25ኛ አመቱን በደማቅ መልኩ ለማሳለፍ የተዘጋጀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ !

ባሳለፍነው አመት የጎልድ ሌብል የጎዳና ላይ ሩጫ ደረጃን ያገኘው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ 55,000 በላይ ተሳታፊዎች እና ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ እንግዶችን አካቶ እሁድ ህዳር 14 /2018 እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ከዚህ ታላቅ የሩጫ ዝግጅት አስቀድሞ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ታላቁ ሩጫ ሲነሳ ቀድሞ ስሙ የሚነሳው ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ የቦስተን እና የቺካጎ ማራቶን ዳይሬክተሮች እንዲሁም የቀድሞ እውቅ አትሌቶች ፖል ቴርጋት፣ ካሊድ ካኖቺ፣ ሞሰስ ታኖዊ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የዝግጅቱን መድረክ ሲመራ የነበረው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጲያ ጀነራል ማናጀር የሆነው ሪቻርድ ኔኩራር ነበር። ሪቻርድ እንግሊዛዊ የቀድሞ የትራክ እና የጎዳና ላይ አትሌት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

በመጀመሪያ ከቱሪዝም ሚኒስትር የመጡት ዶ/ር እንደገና አበበ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለታላቁ ሩጫ 25ኛ አመት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመቀጠልም ላለፉት አመታት የስያሜ መብት አጋር በመሆን ጭምር እና ዘንድሮ 30ኛ አመቱን እያከበረ የሚገኘው ሶፊ ማልት አመራር የሆኑት ዊሊያም መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ዘንድሮ የታላቁ ሩጫ 25ኛ አመት ከድርጀታችን የ30 አመት ጉዞ ጋር መግጠሙ ውድድሩን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴም እንዲሁ ንግግር ያደረገ ሲሆን ላለፉት 28 አመታት ጉዞ አስተዋፅኦ ያደረጉ በጎ ፈቃደኞች፣ ሚዲያዎች እና የታላቁ ሩጫ ቡድንን አመስግኗል። በተለይም ደግሞ የታላቁ ሩጫ አዘጋጅ ቡድኑን ጠንካራ ሰራተኝነት አወድሷል።

ከሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ በመቀጠል ንግግር ያደረገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ ነጋሽ መልእክቱን ያስተላለፈ ሲሆን ተሳታፊዎች ጠዋት 1፡00 መስቀል አደባባይ እንዲደርሱምአሳስቧል። የፈጣን ማእበል መነሻ ግዮን ሆቴል እና የዘና ማዕበል መነሻ መስቀል አደባባይ እንደሚሆንም አስታውሷል፡፡

የጋዜጣዊ መግለጫው ሌላው ሁነት ደግሞ ለአመታት አብሯቸው የሰራውን ሀያት ሪኤጀንሲን ለማመስገን ታላቁ ሩጫ ስጦታ ማበርከቱ  ነበር። ሀያት ሪኤጀንሲ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኬተሪንግ አገልግሎት ላይም ተሳትፎ እያደረገ እንዳለ ተገልጿል።

የቺካጎ ማራቶን የውድድር ዳይሬክተር ኬሪ ፒንኮቭስኪ እና የቦስተን ማራቶን የውድድር ዳይሬክተር ጃክ ፍሌሚንግ ደግሞ በመድረኩ ላይ ከሪቻርድ ጋር መጠነኛ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10ኪ.ሜ አዘጋጆችን አድንቀዋል። ሁለቱም ይህ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ነው።ጃክ ፍሌሚንግ ሲናገሩም “በአስደናቂ ሀገር በጣም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን እንገኛለን። እዚህ ያለው ሁሉም ሰው ቤታችን ያለን ያክል እንዲሰማን እያደረገን ነው። እሁድ ሩጫውን እስከማይ እጅግ ጓጉቻለሁ” ብለዋል።

ከዚህ በመቀጠል ሞሰስ፣ ሀይሌ፣ ካኑቺ እና ቴርጋርት ከሪቻርድ ጋር በመድረኩ ላይ ያደረጉት አጠር ያለ ቆይታ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ እና የአመታት የሩጫ ፉክክራቸውን ያስታወሰ ነበር። እነዚህ አትሌቶች ሁሉም በየዘርፎቻቸው ባለሪኮርድ መሆን ችለው ያለፉ አትሌቶች ሲሆኑ ሞሮኮዊዎ ካኑቺ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደኢትዮጵያ እንደመጣ ገልጿል። በጊዜው ተፎካካሪው ከነበረው ሀይሌ ጋርም እ.ኤ.አ ከ2002 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኛታቸውን አውስቷል።

55,000 ሰዎች የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር የሚሰራበትን ስምምነት መፈፀሙን የምናስታውስ ሲሆን ድርጅቱ እንደ ቺካጎ ማራቶን ካሉ የአለማችን ትላላቅ ማራቶን ጋር በጋራ እንደሚሰራ ይታወቃል። የውድድሩ ቅድመ-ጋዜጣዊ መግለጫም እሁድ ህዳር 14 ,2018 ለሚደረገው ሩጫ መልካም ምኞት በመመኘት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.