‘ራስ አል ካማያህ’ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በበረሀው ድል ቀንቷቸዋል።
የራስ አል ካማያህ የግማሽ ማራቶን ውድድር አምና በኮቪድ ወረርሽኝ አማካኝነት መካሄድ ያልቻለ ሲሆን ዘንድሮ በርካታ ተሳታፊዎች አካቶ በሳውድ አረቢያ ተካሂዷል።
በወንዶች በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ኬንያዊው ኪፕሊሞ ባሳለፍነው አመት ህዳር ወር በፖርቹጋሏ ከተማ ሊዝበን 57:31 በመግባት የአለምን ሪከርድ ማሻሻሉ ይታወሳል። ዘንድሮም ይበልጥ ለማሻሻል ጥረት አድርጎ ባይሳካለትም ግን የቶኪዮ ኦሎምፒክ የ5000 ሜትር 5ኛ በ10,000 ሜትር ደግሞ 3ኛ ያጠናቀቀው የ21 አመቱ ጄኮፕ ኪፕሊሞ 57:56 በመግባት በአንደኝነት ውድድሩን አጠናቋል። 5ኛው ፈጣን የግማሽ ማራቶን ሰአትም ሆኖ ተመዝግቧል። እሱን በመከተል ከ34 ሰከንድ በኋላ ሌላው ኬንያዊ ሮናልድ ክዌሞዪ 58:30 በመግባት 2ኛ ሲሆን ከ5 ሰከንድ በኋላም ሌላው ኬንያዊ ሬንጁ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ኢትዮጵያዊው እሸቱ ቱራ 4ኛ እንዲሁም ሌላው ኢትዮጵያዊ አምደወርቅ ዋለልኝ 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
▪️በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ግርማዊት ገ/እግዚአብሔር ካቻምና በተካሄደው ውድድር የቦታውን ሪከርድ 1:04:31 በመግባት የያዘችውን ኢትዮጵያዊቷ አባብል የሳነህ ሪከርድ በ17 ሰከንድ በማሻሻል በአንደኝነት ውድድሯን አጠናቃለች። የ20 አመቷ ግርማዊት በቅርቡ ባሳለፍነው ወር የተካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 2ኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ሁለት ጊዜ የ5000ሜ ሻምፒዮኗ ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ እንዲሁም ሼላ ቼፕኪሩዪ እንዲሁም ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ቦሰና ሙላቴ ጠንካራ ፉክክር ቢገጥማትም ግርማዊት ገ/እግዚአብሔር 1:04:14 በመግባት በአንደኝነት ውድድሯን አጠናቃለች። ኬንያውያኑ ሄለን ኦቢሪ ፣ ቼፕኪሩዪ እንዲሁም ጄፕቱም 1:04:22 ፣ 1:04:36 እንዲሁም 1:05:28 በመግባት 2ኛ ፣ 3ኛ እና 4ኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል። ኢትዮጵያዊቷ ቦሰና ሙላቴ 1:05:46 በመግባት 5ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
ፈለቀ ደምሴ።