አባይ ላይ የተፋለሙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከሞት ተርፈዋል

ለባህርዳር እና ለጎንደር እንዲሁም ለጠቅላላው ሀገራችን ትልቅ የታሪክ ማህደር የሆነውና በዩኔስኮ የተመዘገበው የቱሪስት መስህብ የጣና ሀይቅ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ 
              ይህንን አደጋ ለመከላከል የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች አረሙን በማጨድ እና ህዝቡን በማስተባበር ስራ ተጠምደው ከርመዋል፡፡ 
ይህን የተረዱት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችም ከፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ጋር በመነጋገር ክለቦቻቸው የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ  በመስማማታቸው ወደ ክለቦቻቸው በመሄድ ያቀረቡት ሀሳብ ድጋፍ ያገኛል። 
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ቦርድም ክለቡ ሶስት የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያካሂድ እና ደጋፊዎቹን ወደ ቦታው አድርሶ የሚመልስ ትራንስፖርት በመከራየት ወደቦታው እንዲጓዙ አመቻችቷል፡፡
         ደጋፊዎቹም ለአራት ተከታታይ ቀናት ስራ ከመፍታታቸው በተጨማሪ ተያያዥ ወጪዎችን በመሸፈን አላማውን ደግፈው ወደቦታው ተጉዘዋል፡፡ አንዳንዶቹም በግል መኪና እና በአውሮፕላን ጭምር በመጓዝ በቦታው ተገኝተዋል፡፡
በተያዘው ፕሮግራም መሠረትም መስከረም 21 ቀን ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከአውስኮድ ሲጫወቱ በቀጣይነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ እና ከአውስኮድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን በማከናወን ገቢው ጣናን ለወረረው የእንቦጭ አረም ማስወገጃ እንዲሆን ታስቧል፡፡
          በመጀመሪያው ቀን ውድድር ለዚህ ወዳጅነት ግጥሚያ ትኩረት በመስጠት ፋሲል ከተማ በደቡብ ክልል ካስትል ዋንጫ ውድድር ላይ የነበረበትን የደረጃ ግጥሚያ ለሁለተኛ ቡድኑ አሳልፎ በመስጠት ወደ ባህርዳር አቅንቷል፡፡
         ውድድሩ የተካሔደው በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሜዳ ሲሆን በእለቱም ከአምስት መቶ ሺ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ስቴዲየሙ መያዝ ከሚችለው በላይ ወደ ሀያ ሺህ የሚገመት ሠው ጢም ብሎ ስለሞላ የተመለሰው ሰው ሌላ ሁለት ስቴዲየም ይሞላ ነበር፡፡
         በእለቱ ውድድር የደጋፊዎች መሞጋገስ እና ፍቅር ልዩ ነበር፡፡ የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ያወድሳሉ የባህርዳር ከተማ ደጋፊዎችም በተመሳሳይ ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ውዳሴ ያቀርባሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም አንወድም ጣና ሲነካ በማለት ይዘምራሉ፡፡

የፋሲል ደጋፊዎችም ሶስት ለአንድ በእንግዳው ቡድን መሸነፋቸው ቢጎመዝዛቸውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት በሰላም ተሰነባብተው ተለያይተው ነበር፡፡

