የታላቁ ሩጫ ምዝገባ ተጀመረ !
ለ2019 ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን አዘጋጆች ኅዳር 13,2018 ዓ.ም እሁድ ዕለት ለሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር እስከ 60 ሺህ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፤ ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ ነው። ታላቁ ሩጫ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር የተመሠረተውን አዲስ የአጋርነት ስምምነትም ያሳወቀ ሲሆን ባንኩ የውድድሩ ዋና ስፖንሰር ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል።
ከዋናው ውድድር ጎን ለጎን የሚካሄደው የሕፃናት ውድድርም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 5 ሺህ ተሳታፊዎች ምዝገባ እንዲያደርጉ እድል ተሰጥቷቸዋል። ባንክ ኦፍ አሜሪካ በተጨማሪም መጋቢት 2019 ዓ.ም ከዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ጋር ተያይዞ የሚካሄደውን የ«ቅድሚያ ለሴቶች» 5 ኪሎ ሜትር ውድድርም እንዲሁ ኣጋር ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዳግማዊት አማረ፣ የተጠናከረው ይህ አጋርነት ለወጣቶች ዕድል፣ ለስፖርት ቱሪዝም እና ለአካባቢው የንግድ ተቋማት ድጋፍ ትኩረት የሚሰጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ገልጸዋል። አዘጋጆች እንደሚናገሩት አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች አሁንም ከኢትዮጵያ ቢሆኑም ውድድሩ በዓለም አትሌቲክስ ደረጃውን የጠበቀ ዕውቅና (World Athletics Label) እያገኘ በመምጣቱ የውጭ አገር ተሳታፊዎች ቁጥር በዚህ ዓመት ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ተሳትፎን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት አካልነትም፣ ከጠቅላላው ቁጥር 5 በመቶ የሚሆነው ማለትም 3 ሺህ ነጻ የምዝገባ ዕድል ለመጨረሻ ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ይሰጣል።
ውድድሩ ከተጀመረ 26 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትክክለኛ የመድረሻ ሰዓት ለሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች የቺፕ ሰዓት አቆጣጠር አገልግሎት ይሰጣል። አዘጋጆችም ተሳታፊዎች ራሳቸውን ለማዘጋጀት አዲስ የተጀመረውን የሥልጠና መተግበሪያ (አፕ) እንዲጠቀሙ እያበረታቱ ነው። ውድድሩ በድጋሚ «ራን ፎር አ ኮዝ» (Run For A Cause) የተሰኘውን የበጎ አድራጎት ዘመቻ የሚያካሂድ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተመረጡ ሦስት ድርጅቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ለዘንድሮው ዘመቻ የተቀመጠው ግብ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የማሰባሰብ ነው።
የባንክ ኦፍ አሜሪካ የሰብ ሰሃራ አፍሪካ ኃላፊ ወ/ሮ ይቮን አይክ እንደተናገሩት ውድድሩ ማህበረሰብን የሚያስተሳስር፣ ወጣቶችን የሚያነሳሳ እና ከውድድር ቀኑ ባለፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያነቃቃ መድረክ ሆኖ አድጓል። ምዝገባ የሚከናወነው በቴሌብር (Telebirr) መተግበሪያ ብቻ ህኖ የመግቢያ ክፍያውም ከመስቀል አደባባይ ለሚነሳው ቀይ ለባሽ 790 ብር፣ ከጊዮን ሆቴል ፊት ለፊት ለሚነሳውና በቺፕ ለሚሰላው አረንጓዴ ለባሽ ደግሞ 950 ብር ተደርጓል።
