42ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን በሐዋሳ ተካሄደ፦ ገመቹ ያደሳ እና ጠጅቱ ስዩም ድል ቀንቷቸዋል!

42ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሀዋሳ ከተማ የተካሄደ ሲሆን እኛም በውድድር ቅኝት ዘገባችን አጠቃላይ የውድድሩን መልክ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል። 

የውድድሩ ዓላማና ፋይዳ
ይህ ታሪካዊ የማራቶን ውድድር በየዓመቱ የሚዘጋጀው በኢትዮጵያና በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የማይደበዝዝ ደማቅ አሻራ ጥሎ ያለፈውን በኦሊምፒክ መድረክ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነውን ክቡር ሻምበል አበበ ቢቂላን ለማሰብ እና ታሪካዊ ስሙንና ዝናውን ህያው አድርጎ ለማቆየት ነው። ከዚህም ባሻገር ውድድሩ በሀገሪቱ ያሉ አዳዲስና ተተኪ የማራቶን አትሌቶችን ለማፍራት፣ ብቃታቸውን ለመፈተሽ እንዲሁም ክለቦችም ሆኑ በግል የሚወዳደሩ ስፖርተኞች ራሳቸውን ለዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲያዘጋጁ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ስፖርታዊ ውድድር ነው።

የውድድሩ ድባብ እና ተሳትፎ
ለ42ኛ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ ታላቅ የማራቶን ውድድር ውቧ የሲዳማ ክልል መዲና በሆነችው በሐዋሳ ከተማ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል። በጥቅሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ክለቦችንና የግል ተወዳዳሪዎችን ያካተቱ 323 አትሌቶች የተሳተፉበት ሲሆን ውድድሩ ብርቱ ፉክክርና ማራኪ ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት ነበር።

የወንዶች ማራቶን ውጤት
በወንዶች መካከል በተደረገው  ብርቱ ፉክክር የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ አትሌቶች የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። የዚሁ ክለብ አትሌት የሆነው ገመቹ ያደሳ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ የዘንድሮው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ሻምፒዮን መሆን ችሏል።

የወንዶች ሙሉ የደረጃ ሰሌዳ (ከ1 እስከ 8)፦
1. ገመቹ ያዴሳ (ኢትዮ ኤሌትሪክ) — 1ኛ ደረጃ (አሸናፊ)
2. ባንተ መኮንን (ኢትዮ ኤሌትሪክ) — 2ኛ ደረጃ
3. አቡ ገላው (መቻል) — 3ኛ ደረጃ
4. አዕምሮ ኃይሉ (ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን) — 4ኛ ደረጃ
5. ጥላሁን አበባው (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) — 5ኛ ደረጃ
6. ተመስገን ጎንፋ (ኦሮሚያ ፖሊስ) — 6ኛ ደረጃ
7. አሰፋ ማሩ (በግል) — 7ኛ ደረጃ
8. ልመንህ ጌታቸው (መቻል) — 8ኛ ደረጃ

የሴቶች ማራቶን ውጤት
በሴቶች ዘርፍ በተደረገው የማራቶን ፉክክር የመቻል ስፖርት ክለብ አትሌት የሆነችው ጠጅቱ ስዩም ድንቅ ብቃቷንና ጥንካሬዋን በማሳየት ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች። ከእሷ በመከተል የኦሮሚያ ፖሊስና የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቶች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

የሴቶች ሙሉ የደረጃ ሰሌዳ (ከ1 እስከ 8)፦
1. ጠጅቱ ስዩም (መቻል) — 1ኛ ደረጃ (አሸናፊ)
2. ኮረኒ ጃለሊ (ኦሮሚያ ፖሊስ) — 2ኛ ደረጃ
3. ትዕግስት ጌትነት (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) — 3ኛ ደረጃ
4. ጋዲሴ እሸቱ (ኦሮሚያ ፖሊስ) — 4ኛ ደረጃ
5. ተስፋነሽ መርጋ (ኦሜድላ) — 5ኛ ደረጃ
6. መሠረት ቂጣታ (ኦሮሚያ ፖሊስ) — 6ኛ ደረጃ
7. ኮሬ ታምሩ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) — 7ኛ ደረጃ
8. አያንቱ ገመቹ (ኦሜድላ) — 8ኛ ደረጃ

የአንጋፋ አትሌቶች (የ21 ኪሎ ሜትር) ውድድር
ከዋናው የ42 ኪሎ ሜትር ማራቶን ጎን ለጎን፣ ለአንጋፋ አትሌቶች መነቃቃትንና አርአያነትን ለመፍጠር የተዘጋጀ የ21 ኪሎ ሜትር የጎንዮሽ ውድድር በሁለት የዕድሜ እርከኖች ተከፍሎ ተካሂዷል፦
• ከ50 ዓመት በላይ የዕድሜ እርከን፦ አትሌት ገ/ሊባኖስ ገ/እግዚአብሔር አንደኛ በመሆን ሲያጠናቅቅ፣ አብደላ ሱሌይማን እና አያሌው እንዳለ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
• ከ50 ዓመት በታች የዕድሜ እርከን፦ አትሌት በቀለ ረታ ውድድሩን በቀዳሚነት የጨረሰ ሲሆን፣ ቦጋለ ሰይፉ እና አሠፋ መገርሳ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

የሽልማት ሥነ-ሥርዓት
ውድድሩ በስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ ለአሸናፊ አትሌቶች እውቅና እያ የገንዘብ ሽልማት የመስጠት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ በክብር እንግድነት በመገኘት፣ በደማቅ ፉክክር ላሸነፉት አትሌቶች የተዘጋጀላቸውን የሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት በክብር አበርክተውላቸዋል።

✍️ ዮናታን አየለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.