ይህን ፍቅር ግን በዋናነት አላማ አድርገው ቀጠሮ በተያዘለት በማግስቱ ሰኞ መስከረም 22 ቀን በተደረገው የእንቦጭ ነቀላ ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ ደግመን አላየነውም፡፡ በአረሙ ወቅት ሁለት ደጋፊዎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር፡፡
       ቅዱስ ጊዮርጊሶችን አባይ በረኻን አቋርጠው ያስኬዳቸው ዋናው መነሻ የጣና ሀይቅ በእንቦጭ አረም እየተጠቃ መሆኑን መስማታቸው ሲሆን በቦታው ሲደርሱ ያስተዋሉት ግን ከዛም የከፋ ነበር ፡፡
         ደቡብ እና ሰሜን ጎንደርን እንዲሁም በምእራብ ጎጃም ላይ በ3620 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ላይ የተጣለለው የጣና ሀይቅ እንቦጭ የተባለ ውሀ ቀለቡ የሆነ አረም እንደወረርሺኝ እየተዛመተ ህልውናውን እየተፈታተነው እና በውስጡ የሚገኙ እጽዋትን እና አሳዎችን እያጠፋ ይገኛል፡፡ ከደንቢያ የተነሳው እንቦጭ አረም በአሁን ግዜ ሰሜናዊ ምስራቅ የሀይቁን ክፍል አዳርሷል፡፡
         የጣና ሀይቅ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ያለው እና ለሀገራችን ኢኮናሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ 
ለናሙና ያህል 
1. በ2008 ዓ.ም 45,959 ( አርባ አምስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ዘጠኝ) ቱሪስቶች
2. 278,228 (ሁለት መቶ ሰባ ስምንት ሺ ሁለት መቶ ሀያ ስምንት ) የሀገር ውስጥ ነዋሪዎች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ጎብኝተውታል ፡፡
ከነዚህ ጎብኚዎች ባጠቃላይ 429,774,914 (አራት መቶ ሀያ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰባ አራት ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ አራት )ብር ገቢ መገኘቱን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
          ይህ እንግዲህ ጎብኚዎቹ ወደ ክልሉ ከመሄዳቸው በፊት ከአዲስ አበባ ኤርፖርት ጀምሮ የሚመነዝሩትን ዶላር አያካትትም፡፡ በተጨማሪም የጣናን ሀይቅ እና ገዳማትን ሊጎበኙ የሚመጡ ጎብኚዎች ላሊበላ፣ ጪስ አባይ ፏፏቴ፣ አክሱምንና ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን ሊጎበኙ ይችላሉ፡፡
         ከቱሪስቶች ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ በአሳ ምርት የሚገኘው ገቢ እና ለመላው ሀገሪቱ የሚሠጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡
        የተቀናጀ ማህረሠብ አቀፍ ከግብርና ጋር የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በየስድስት ወሩ ጣና ላይ በሚያደርገው አሰሳ ከጎንደር በሚመጣው ወንዝ መገጭ አካባቢ በነሀሴ 2003 ዓ.ም በዶክተር አያሌው ወንዲ  አማካኝነት የእንቦጭ አረም መከሰቱን በማወቁ ክስተቱን መርምሮ በማረጋገጥ በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም ለክልሉ መንግስት ያሳውቃሉ፡ በዚህም መሰረት የተወሰነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና ቅስቀሳ ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሰጥ የተደረገ ሲሆን ከተወሰነ ግዜ በሗላ ይህ እንቅስቃሴ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
         ይህን አረም ለማጥፋት ካሉት መንገዶች አንዱ ኬሚካል ያለው መድሀኒት መርጨት ቢሆንም ይህን ለማድረግ የአካባቢው ማህረሰብ እና እንስሳት ውሀውን ለመጠጥነት ስለሚጠቀሙበት መጠቀም ስለማይቻል በሰው ሀይልና በእጅ መሳሪያ ለመከላከል እየተሞከረ ቆይቷል፡፡
ይህ በሰው ሀይል እና በእጅ መሳሪያ መጠቀም ግን አረሙ ሳይስፋፋ በአጭሩ ለመቅጨት ብቻ ነው፡፡ እንደአማራጭ የሚታየው በአሁን ወቅት ግን አረሙ እየተስፋፋ ሄዶ በሀይቁ ዳርቻ ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ አዳርሷል፡፡

        ይህን አረም ለማስወገድ እንደባለሞያዎቹ አስተያየት ተከታታይ እና ያልተቋረጠ ስራ ይጠይቃል ፡፡  ይህን ለማድረግ ደግሞ የአካባቢው አርሶ አደር ሀይቁ ላይ እስከ አንገቱ ድረስ በመግባት እንቦጩን ለመንቀል ታግሏል፡፡ አንድ ቀን ገብቶ ሲነቅል የዋለ ሰው በተከታታይ ቀን መድገም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ውሀው ራሱ የግለሰቡን የውስጥን አሰራር ያቃውሰዋል፡፡ ለጤናውም ችግር ያመጣል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የወባ በሽታ ስላለ ቀደም ብለው በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ያገረሽባቸዋል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ አሰራር የአካባቢው ነዋሪ ተከታታይ ትግል ቢያደርግም በአሁን ሰአት እየደከመው እና ተስፋ እየቆረጠ መጥቷል፡፡ በበጋው ወቅት ደግሞ ውሀው ስለሚቀንስ እና እንቦጩ ወደ መሬት ሰርጎ ስለሚገባ ለመንቀልም ሆነ ለማጨድ እንዳሁኑ አመቺ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ለጊዜው በጀልባ የታገዘ ተከታታይ ስራ ያስፈልጋል፡፡

