በባዶ እግር ታሪክ ሲፃፍ…ሻምበል አበበ ቢቂላ
በማራቶን የመጀመሪያ ጥቁር አፍሪካዊ ሆኖ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለው አትሌት ጀግናው አበበ ቢቂላ ጃቶ በተሰኘች ስፍራ የዛሬ 92 አመት ተወለደ፤ ልክ እንደዛኔው የገጠራማ አካባቢ ተወላጆች ሁሉ አበበ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከብት ይጠብቅ ነበር።
እድሜው ወደአስራዎቹ ሲገባም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የሀገሪቶን የኢምፔሪያል ጋርድ ተቀላቅሎ፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴን ከሚጠብቁት ጠባቂዎች አንዱ መሆን ቻለ። በዚያም ሳለ በሩጫው ተሰጥኦ እንዳለው ማሳየት ቻለ፤ በስዊድናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካኖን ስርም መሰልጠን ጀመረ፤አበበ ግን በወቅቱ የሀገሪቷ ምርጡ አትሌት አልነበረም፤ ዋሚ ቢራቱ ለ1960ው የሮም ኦሎምፒክ ተቀዳሚ ተመራጩ አትሌት ሆነ፤ ሆኖም ዋሚ ቢራቱ ሮም ከመሄዱ ከቀናት በፊት ህመም አጋጠመው፤ በሮም ኦሎምፒክ ላይም መካፈል ሳይችል ቀረ።
አበበም ዋሚ ቢራቱን ተክቶ ሄደ። አበበ ሮም ሲደርስ መሮጫ ጫማው ተገንጥሎ የነበረ በመሆኑ ሌላ አመራጭ መፈለግ ነበረበት፤ አዲስ ጫማ አርጎ ቢሮጥም ምቾት እንደሚነሳው በማሰብ በሮም የኮብልስቶን ጎዳናዎች ላይ በባዶ እግሩ ለመሮጥ ወሰነ። በውድድሩ እንደሚያሰንፍ ሰፊ ቅድመ-ግምት ከተሰጠው ሞሮኮዊ አትሌት ጋርም ተፋለመ፤ በስተመጨረሻም አሸነፈ። 2:15:16 በሆነ ሰአት ገባ።
ይሄ ድሉ አንድ ዝም ብሎ ተራ ድል አደለም፤ አስቡት በባዶ እግር ነው የሮጠው፤ አስቡት በኦሎምፒክ ታሪክ ማራቶንን ማሸነፍ የቻለ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ሆኗል፤ ምን ይሄ ብቻ ባለሪኮርድም ጭምር በመሆን ታሪክ ፅፏል። ” በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ፤ አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ” ሲልም ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ አቀነቀነ። ብዙዎችም ስለእሱ መነጋገር ጀመሩ።

የእርሱ ድል ምስራቅ አፍሪካ በረጅም ርቀት ላይ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን አትሌቶች ማፍራት እንደምትችል ያሳየ ነበር። አበበ በዚህ አላበቃም በ1964ቱ ኦሎምፒክም የቶክዮ ኦሎምፒክን አሸነፈ፤ የሚገርመው ይህ አይደለም ኦሎምፒኩን ያሸነፈው የትርፍ አንጀቱ ከወጣለት ከ14 ቀናት በኋላ ነው። አሁንም በድጋሜ ሪኮርድ በመስበር የኦሎምፒክ ወርቅን አሳካ፤ ይህም ስሙን በታሪክ መዝገብ በደማቁ እንዲፃፍ አደረገው። አበበ በታሪክ ተከታታይ ማራቶኖችን ማሸነፍ የቻለ ቀዳሚው አትሌት መሆንም ችሎ ነበር።
በ1969 ያልተጠቀ ነገር ጀግናው ላይ ተከሰተ፤ አበበ የመኪና አደጋ አጋጠመው፤ አደጋውም በዊልቼር ላይ አስቀመጠው፤ እነዛ ሲያሻው በባዶ እግር አልያም ጫማ ተጫምቶ ያሸነፈባቸው እግሮች ከዱት። ሰውዬው ግን አበበ ነው፤ ማበብ እንጂ መክሰም መች ያውቅና የቀስት ውርወራ እና የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ላይ መካፈል ጀመረ። በ1970ም በለንደኔ በተካሄደው የስቶክ ማንድቬል ጨዋታ ላይ ተሳተፈ። በ1971ም በኖርዌይ ለአካል ጉዳተኞች በተዘጋጀው የሀገር አቋራጭ በቀስት ውድድር ማሸነፍ ቻለ።
የአካል ጉዳት አበበን አላቆመውም፤ ነገር ግን ከአደጋው ጋር ተያይዞ በተከሰቱበት ህመሞች ምክንያት በ1973 በ41 አመቱ ላይመለስ አሸለበ። አበበ የሚለው ስም ግን አሁን ድረስ ከመቃብር በላይ መሆኑን የሮም እና የቶክዮ ጎዳናዎች ምስክር ናቸው።
* በፅሁፉ ላይ የተፃፉት አመቶች በሙሉ የተፃፉት እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር ነው።
