ሩቲ እና ጄፕቺርቺር ለምን ታገዱ? ቀጣይ እርምጃዎችስ?
ኬንያዊቷ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ፔሬስ ጄፕቺርቺር በጊዜያዊነት ከየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር ስትታገድ ኢትዮጵያዊቷ ሯጭ ሩቲ አጋ ደግሞ ስድስት ዓመት እገዳ ተጥሎባታል።
በዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ ሁለት የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች በ”ዶፒንግ” ጉዳይ መነሳታቸው በአትሌቲክሱ ዓለም መነጋገሪያ ሆኗል።
የኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ጉዳይ አሁንም በምርመራ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያዊቷ ሩቲ አጋ ጉዳይ ግን በስድስት ዓመት እገዳ ተጠናቋል።
የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ፔሬስ ጄፕቼርቼር መታገድ

የ33 ዓመቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር በ2021 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ እንዳሸነፈች ይታወሳል። በተመሳሳይ በቶክዮ 2025 የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን ለሀገሯ አስገኝታለች። በዛ ውድድር ላይ እንደውም ከኢትዮጵያዊቶ ትግስት አሰፋ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ እንደነበር አይዘነጋም። የዋና ዋና ማራቶን ድሎቿን ለመጥቀስ ያህል አትሌቷ እንደ ኒውዮርክ እና ቦስተን ባሉ የማራቶን ውድድሮች ላይ አሸናፊ በመሆን ትታወቃለች።
የ”አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት” በጥቅምት 13 ባወጣው መግለጫ ከአትሌቷ በተወሰደ የደም ናሙና ውስጥ የኢፒኦ (EPO) ንጥረ ነገር መገኘቱን ተከትሎ በጊዜያዊነት መታገዷን አስታውቋል። ጄፕቺርቺር ጥፋተኛ ሆና የተገኘችው ከውድድር ውጭ በተደረላት የአበረታች ንጥረ-ነገር ምርመራ ሲሆን ይህም መርማሪዎች አትሌቱ ሳያውቅ ድንገት ወደመኖሪያ ቤት በማምራት የደም ናሙና ወስደው የሚያደርጉት የምርመራ አይነት ነው።
ኢፒኦ የቀይ የደም ሴሎች በብዛት እንዲመረቱ የሚያደርግ ንጥረ- ነገር መሆኑን ተከትሎ ለአትሌቱ የደም ኦክስጅን የመሸከም አቅሙን በመጨመር ብቃቱ ከነበረው የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል። በተለይም ደግሞ ፅናትን በሚጠይቁ የማራቶን አይነት ውድድሮች አትሌቶችን በማበርታት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ጄፕቺርቺር ከመታገዷ በፊት በወርሀ ነሀሴ የሲድኒ ማራቶንን በ2:18:31 በማጠናቀቅ አሸንፋ ነበር። የናሙናው ውጤት ግን የሲዲኒውን ውጤት ጨምሮ በስፖርት ሕይወቷ ላይ ከባድ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
የጄፕቺርቺር ወኪል( ማናጀር) ጣሊያናዊው ጂያኒ ዴማዶና ከ”አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ” ( AFP) ጋር በነበራቸው ቆይታ ከአትሌቷ ጋር ለ13 ዓመታት በሙያዊ ግንኙነት እንደቆዩና በእሷ ላይ እምነት እንደነበረው ገልፀዋል። በAFP የዜና ዘገባ ላይ ዴማዶና ሲናገሩም በእሷ ላይ የጣሉት እምነት በመጉደሉ በማዘን “ሙሉ በሙሉ ተሳስቼ ነበር” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አትሌቷ ያስመዘገበችውን ታላቅ የስፖርት ስኬት በዚህ መልኩ ማበላሸቷ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል።
ዴማዶና በተመሳሳይ ለ”ሌትስራንዶትኮም” ድረ-ገፅ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ አትሌቶች ከውድድር መሰረዝ እንዳለባቸው አፅንኦት በመስጠት ገልጿል። እንደ ዴማዶና ገለጻ የዶፒንግ ቁጥጥር ባለሙያዎች በሐምሌ 17 ናሙና ለመውሰድ ወደ ጄፕቺርቺር መኖሪያ ቤት ሲሄዱ የመግባት ችግር ገጥሟቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ዴማዶና ራሳቸው ከእሷ ጋር ተነጋግረው ለምርመራ ባለሙያዎቹ በሯን እንድትከፍት እንደጠየቋት ተዘግቧል።
