ጂያኒ ዴማዶና: ከአትሌቶች ጀርባ ያለው ታላቅ ሰው( ‘ኤክስክሉሲቭ’ ቃለ-ምልልስ)

ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ከትላልቅ አትሌቶች ጀርባ የሚጠበስ አንድ ትልቅ ሰው አሉ። እኚህም ሰው ጂያኒ ዴማዶና ይሰኛሉ። ዴማዶና እውቅ የአትሌቶች ማናጀር ሲሆኑ በስሩ ትግስት አሰፋ እንዲሁም ታምራት ቶላ የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይገኛሉ። ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ሰባስታያን ሳዌን እንዲሁ በቅርበት ይከተላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ማራቶንን ከ2 ሰአት በታች በመግባት ባለሪኮርድ የሆነው ሰባስትያን ሳዌም በእርሳቸው ስር ከነበሩ አትሌቶች መሀል ይጠቀሳል።

ዴማዶና አሁን 72 አመት የሞላቸው ሲሆን የአትሌቶች ማናጀር ከመሆናቸው በፊት ሯጭ ነበሩ። በ1987ቱ የኒውዮርክ ማራቶን በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቁበት ውጤትም በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ስኬታቸው ነው። ጂያኒ ዴማዶና ከገፃችን ኢትዮጵያንስ ስፖርት ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ዴማዶና ለአመታት በርካታ አትሌቶችን ሲያስተዳድር ቆይቷል። አሁን ግን የሥራ ጫናውን ለመቀነስ ውሳኔ ማድረጋቸውን በቃለ-ምልልሳችን መጀመሪያ ላይ አጫውተውናል። “ከጥር 2025 ጀምሮ 95 በመቶ የሚሆኑትን አትሌቶቼን ለቀድሞ ረዳቶቼ ሞኒካ ፖንት እና ኤሪክ ሊሎት አስረክቤያለሁ” የሚሉት ዴሞዴና ለዚህ ውሳኔያቸወሰ ምክንያቱም የእድሜ መግፋት እንደሆነ ገልፀውልናል።  “72 ዓመቴ ነው። ትልቅ ኩባንያ ማስተዳደር ብዙ ሥራና ጭንቀት ይጠይቃል” ሲሉም ሀሳባቸውን ያብራራሉ።

ለጊዜው በቀጥታ የሚያስተዳድራቸው ወደ 10 የሚጠጉ አትሌቶች ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ባሳደጋቸው ሰዎች አማካይነት በዓለም አትሌቲክስ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ አሁንም ጠንካራ ነው። “እነዚህ ውጤቶች የመጡት ከብዙ ዓመታት ከባድ ሥራ፣ ከቁርጠኝነት እና በኢትዮጵያና ኬንያ ውስጥ ካሉን ጥሩ አሠልጣኞች ጋር በመሥራታችን ነው” ሲሉም የአትሌቶቹን ስኬት ዋነኛ ግብአቶች ይጠቅሳሉ።

ለዴማዶና የአትሌቶች አስተዳዳሪ( Manager) መሆን ማለት ኮንትራት መፈረም ወይም ለአትሌት ውድድር መፈለግ ብቻ አይደለም። እውነተኛው ሥራ አትሌቱ በሚያድግበት አካባቢ እንደሚጀምር ያምናል። “በጣም አስፈላጊው ሥራ የሚሠራው አትሌቶቹን በሚያሠለጥኑት በኢትዮጵያና ኬንያ ነው። ከዚያ በኋላ የማኔጅመንቱ ሥራ አትሌቱን በሙያው እንዲያድግ ማገዝ ነው” የሚሉት ዴማዶና በኬንያ ከአሠልጣኝ ክላውዲዮ ቤራርዴሊ እና በኢትዮጵያ ከአሠልጣኝ ገመዱ ደደፎ ጋር የሠሩትን ረጅም ትብብር ያነሳሉ።

