ሲዳማ ቡና ገብረ መድህን ኃይሌን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ ቀጠረ
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ አቶ ገብረ መድህን ኃይሌ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን የክለቡ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አስታውቋል።
ክለቡ ከቀረቡት ዕጩ አሠልጣኞች ጥቆማ መካከል አሠልጣኙ ያላቸውን የረጅም ዓመታት ሥራ ልምድ፣ የሕይወት ተሞክሮ፣ በአሠልጣኝነት ዘመን ያሳዩትን ውጤታማነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦርዱ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ ቀጥሯቸዋል።
አሠልጣኙ ከዚህ ቀደም ባሠለጠኗቸው ክለቦች ጅማ አባጅፋር እና መቐለ 70 አንደርታ የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮን ያደረጉ ሲሆን፤ በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ በነበራቸው ቆይታ ሁለት ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ወይም ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።
በቀጣይም የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብን ከገጠመው የውጤት ቀውስ በማውጣት ክለቡን እንደሚታደጉና የስፖርት ቤተሰቡን መሻት እንደሚያሳኩ እምነት መጣሉን ከሲዳማ ክልል ባህል፣ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።