         በተጨማሪም አንድ ማደበሪያ የታጨደ አረም አስወግዶ ከሀይቁ ለሚያወጣ አርሶ አደር የተወሰነ ክፍያ ቢደረግለት አርሶ አደሩ ከነልጆቹ እና የልጅ ለጆቹ ሊረባረብ ይችላል፡፡ ምከንያቱም የሰው ሀይል እንጠቀም ከተባለ የከተማው ሰው እና ከሌላ አካባቢ የመጣው ሰው አስተማማኝ የዋና ችሎታ ስለማይኖረው የአካባቢው ህዝብ የእለት ተእለት ኑሮውን በመተው በቋሚነት ለማገዝ ይቸግረዋል፡፡
         ይህ አረም አውሮፓ ላይ ሳይከሰት ሲቀር ችግሩ አፍሪካ ላይ እንደሚበረታ እና የምድር ወገብን ተከትሎ የሚመጣው አረም ደቡብ አሜሪካ እና አውስትራሊያን ጨምሮ ከአፍሪካም ግብጽ እና ሱዳንን ያጠቃ ሲሆን ለግብጽ እና ለሱዳን ግን ችግሩ አስጊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የብዝሀ ህይወት ስነ ምህዳሩ ኑሮን እና ገቢን የሚፈታተን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ውሀውን የሚጠቀሙበት ለመስኖ ብቻ ነው፡፡

  ስለሆነም ካናል ላይ ኬሚካል ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ግብጻውያን ይህ አረም በሚበዛባቸው ግዜ ግድቡን ይዘጉትና ኬሚካል ይረጫሉ፡፡ ችግሩ ከመጠን አያልፍም ሊቆጣጠሩትም የሚችሉበት እድልም አላቸው፡፡ 
         እኛ ግን ኬሚካል እንዳንጠቀም እንስሳዎች ወይም ጢንዚዛዎች እንዲበሉት በማድረግ ወይም በሽታ እንዲያጠቃው በማድረግ ለማስወገድ እንዳይሞከር በጣም ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ በተጨማሪ አረሙ ላለመስፋፋቱ እና ስነህይወታዊው የማስወገጃ መንገድ ውጤታማ ለመሆኑ ሰፊ ጥናት ይጠይቃል፡፡
  እንደ አውሮፓውያኑ በማሽን ለማጨድ እና ለማጥፋት  የሀይቁ ጥልቀት እና ስፋት ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ማሽኑ ቢያንስ አስር ሜትር ይፈልጋል፤ የኛ ደግሞ ዳር ዳሩን ከአንድ ሜትር በታች እስከ ሀምሳ ሴንቲ ሜትር ድረሰ በአረሙ ተወጧል፡፡
ስለዚህ ማሽኑ ከተገኘ ለእኛ ሀይቅ የሚስማማ ማሽን በትእዛዝ መሠራት ( መገዛት) አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ዩኒቨርስቲዎች እና የግል ባለሀብቶች ሙከራ ቢያደርጉም ወደውጤት አልተመጣም፡፡
ምክንያቱም ችግሩ እንዳሁኑ አሳሳቢ ሆኖ አልታየም፡፡ 
ይህን አረም የሚያጭድ ማሽን ለመገዛት ቪክቶሪያ ላይ እስከ ሰባ ሚሊዮን ብር ያወጣል፡፡ ጣናን ያስጨነቀው አረም ደግሞ ያካለለው ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በላይ ስለሆነ አንድ ማሽን በቂ አይደለም ቢያንስ ሰፋ ያለ ጥልቀት ላለው ቦታ ማሽኑ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ጥልቀት ለሌለው ዳርቻው አካባቢ ደግሞ አነስተኛ ማሽኖችን መግዛት ካልተገኘም በትዛዝ ማሰራት ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም ከሀይቁ ጋር ተስማምተው የሚኖሩት እና በእንቦጭ አረም ወረርሺኝ የተዋጡት እና የጠፉት ነባር ዝርያዎቹ እነ ደንገል እነ ሲላ እና እንጫጭላ እንዲሁም ቄጤማ እንደገና እንዲያገግሙ ማድረግ፤ ጠፍተውም ከሆነ እየተተከሉ እንዲራቡ በማድረግ ወደቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ በማድረግ አካባቢው ለእንቦጭ እንዳይመች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
         እነዚህ ከሀይቁ ጋር ተስማምተው አሳው እንቁላሉን የሚጥልባቸው እና የሚራባባቸው እጽዋቶች ናቸው፡፡ እንቦጭ አረምም የሀይቁን ውሀ እየመጠጠ የውሀው መጠን እንዲቀንስ ከማድረጉ በተጨማሪ እነዚህን የአሳ መራቢያ የሆኑ እጽዋትን ምግብ በመሻማት ያጠፋቸዋል፡፡ይህንን ችግር ለመታደግ የሚመለከተው አካል ህዝቡን በማስተባበር እና በመረባረብ እንቦጭን ማጥፋት ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም የጣና አካባቢን ልቅ የከብቶች ግጦሽ እና እስከድንበሩ ድረስ የተስፋፋውን እርሻ በማስቆም ለሀይቁ የሚስማሙት እጽዋት እንዲራቡ በማድረግ ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 
ከነዚህ መንገዶች አንዱ ህዝቡ የሚያነቃቁ እና የሚያስተባብሩ መድረኮችን ማመቻቸት ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ወደባህርዳር ለወዳጅነት ውድድር ያቀናው በግጥሚያው በሚገኘው ገቢ ችግሩን ለመቅረፍ ከማገዙ በተጨማሪ ደጋፊዎቹ ቦታው ላይ ተገኝተው አረም ነቀላው ላይ እንዲሳተፉ እና በህብረተሰቡ ላይ መነቃቃትን እንዲፈጥሩ ነበር፡፡
              ሆኖም ግን ደጋፊዎቹ ወደቦታው ሲጓዙ አብሯቸው የተጓዘም ሆነ አጋጣሚውን ለቅስቀሳ ሊጠቀምበት የተዘጋጀ የሚዲያ አካል አልነበረም፡፡ እንቦጩን ለመንቀል የሄዱትም አባይ ላይ በመሆኑ እና ወራጅ ስለነበረ የተወሰኑ ደጋፊዎችም በወራጅ ውሀው የመወሰድ አስደንጋጭ ክስተት ገጥሞአቸዋል፡፡

