራ ይጠይቃል። ቀላል አይደለም” ሲል ይናገራል።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በ2025 በቶክዮ ከተካሄደው የአለም ሻምፒዮና ላይ የብር ሜዳሊያ ካሳካ በኋላ ከትራክ ወደ ጎዳና ውድድሮች እንደሚሸጋገር መግለፁ አይዘነጋም። ዮሚፍ የጎዳና ላይ ውድድር ጉዞውን የጀመረውም ጥቅምት ላይ የቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶንን በመሮጥ ሲሆን በዛ ውድድር ላይ ከማሸነፉ በተጨማሪ 57:30 በመግባት የርቀቱን ሪኮርድ ማሻሻሉ አይዘነጋም። የፊታችን እሁድ ደግሞ የመጀመሪያ ማራቶኑን ብርቱ ተፎካካሪዎች በሚገኙበት የለንደን ማራቶን ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ሌላኛው የመጀመሪያ ማራቶኑን የሚሮጠው ደግሞ በ5000 ሜትር የአለም ሁለተኛ ፈጣን ሰአት ያለው ሀጎስ ገ/ህይወት ነው። ሀጎስ በ2023 የቫሌንሺያን ግማሽ ማራቶን 57:41 በመግባት ማጠናቀቅ ችሎ እንደነበር አይዘነጋም።

በሴቶቹ ምድብ ስንመጣ ደግሞ ከውድድሩ አስቀድሞ ድምቀት ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ አሸናፊዋ ሲፋን ሀሰን እና የ2025 የቶክዮ የአለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ ፔሬስ ጄፕቼርቼር በጉዳት ራሳቸውን ማግለላቸው መገለፁ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የአምና የውድድሩ አሸናፊ ትግስት አሰፋ ፣ የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ሄለን ኦብሪ  እንዲሁም የ2025 ፈጣኗ ሴት ጆይክላይን ጄፕኮስጊ የሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር ይጠበቃል።

የሩጫ ህይወቷን በአጫጭር ርቀቶች የጀመረችው ትግስት በጉዳት ከውድድር ከራቀች በኋላ በ2022 በበርሊን ማራቶን ሪኮርድ በሆነ ሰአት በመግባት ስታሸንፍ የአለም የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪያን ትኩረትን መሴብ ችላ ነበር። ትግሰት ከዛ በኋላ ባሉት አመታት በርቀቱ ወጥ የሆነ ብቃት ከሚያሳዩ አትሌቶች መሀከል የተካተተችበትን ውጤት ማስመዝገብም ችላለች። ከበርሊኑ ማራቶን አንስቶ በሮጠቻቸው 6 ማራቶኖችም ሶስቱን ማሸነፍ መቻሏ ጥሩ አፈፃፀም እንዳላት የሚያሳይ ቁጥራዊ መረጃ ሆኖ እናገኘዋለን። አምና 2:15:50 በመሮጥ በለንደን ባለድል የነበረችው ትግስት ለዳግም ድል ስትፋለም ” በዚህኛው ሩጫ ከአምናው የተሻለ እንደምሮጥ ተስፋ አደርጋለሁ” ሰትል ተናግራለች። ” ካለፈው አመት በተሻለ መልኩ በልምምድ ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ፤ ስለዚህ አምና በውድድሩ ያሳካሁትን ሰአት ለማሻሻል አቅም ያለኝ ይመስለኛል” ያለችው ትግስት የአለም ሪኮርድን ዳግም የምሰብር ከሆነ ፔስ ሜከሮቹ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፃለች። ለግማሽ ማራቶኑ ‘ ፔስሜከሮቹ’ የሚያስቀምጡት ሰአትም ከአምናው የተሻለ ሆኖ የበለጠ ፈጣን ሰአት ለመሮጥ እንደሚያስችለኝ እጠብቃለሁ ሰትልም ተደምጣለች።

የለንደን ማራቶን ሪኮርድ በ2003 በፓውላ ራድክሊፍ የተገኘ ሲሆን 2:15:25 በመግባት ያሳካችው እንደሆነ አይዘነጋም። በወቅቱም የነበሩት ‘ ፔስ ሜከሮች’ ወንድ አትሌቶች ነበሩ።

የአየር ንብረት ግምት እንደሚያሳየው በእለቱ በለንደን ለማራቶን ተስማሚ የሚባል የአየር ንብረት ይኖራል። ከፊል ደማናማ የሆነ የአየር ሁኔታ እንደሚኖርም ይጠበቃል። የሴቶቹ ውድድር 5:05 ሲል የሚጀመር ሲሆን የወንዶቹ ደግሞ 5:35 ላይ ይጀምራል። 59,000 ተሳታፊዎች የሚሮጡበት የዘንድሮው ውድድር ባሳለፍነው አመት 56,640 ሰዎች ጨርሰው በርካታ ተሳታፊዎች የጨረሱበት ማራቶን በሚል ያስመዘገበውን ሪኮርድ ለማሻሻል ያልማል። በዚህ ውድድር ላይ በተለያዩ ዘርፎች ዝና እና ሀብትን መገንባት የቻሉ በርካታ ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉም ይሆናል።

✍️ ዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.