በትልልቅ ማራቶኖች ወቅት ስላለ ዝግጅት ሲያነሱም “አትሌቶቹ ለለንደን ማራቶን ለመዘጋጀት ለአራት ወራት ይሠለጥናሉ” ይላሉ።  “አሠልጣኞች፣ ፊዚዮቴራፒስቶች፣ Tecar እና Indiba ያሉ የፊዚዮቴራፒ መሳሪያዎች፣ አትሌቶቹን ወደ ልምምድ የሚያጓጉዙ ሚኒባሶች እና በሜዳ ላይ የምንከታተላቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች አሉ” ሲሉም ከአትሌቶች ጀርባ ያለውን የዝግጅት ሂደት አብራርተዋል። ተመልካቾች በመጨረሻ የሚያዩት አትሌቱ የመስመር ላይ መድረሱን ብቻ ቢሆንም፣ ከዚያ ውጤት ጀርባ ወራትና ዓመታት የፈጀ ሥራ እንዳለ ዴማዶና አፅንኦት በመስጠት ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት ዴማዶና ከሚያስተዳድሯቸው አትሌቶች መካከል ዮሚፍ ቀጀልቻ ዋነኛው እንደሆነ በመግቢያችን ላይ ገልፀናል። ዮሚፍ በተለያዩ ርቀቶች ያለውን ልዩ ብቃት ቀደም ሲል አሳይቷል። በቅርቡ ባስመዘገበው ታሪካዊ ውጤት ደግሞ ሌላ ገጽ ከፍቷል።ዴማዶና ግን ዮሚፍ አሁን የደረሰበት ጣሪያው እንዳልሆነ ያምናሉ። ስለ ማራቶን የወደፊት ሪከርዶች ሲናገር ከሴባስቲያን ሳዌ ጎን ዮሚፍንም በልዩ ሁኔታ ጠቅሷል።”ሳዌ  ከ1 ሰአት 59 ደቂቃ በታች መሮጥ ይችላል። ዮሚፍም እንዲሁ..” ይላል። ይህ ንግግር ዮሚፍ በቅርቡ ካስመዘገበው ታሪካዊ ሪከርድ በኋላ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል።

ለዴማዶና ተሰጥኦ ብቻውን በቂ አይደለም። “ተሰጥኦ ቢኖርህም ሙሉ ትኩረትና ቁርጠኝነት ከሌለ ብቻውን ምንም ነው” ይላሉ።ዴማዶና ንግግሩን ሲበጥል አትሌት ሲመለከት በመጀመሪያ የሚፈልገው ተሰጥኦ መሆኑን መለስ ብሎ ያስታውሳል።  “በመጀመሪያ በአትሌቱ ውስጥ ያለውን ተሰጥኦ እንመለከታለን። ከዚያ በኋላ አትሌቱ አሠልጣኙ የሚነግረውን ለማዳመጥ ያለውን ዝንባሌ እንመለከታለን። ይህ በስፖርታዊ ልምምድ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሕይወቱን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበትም ይጨምራል” ሲሉም በዝርዝር ይናገራሉ። የስነ-ልቦና ድጋፍ ለአትሌቱ ወሳኝ እንደሆነ የሚጠቅሱት ዴማዶና አንድ አትሌት በተረጋጋ ሁኔታ አስቦ የሰከኑ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ካልቻለ ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ መቆየት አይችልም በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

ዴማዶና ስለ ኢትዮጵያዊቷ የማራቶን ኮከብ ትግስት አሰፋም በአድናቆት ተናግረዋል። በትክክለኛው ሁኔታ ከተገኘች የበለጠ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ እንደምትችል ያምናሉ። “ትግስት ከወንድ ፔሰሮች ጋር በምትሮጥበት ውድድር ከ2፡11 በታች መሮጥ ትችላለች። ምናልባት ከዚያም ፈጣን ትሮጣለች፣ ግን ጥሩ ፔሰሮችና ተስማሚ የአየር ሁኔታ ያስፈልጋሉ” የሚሉት ዴማዶና “ትግስት ቀስበቀስ ውድድር እንዴት እንደምታሸንፍ ተረድታለች” በማለት አብራርተዋል።

ትግስት አሰፋ በለንደን ማራቶን ” የሴቶች ብቻ” ( Women Only) ሪኮርድን መስበሯ ይታወሳል። ዴማዶናም እሱን መነሻ አድርገው ሲያብራሩ  “ከኦቢሪ እና ከጄፕኮስጌይ መራቅ እንደማትችል ስትረዳ ጉልበቷን ቆጠበች። በመጨረሻዎቹ 500 ሜትሮች ላይ 11 ሰከንድ ልዩነት ፈጠረችባቸው። አስደናቂ አጨራረስ ነበር” ብለዋል።

የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች  ለብዙ ዓመታት በረጅም ርቀት ሩጫ ዓለምን ተቆጣጥረው ቆይተዋል። ዴማዶና ከዚህ በስተጀርባ ያለው አንዱ ዋና ምክንያት ከፍታ( high altitude) እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ከፍታ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ልምምድ፣ ጥሩ አሠልጣኝ እና ሙሉ ቁርጠኝነት አንድን አትሌት ወደ ከፍተኛው ደረጃ እንደሚያደርሱ ያምናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.