ይህ ጉዳይ በጄፕቺርቺር የስፖርት ሕይወት ላይ ከባድ ጥላ ያጠላ ቢሆንም አሁንም ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው። አንድ አትሌት በምርመራ ወቅት ሁለተኛ ናሙና ወይም ” B sample” ይሰጣል። በዚህ መሰረት ታዲያ ጄፕቺርቺርም ምርመራው ተጠናቆ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ሁለተኛው ናሙና ይመርምርልኝ ብላ የመጠየቅ መብት አላት። ምርመራው ተደርጎ ግን ውጤቱ ተመሳሳይ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከውድድር ታግዳ እንድትቆይ ይደረጋል።
የጄፕቺርቺር እገዳ ዜና ከተሰማ በኋላ አትሌቶችና የሩጫ ስፖርት ተከታታዮች በማህበራዊ ሚዲያ ሀሳባቸውን እያንሸራሸሩ ይገኛሉ። አንዳንዶቹ የአበረታች ንጥረ-ነገር ጉዳዮች በተደጋጋሚ መከሰታቸውን በመቃወም በንጹሕ ውድድር የሚያምኑ አትሌቶች የሚያጋጥማቸውን ተጽዕኖ አንስተዋል።
የኦሎምፒክ የማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊና የስፖርት ተንታኟ ካራ ጎቸር በጉዳዩ ላይ በሰጠችው ሀሳብ በውድድሮች ላይ ከጄፕቺርቺር በኋላ የጨረሱ አትሌቶች ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ አሳስባለች። ጎቸር “በማራቶን ውድድር ከጄፕቺርቺር ኋላ የጨረሱና በውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ የደረሰባቸው አትሌቶች ሁኔታ ያሳዝነኛል።” ብላለች።
አሜሪካዊቷ ሯጭ ናቶሻ ሮጀርስ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ የተደጋጋሚ የአበረታች ንጥረ-ነገር ዜናዎች ላይ ብስጭቷን ገልጻለች። እሷም ጉዳዩ እንደተለመደ ዜና መታየቱን ኮንና የሚወሰዲ እርምጃዎች ጠንካራ እና ውጤታቸው የሚታይ መሆን እንዳለበት ጠቁማለች።
የጄፕቺርቺር ጉዳይ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ኮ የዶፒንግ ቁጥጥር ሥራዎችን እንዴት እየመሩ ነው በሚለው ላይም ተጨማሪ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
ኮ በወርሀ ጥቅምት 2026 በናይሮቢ በነበረው ጉብኝታቸው ኬንያ የ2029 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ማስተናገዷ በሀገሪቱ ያለውን የአበረታች ንጥረ-ነገር ችግርን ለመታገል የበለጠ ትኩረት እንደሚያመጣ ተናግረው ነበር።
ኮ የዶፒንግ ቁጥጥር እየተሻሻለ እንደሆነም ሲገልፁ ተደምጠዋል። የ”አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት” የሚያካሂደው ምርመራ ከቀድሞው የበለጠ ጥልቅ፣ ሰፊና በመረጃ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን ዓለም አቀፉ የአበረታች ንጥረ-ነገር ቁጥጥር ሥርዓት ፍጹም ሊሆን እንደማይችልም አምነዋል።
ኬንያ በ2029 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ መመረጧ ለአፍሪካ ታሪካዊ እድል ነው። ይሁን እንጂ በአገሪቱ የዶፒንግ ጉዳዮች በተደጋጋሚ መነሳታቸው የዝግጅቱን የስፖርት ታማኝነት አስመልክቶ ጥያቄዎች አስነስቷል። የኬንያ የአትሌቲክስ የወጣቶች ልማት ዳይሬክተርና የአገሪቱ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝዳንት ባርናባስ ኮሪር፣ የጄፕቺርቺር እገዳ ኬንያ የ2029 ሻምፒዮናን እንድታስተናግድ ከተመረጠች ብዙም ሳይቆይ መሰማቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
የዓለም ፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካም ኬንያ እንደ “የሻምፒዮኖች አገር” የምትታወቅ ከሆነ ይህንን ስም ለመጠበቅ ንጹሕ ስፖርትን ማረጋገጥ እንዳለባት አሳስበዋል። በመሆኑም የጄፕቺርቺር ጉዳይ የአንድ አትሌት የግል ችግር ብቻ አይደለም። የኬንያን የዶፒንግ ቁጥጥር ሥርዓት፣ የዓለም አትሌቲክስ የቁጥጥር አቅምና በንጹሕ ውድድር ላይ የሚኖረውን እምነት በድጋሚ እንዲመረመሩ የሚያደርግ ጉዳይ ነው።
አበረታች ንጥረ-ነገር ከመውሰድም በላይ መዘዝ ያስከተለው የሩቲ አጋ “ፌክ” የህክምና ወረቀት..

