13ኛው የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ።

13ኛው የዩሮፓ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ በስፔን ሲቭያ ከተማ ራሞ ሳንቶስ ፒጅዋን ስቴዲየም ተካሂዷል።

▪️ሁለቱም ቡድኖች ሁለተኛ የአውሮፓ ዋንጫቸውን ለማግኘት የተፋጠጡ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1972 በባርሴሎና በተካሄደው ጨዋታ  የስኮትላንዱ ግላስኮው ሬንጀርስ የሩሲያውን ዳይናሞ ሞስኮ በዋንጫ ጨዋታው 3-2 በማሸነፍ ባለ ክብር ነበር። የጀርመኑ ኢንትራ ፍራንክፈርት በበኩሉ ሌላኛውን የቡንደስሊጋ ቡድን ቦሩሲያ ሞንቼግላድባህን በ1980 በተካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ በድምር ውጤት 3-3 ግን ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ህግ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሎ ነበር።

▪️ፍራንክፈርት ወደ ስፔን አቅንቶ 2 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን በአጠቃላይ 5 ጊዜ መጥቶ ሽንፈትን አላስተናገደም። በግማሽ ፍፃሜው በካምፕ ኑ ባርሴሎናን ከውድድሩ ማሰናበታቸው ይታወሳል። ሬንጀርስ በበኩሉ በስፔን ጥሩ ሪከርድ ባይኖረውም በውድድሩ 2 የጀርመን ክለቦችን ማሰናበቱ እንደ ጠንካራ ጎን ይቆጥረዋል።

▪️ከዛሬ በፊት ሁለቱ ቡድኖች በ1959/60 የውድድር ዘመን በአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ የተገናኙ ሲሆን ፍራንክፈርት በድምር ውጤት 12-4 ማሸነፍ ችለው ነበር ምንም በፍፃሜው በሪያል ማድሪድ ቢሸነፉም ማለት ነው።

▪️የሁለቱም ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች በሲቭያ የተገኙ ሲሆን ጨዋታው የሚካሄድበት ራሞ ሳንቶስ ፑጁአን 40,000 ተመልካች ብቻ የመያዝ አቅም ስላለው ሴልቲክ በ2003 በፖርቶ በተሸነፈበት እና 57,000 ሰዎችን መያዝ ወደሚችለው ስታዲዮ  ላ ካርቱሀ ስቴዲየም ግዙፍ ስክሪኖች ታግዘው ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ተገደዋል። ለሁለቱም ክለቦች በአጠቃላይ 18,000 ቲኬቶችን መሸጡም ተገልጿል።

▪️የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የማጥቃት እንዲሁም የመከላከል እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር። ሬንጀርስ በቀድሞ የሼፍልድ ተጫዋች ጆን ለንደስትራም እንዲሁም ፍራንክፈርት በአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ኮስቲች አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

▪️በሁለተኛው አጋማሽ 57ኛው ደቂቃ ላይ የፍራንክፈርቱ አማካይ ጅብሪ ሶው እና ተከላካዩ ቱታ ስህተት በሚገባ በመጠቀም አጥቂው ጆ አሪቦ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጠረ።

▪️መሪነታቸው ለ12 ደቂቃዎች ብቻ ነው የቆየው። ኮስቲች ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ በሁለት ተከላካዮች መሀል የነበረው ሳንቶስ ቦር ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ አስገኝቷል።

▪️መደበኛ 90 ደቂቃውም በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ወደ ጭማሪ ሰአት አምርተዋል። በተጨመረው 30 ደቂቃ በአንፃራዊነት ሬንጀርሶች ወደ ግብ በመድረስ እንዲሁም ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ ነበሩ። ግን ሁለቱም ቡድኖች መሪ መሆን የሚችሉበትን ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ለማምራት ተገደዋል።

በፍፁም ቅጣት ምቱም ኢንትራ ፍራንክፈርት 5-4 በማሸነፍ የጀርመኑ ክለብ ሻምፒዮን መሆን ችሏል። የዘንድሮው የዩሮፓ ሊግ ልክ እንደ አምናው በፍፁም ቅጣት ምት እልባት ያገኘ ሲሆን በተከታታይ አመት ይህ መሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደርገዋል። በሬንጀርስ በኩል ጨዋታው ተጠናቆ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ከማምራቱ 3 ደቂቃዎች በፊት የገባው የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች አሮን ራምሴ ፍፁም ቅጣት ምቱን ያመከነ ተጫዋች ነው።

▪️ኢንትራ ፍራንክፈርት ይህ ውድድር አዲስ መልክ እና ስም ከያዘ በኋላ ያሸነፉት የመጀመሪያ ዋንጫም መሆን ችሏል። ይህ ብቻም አይደለም የዘንድሮው የ2021/22 የዩሮፓ ሊግ ከተጀመረ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫ ያነሳ ሶስተኛው ቡድን መሆን ችሏል። አምና ቪላሪያል እንዲሁም በ2018/19 ቼልሲ በተመሳሳይ ምንም ጨዋታ ሳይሸነፉ ዋንጫውን ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።

ሚካኤል ደጀኔ።

Michael dejene

Michael dejene Bsc in computer science Born in october 12,1998 Age 23 Editor of ethiopianssport.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.