የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
ሊቨርፑል ከ ማንችስተር ዩናይትድ
የ2020/21 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እስከአሁን ከተደረጉ በጨዋታዎች ትልቁ የሚባለው ፍልሚያ እሁድ ማታ 1፡30 ሲል በአንፊልድ በሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ መካከል ይካሄዳል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ ሊጉን በድምሩ ለ39 ጊዜ በመውሰድ የሊጉ ቀዳሚ ክለቦች ሲሆን ወደ መጠላላት ያዘነበለ ጠንካራ ባላንጣነትም በመካከላቸው አለ፡፡
የላንክሻየር ደርቢ እየተባለ የሚጠራው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የሚደረግበት ቀን ሲቃለብ አይኖች ሁሉ ወደ እዚያ ያመራሉ፤ በ35.4 ማይል ርቀት ላይ ብቻ የሚገኙት የነዚህ ክለብ ደጋፊዎችን ለመቆጣጠር የብሪታንያ ፓሊስም ከየትኛውም ጨዋታ በላይ ከፍተኛ ስራ ይበዛበታል፡፡
ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን በሁዋላ የቀድሞው ሞገሱን ያጣው ዩናይትድ በኦሌጎናር ሶልሻየር መሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታው ሲሆን ከሜዳቸው ውጪ ያላቸው ያለመሸነፍ ሪኮርድ ለማንቺስተር ዩናይትድ በጨዋታው ነጥብ ይዘው ሊወጡ ይችላሉ የሚል ግምት አሰጥቷቸዋል፡፡
በተቃራኒው ብዙዎቹን ባስማማ መልኩ ያለፉትን ሁለት ዓመታት አይነት ጥንካሬ ላይ የማይገኘው የየርገን ክሎፑ ሊቨርፑል በሜዳው ላይ ያለው የበላይነት ግን ውጤት ይዞ እንዲወጣ ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሊቨርፑል በኩል አሰልጣኝ የርገን ከሎፕ ያለፉት 3 ጨዋታዎች በጉዳት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው የመሀል ተከላካዩ ጆዬል ማቲፕ ለጨዋታው የሚደርስበት ተስፋ እንዳለው የተናገሩ ሲሆን ፊትነሱን ማግኘት የማይችል ከሆነ በምትኩ ከታዳጊዎቹ ራያን ዊልያምስ ወይም ናቲ ፊሊፕስ አንዳቸው ቦታውን የሚሸፍኑ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቁት ቨርጂል ቫን ዳይክ ፣ ጆይ ጎሜዝ ፣ ዲዬጎ ጆታ ፣ ኮስታኖስ ቲሚካስ እና ናቢ ኬዬታ ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን የቲያጎ አልካንትራን ግን ለጨዋታ በቁ ነው፡፡
በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል የመሀል ተከላካዩ ቪክቶር ሊንደሎፍ ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ሲሆን ኤሪክ ቤይሊ ቦታውን እንደሚተካው ሲጠበቅ በሌላ በኩል ብሬንዳን ዊልያምስ እና ፊል ጆንስ ከጨዋታ ውጪ ናቸው፡፡ ከበርንሌይ ጋር ወደ ሜዳ የተመለሱት አንቶኒ ማርሻል እና ኔማንያ ማቲች ለዚህም ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አሰላለፍ
ማንቸስተር ዩናይትድ፡- ዴሂያ፣ ዋንቢሳካ፣ ቤይሊ፣ ማጓየር፣ ሾው፣ ማክቶሚናይ፣ ፍሬድ፣ ፖግባ፣ ፈርናንዴዝ፣ ማርሻል፣ ራሽፎርድ
ሊቨርፑል፡- አድሪያን፣ አ. አርሎንድ፣ ፋቢኒሆ፣ ማቲፕ፣ ሮበርትሰን፣ ሄንደርሰን፣ ቲያጎ ፣ ዊናልደም፣ ማኔ፣ ፈርሚኖ፣ ሳላህ