የ32 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ሯጭ ሩቲ አጋ በ2019 የቶኪዮ ማራቶንን በ2:20:40 በማጠናቀቅ አሸንፋ ነበር። አቱን ላይ ታዲያ ከአበረታች ንጥረ-ነገር ጋር በተያያዘ ስድስት ዓመት ከውድድር እንድትታገድ ተወስኗል።
የ”አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት” በጥቅምት 13 ባወጣው መግለጫ ሩቲ በመጋቢት 2026 በቻይና በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ካሸነፈች በኋላ በተወሰደ ናሙና ውስጥ ሜቲልፕሬድኒሶሎን (Methylprednisolone) የተባለ ንጥረ ነገር መገኘቱን አስታውቋል።
ይህ ንጥረ ነገር እብጠትንና ሌሎች የጤና ችግሮችን ለማከም የሚያገለግል የኮርቲኮስቴሮይድ መድኃኒት ነው። ለስፖርተኞች ግን አጠቃቀሙን በተመለከተ የተቀመጠ መርህ አለ።ሩቲም ያንን ደንብ ተላልፋለች በሚል ጉዳዩ ከአበረታች ንጥረ-ነገር ጋር ሊያያዝ ችሏል።
ሩቲ መድሀኒቱ በደሟ ውስጥ በመገኘቱ ቅጣት የተላለፈባት ሁለት አመት ቢሆንም ከዛ በኋላ ለምን መድሀኒቱን እንደተጠቀመች ለማስረዳት ያቀረቀችው የህክምና ማስረጃ ” ፌክ” መሆኑን ተከትሎ ተጨማሪ 4 አመት እንድትቀጣ ሆኗል።
መድኃኒቱን የወሰደችው በጉልበቷ ላይ ያጋጠማትን ሕመም ለማከም እንደሆነ የጠለፀችው ሩቲ ለዚህም ድጋፍ እንዲሆናት በኢትዮጵያ በሚገኝ ሐኪም የተሰጠ ነው ያለችውን የሕክምና ማዘዣ ለመርማሪዎች አቅርባለች። ሆኖም በምርመራው ወቅት በማዘዣው ላይ የተጠቀሰው ክሊኒክ እንደሌለ ተረጋግጧል። የህክምና ማዘዣውን የፈረመው ሰውም የሩቲ የቤተሰብ አባል ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ሰው በሚመለከተው ባለሥልጣን መስሪያ ቤትም ሕክምና ባለሙያ ሆኖ ያልተመዘገበ መሆኑም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ማዘዣውን የፈረመው የቤተሰብ አባሏ ከዚህ ቀደም ይሠራበት ከነበረ የሥራ ቦታ የቀረ የቀድሞ የሐኪም ማዘዣ ወረቀት እንደተጠቀመ ቢናገርም የተጠቀሰው ክሊኒክ ግን ግለሰቡ በዚያ ቦታ ሠርቶ እንደማያውቅ እና ማዘዣዝም የክሊኒኩ እንዳልሆነ መረጋገጡ ተዘግቧል።
በዚህ ምክንያት አበረታች ንጥረ-ነገሩ በሩቲ የደም ናሙና ውስጥ መገኘቱን ብቻ ሳይሆን፣ ምርመራውን ለማሳሳት የሐሰት መረጃና ሰነድ ተጠቅማለች የሚለውንም ክስ አካቶ የ6 አመታት ቅጣት ተጥሎባታል።
ኬንያና ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ዓለም ከታላላቅ አትሌቶች የሚያፈሩ አገራት ናቸው። ሆኖም በከፍተኛ ደረጃ የሚወዳደሩ አትሌቶች በዶፒንግ ጉዳዮች መካተታቸው በስፖርቱ ቤተሰቡ ዘንድ ሌሎችስ? በሚል ጥርጣሬን የጫረ ጉዳይ ሆኖ እየተንሸራሸረ ይገኛል።