 ደጋፊዎቹ የነበሩበት የተጣለለ የአባይ  ውራጅ ውሃ ላይ መዋኘት የተለየ ስልት ያስፈልገው ነበር አንድ ደጋፊ ከግሩፑ ነጠል በማለት ሲዋኝ ራሱን መቆጣጠር ተስኖት ውሀው ሲወስደው ቢጮህም ደጋፊዎቹ በዝማሪ እንቦጭ አረሙ ላይ ስለተጠመዱ አላስተዋሉትም እሱን ለማዳን ወደውሃው የገቡት አንድ ደጋፊ እና አንድ ጋዜጠኛም በተመሳሳይ ሁኔታ ውሃው በግምታ ከ70 ሜትር በላይ እያራቀ ሲወስዳቸውም ማንም አላሰተዋላቸውም መሀል ላይሊያጠፉት የነበረን

 እንቦጭ አረም ይዘው ሲጨነቁ ያየ የአካባቢው ዋናተኛ ገበሬ ወደውሀው በመግባት ታድጓቸዋል ፡፡     
ከፋሲል ከነማዎችም ሆነ ከባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች በኳስ ሜዳው ላይ የነበራቸው ፍቅር እና መተሳሰር በእንቦጩ ነቀላው ላይ አልቀጠለም፡፡መንገድ የሚመራቸው አካል አና በቂ የዋና ችሎታ ያለው አደጋውን የሚከላከልላቸው ሰው አልተመደበላቸውም፡፡ 
ከአደጋው የተረፉት ለሌሎቹ በመንገር እና እርስ በርስ በመረዳዳት ቦታው ላይ ከአምስት ሰአት በላይ በመቆየት ከእንቦጩ ጋር በመፋለም ከጠበቁት በላይ አረም የነቀሉ ሲሆን በስተመጨረሻም የከፋ ወራጅ ውሀ ይመጣል በማለት ከአካባቢው ሰዎች በተነገራቸው ምክር ከባህሩ ወጥተው እየዘመሩ እና እየጨፈሩ ሲሄዱ የአካባቢው ህዝብ በአግራሞት ይመለከታቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ስፖርት ዶት ኮም አዘጋጅ /ethiopiansport.com/ያነጋገራቸው የሀይቁ አካባቢ ነዋሪዎች ስለእንቦጭ አረም እና ስለሚያስከትለው ችግር የሚያውቁት መረጃ እንደሌለ ተገንዝበናል፡፡


ይህም ለአካባቢው ህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በበቂ እንዳልተሰራ አመላካች ነው፡፡ 
አረሙን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ተመሳሳይ ስፖርታዊ ውድድሮችንና ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት ተጨማሪ ገቢ
በመሰብሰብ ማሽኖችን በትዕዛዝ ለማሰራትና በመግዛት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ምሁራን ገልፀውልናል፡፡ 

  የጣናን ሀይቅን ወቅታዊ ችገር በተመለከተ የባህርዳር የኒቨርስቲ ምሁራንን ለማናገር ባደረግነው ጥረት አንዳንድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ለጊዜው ምንም አይነት ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል፡፡ ሆኖም ካላይ ያሉትን መጠነኛ መረጃዎች እንድናገኝ ለረዱን ምሁራን እና የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሰራተኞች በአንባቢዎች ስም እናመሰግናነን ፡፡

ሁሉም ወገን የጣናን ችግር ለመፍታት እዲረባረብ እና የፋሲል ከተማን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን አይነት ተመሳሳይ ተግባር አዲከተሉ እርስዎም ይህንን ጽኁፍ አንብበው ለሌሎች የፌስቡክ ጋደኛችዎት እንዲደርስ ሼር በማድረግ  ይተባበሩ

Leave a Reply

Your email address will not be published.